የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣው ሲሰረዝ አስር ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የተካሄደው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ማውጣት ሂደት ውድቅ ሲደረግ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አስር ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንዳስታወቁት የዕጣ ማውጣት ሂደቱ ተዓማኒነት የሌለው ስለነበረ ዕጣው ሙሉ ለሙሉ ውድቅ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

ከንቲባዋ በእጣ ማውጣት ሂደቱን በተመለከተ የነበሩ ጉድለቶችን አስመልክቶ ለአስተዳደሩ ጥቆማ በደረሰው ጊዜ በአስቸኳይ የማጣራት ሥራ መካሄዱን ገልጸዋል።

በዚህም “የቴክኖሎጂ ውንብድና አጋጥሞናል፣ ድርጊቱን አመራር የመራው ወንበዴ ነው። በዚህ ሂደት የቤት ስርቆት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፍላጎት ጭምር መግለጽ ይቻላል” ሲሉ ድርጊቱ ፖለቲካዊ አላማንም የያዘ ነው ብለዋል።

ከዚሁ ሁኔታ ጋር በተያያዘ አንድ የቢሮ ኃላፊ ከኃላፊነታቸው ሲነሱ ከከተማው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ እንዲሁም የቤቶች ልማት ቢሮ አስር የሚሆኑ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ሙሉቀን ሃብቱ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ደግሞ ምክትል የቢሮ ኃላፊው አብርሀም ሰርሞሎ፣ ዳይሬክተሩ መብራቱ ወልደኪዳን ዳይሬክተር፣ .የቤቶች ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ኩምሳ ቶላና የሶፍትዌር ባለሙያዎች የሆኑት ፣ ሀብታሙ ከበደ፣ ዮሴፍ ሙላት፣ ጌታቸው በሪሁን፣ቃሲም ከድር፣ ስጦታው ግዛቸው፣ ባየልኝ ረታ፣ ሚኪያስ ቶሌራ መሆናቸውን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።

ባለፉት ቀናት በከተማው ነዋሪ ዘንድ ዋነኛ መነጋገሪያ በሆነው እና በአስተዳደሩ ውስጥም ዋነኛ ጉዳይ ሆኖ ቆይቶ ዕጣው ሲሰረዝ በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል።

የአዲስ አበባ መስተዳድር እንዳለው ይህ እርምጃ በዚህ የሚቆም እንዳልሆነ አመልክቶ እንደየተፈጸመው ጥፋት መጠን እርምጃው የሚቀጥል ይሆናል ብሏል።

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለማግኘት ለተመዘገቡ ሰዎች የተካሄደውን ይህ የዕጣ ሂደት ተከትሎ ቅሬታዎች ቀርበው ምርመራ የተጀመረ ሲሆን ከታዩ ጉድለቶች ጋር በተያያዘ የከተማው አስተዳደር ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ሲነገር ቆይቷል።

የከተማው አስተዳደር ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይም ቤቶቹን ለማስተላለፍ ከተከናወነው የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት በኋላ የተለያዩ ጥቆማዎች መቅረባቸውን አመልክቷል።

ይህንንም ተከትሎ በዕጣው ውስጥ በተካተተው መረጃ ላይ በተደረገው ማጣራት “በባንክ የተላከውና ለዕጣ እንዲውል ወደ ኮምፒውተር የተጫነው ዳታ ላይ ልዩነቶች ተግኝተዋል” ሲል ተፈጠረ ያለውን ችግር አመልክቷል።

ጨምሮም ባለፈው አርብ በወጣው የቤቶች ማስተላለፍ የዕታ ሂደት ላይ በተደረገው ማጣራት “ላልቆጠቡ ሰዎች ዕጣ መውጣትን ጨምሮ የተለያዩ የተዓማኒነት ጉድለቶች ታይተዋል” ሲል ገልጿል።

በዚህም ምክንያት የቤት ማስተላለፍ ሂደቱ ላይ ተከስተዋል የተባሉ “የተዓማኒነት ጉድለቶች” ገለልተኛ በሆኑ በሚመለከታቸው ተቋማት ተጨማሪ የማጣራት ሥራ በመከናወን ላይ ነው ብሏል የከተማው አስተዳደር ባወጣው መግለጫ።

ከተከሰተው የአሰራር መዛባት ጋር በተያያዘም “የተጠረጠሩ ባለሙያዎች እና አመራር በቁጥጥር ሥር ሆነው ምርመራ እየተደረገባቸው” እንደሚገኝም አረጋግጦ ነበር።

ከተለያዩ የከተማው መስተዳደርና ከፌደራል መሥሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር በተደረገው ማጣራት በሂደቱ ላይ የተዛቡ አሰራሮች እንደነበሩ ተገልጿል።

ይህ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ለከተማው ነዋሪዎች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማቅረብ ሲካሄድ የቆየው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታና በዕጣ የማስተላለፍ ሂደት ከዚህ በፊትም ከነዋሪው በኩል ምላሽ ኣላገኘም ጥያቄ ሲነሳበት ቆይቷል።

ባለፈው ሳምንት የወጣውና ችግሮች ነበሩበት ተብሎ የተሰረዘው ዕጣ የማውጣት ሂደት ለ20/80 ቆጣቢዎች 14ኛ ዙር እንዲሁም ለ40/60 ቆጣቢዎች 3ኛ ዙር ነበር።