ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማር ለጤናችን ምን ያህል ጠቃሚ ነው? መመገብ ያለባቸውስ እነማን ናቸው?
ንቦች ከአበባ የሚገኝን ጣፋጭ ፈሳሽ [ኔክታር] ቀስመው የሚያዘጋጁት ማር ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት እንደ መድኃኒት ይቆጠራል።
ከቤት ውስጥ መጥፋት ከሌለባቸው ምግቦች ውስጥም ሲጠቀስ ይሰማል።
ጥንታውያን ግሪኮች ማርን “የፈጣሪ ምግብ” ሲሉ ነው የሚገልጹት። በቻይና ደግሞ መድኃኒት ተደርጎ ነው የሚታሰበው።
በአብዛኛው ወርቃማ ቀለም ያለው ይህ ጣፋጭ የተፈጥሮ ፈሳሽ ለምግብነት እና ለመድኃኒትነት የሚጠቅሙ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ ይዟል።
እንደየ አካባቢው እና ንቦች እንደሚቀስሙት የአበባ ዓይነትም ቀለሙ የተለያየ ይሆናል።
ለመሆኑ ከስኳር የሚጣፍጠው የተፈጥሮ ማር ብቸኛው የስኳር አማራጭ ነው? ለሁሉም ሰውስ በእኩል ይጠቅማል? ሕጻናትን ለመመገብስ የዕድሜ ገደብ አለው? የምንወስደው መጠንስ ምን ያህል መሆን አለበት?
ለእነዚህ የበርካታ ሰዎች የዘውትር ጥያቄዎች የሥነ ምግብ ባለሙያ የሆኑት ጆ ልዊን ምላሽ አላቸው።
ማር ምን ዓይነት ንጥረ ነገሮች አሉት?
ንጹህ የተፈጥሮ ማር [ያልተቀነባበረ] በውስጡ አሚኖ አሲድ፣ አንታይኦክሲደንት፣ ቫይታሚኖች፣ ሚኒራሎች እና ስኳር ይዟል።
ማር ከፍተኛ የፍሩክቶስ ይዘት ያለው በመሆኑም ከስኳር በላይ ጣፋጭ ነው። ነገር ግን ግላይቼሚክ ኢንዴክስ (ጂአይ) ባወጣው ደረጃ መሠረት ማር ያለው ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር (ካርቦሃይድሬት) መካከለኛ ነው።
ጂአይ እያንዳንዱ የምንመገበው ምግብ ተፈጭቶ በምን ያህል ፍጥነት በደማችን ውስጥ የሚገኝ የስኳር (ግሉኮስ) መጠን ላይ ተፅእኖ እንደሚያደርስ የሚያሳይ የመለኪያ ሥርዓት ነው።
አንድ የሾርባ ማንኪያ (20 ግራም) ማር 58 ኪሎ ካሎሪ፣ 15.3 ግራም ካርቦሃይድሬት፣ 15.4 ግራም ስኳር፣ 0.1 ግራም ፕሮቲን እና 0 ግራም ስብን ይይዛል።
የማር የጤና ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
የማር የጤና ጥቅሞች በሚቀነባበርበት መንገድ እና ንቦች በሚቀስሙት የአበባ ጥራት ላይ ይወሰናል።
ንጹህ የተፈጥሮ ማር በማንኛውም መንገድ ያልቀለጠ፣ ያልተቀነባበረ፣ ያልተጣራ፣ ያልተጠለለ ወይም ሌላ ግብዓት ያልተጨመረበት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ማር በማቀነባበር ሒደት ያልተወገዱ እና ለጤና የሚጠቅሙ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ነው።
በሚይዛቸው ንጥረ ነገሮችም ማር ለበርካታ ዓመታት ረቂቅ ተህዋስያንን ለማጥፋት ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።
መጠነኛ የሆነ ቆዳ ላይ የሚያጋጥሙ ቁስሎችን፣ የብግነትን ( አልሰር) እና የቃጠሎ ጉዳቶችን የማገገም ሒደትን ማር ያፋጥናል ተብሎም ይታመናል።
ማር በውስጡ ግሉኮስ እና ፍሩክቶስ የተባሉ የስኳር ዓይነቶችን የያዘ ሲሆን፣ እነዚህ ስኳሮች ደግሞ ፈሳሽን የመምጠጥ ባህሪ አላቸው።
በመሆኑም በውስጡ እነዚህን የስኳር ዓይነቶች የያዘው ማር በቁስል ላይ ያለን ፈሳሽ የመምጠጥ እና የማድረቅ አቅም አለው። ይህም በተጎዳው አካል ላይ ያለውን የባክቴሪያ እና የፈንገስ እድገትን ይገታል።
ጠቆር የሚለው የማር ዓይነት ደግሞ ‘ፍላቮኖይድ’ በተባለ ኬሚካላዊ ውህድ የበለጸገ ነው።
ፍላቮኖይድ ፀረ ባክቴሪያ፣ ፀረ ቫይረስ፣ እንዲሁም አለርጂ እና የሰውነት መቆጣትን የሚከላከል ንጥረ ነገር አለው። ባለው የፍላቮኖይድ ንጥረ ነገር ምክንያትም በርካቶች ስኳርን እና አንታይኦክሲደንትን ለማግኘት ማርን እንደ ጤናማ የምግብ አማራጭ ይወስዱታል።
ሆኖም ግን አወሳሰዱ ላይ ጥንቃቄን ሲያደርጉ አይስተዋልም።
የሥነ ምግብ ባለሙያ የሆኑት ጆ ልዊን እንደሚሉት ማር ከአንድ የሾርባ ማንኪያ ስኳር ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ የካርቦሃይድሬት መጠን ነው ያለው። ሆኖም በውስጡ የያዘው ከፍተኛ የካሎሪ መጠን በደም ውስጥ ያለን የስኳር መጠን ስለሚጨመር በመጠኑ እንዲወሰድ ይመክራሉ።
ከማር እና ከስኳር ለጤና የተሻለው የቱ ነው?
ማር ከስኳር ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ የካርቦሃይድሬት መጠን ያለው። ይህ ማለት በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን እንደ ስኳር በፍጥነት አይጨምረውም ማለት ነው። ማር ከስኳር ይበልጥ ጣፋጭ በመሆኑም መመገብ የሚያስፈልገን ትንሽ ነው።
አንድ የሾርባ ማንኪያ ማር ብዙ ካሎሪ ስላለው በምንወስደው መጠን ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
ማር ምርጫችን ከሆነና መመገብ የምንችል ከሆነ ከስኳር ይልቅ ብዙ ቫይታሚኖችን፣ ኤንዛይሞችን፣ አንታይኦክሲደንቶችን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን በውስጡ የያዘውን ንጹህ የተፈጥሮ ማር መመገብ የጤና ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ባለሙያው አስረድተዋል።
ማር ለሁሉም ሰው ጠቃሚ ነው?
በሚመከረው መጠን ልክ ከተወሰደ ማር ከስኳር ነጻ እንደሆነ ምግብ የሚቆጠር ነው። ለበርካታ አዋቂዎችም ጤና ጠቃሚ ሲሆን፣ የሚያስልጋቸውን ትክክለኛ መጠን ግን ማወቅ ይጠበቅባቸዋል።
ስኳር ላለባቸው ሰዎች አሊያም በደማቸው ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለማስተካከል ጥረት እያደረጉ ያሉ ሰዎች ስኳርን በማር መተካታቸው “አልሸሹም ዞር አሉ” እንደማለት ነው። ምክንያቱም ሁለቱም በደም ውስጥ ያለን የስኳር መጠን ይጨምራሉ።
ከዚህም ባሻገር ከ12 ወር አሊያም ከአንድ ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ንጹህ [ያልተቀነባበረም] ሆነ የተቀነባበረ ማር መመገብ የለባቸውም። ምንያቱም የሰውነት የነርቭ ሥርዓት ላይ ጉዳት ለሚያደርስ ‘ቦቱሊዝም’ ለተባለ የምግብ መመረዝ ተጋላጭ ሊያደርጋቸው ስለሚችል ነው።
ምንም እንኳን አብዛኞቻችን ማርን በምግብ ዝርዝራችን ውስጥ ብናካትትም በሁሉም ሰው ዘንድ ተቀባይነት ላይኖረውም ይችላል።
የእንስሳት ተዋፅኦ ለማይመገቡ [ቪጋን] ለሆኑ ሰዎች ማር ተመራጭ አይደለም። ምክንያቱም ማር ምንም እንኳን ምንጩ አበባ [እፅዋት] ቢሆንም በክረምት ወራት የራሳቸውን ሕይወት ለማቆየት ሲሉ ታትረው ማር ከሚሰሩት ንቦች ጋር ስለሚያያዝ በቪጋኖች ዘንድ እንደ የእንስሳት ተዋፅኦ ይቆጠራል።