"ለ15 ዓመታት ኮንዶሚኒየም እየጠበቅኩ ሁለት ልጆች ወልጃለሁ" የአዲስ አበባ ነዋሪ

"ለ15 ዓመታት ኮንዶሚኒየም እየጠበቅኩ ሁለት ልጆች ወልጃለሁ" ይህ የተሰማው ስሜ አይጠቀስ ካሉ አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ነው።

ቤት የመኖር ተስፋቸውን ሰንቀው የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ ይደርሰኛል ብለው የተመዘገቡት በ1997 ዓ.ም ነበር።

የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንዲሰጣቸው በማህበር ተደራጅተው ከተመዘገቡት የመጀመሪያው ዙር ተመዝጋቢም መካከል ናቸው።

ለአስራ አምስት ዓመታትም ያህል ቤት ይደርሰኛል ብለው ጠብቀዋል።

በእርሳቸው ማህበር ውስጥ ከሚገኙት ከሃያ አባላቱ በላይ በሙሉ የቤት ባለቤት ቢሆኑም እርሳቸው ግን አልደረሳቸውም።

ከእርሳቸው የሚጠበቅባቸውን በየወሩ ምንም ሳያዛንፉ ከመቆጠባቸውም አንፃር ለምን አልደረሰኝም ብለው ሲያስቡም የሚሰጡት ምክንያት "ዕጣው ፍትሃዊ ስላልሆነ ነው" የሚል ነው።

"በመተዋወቅና በመጠቃቀም ቢሆን ነው እንጂ ይህንን ያህል ዓመት ጠብቄ የማይደርሰኝ ምክንያት የለውም" ይላሉ።

ከዚያም በተጨማሪ ያልተመዘገቡ ሰዎች ቤት እየተሰጣቸው እንደሆነም ሲሰሙ ይህንኑ ጥርጣሬያቸውን አረጋገጠላቸው።

ሆኖም ለዓመታትም ቤት ይኖረኛል በሚል ተስፋም የቆጠቡትን ብር ሊነኩም አልፈለጉም "ለሌላ ነገር እንዳላደርገው ሁሉ ይዞኛል" ይላሉ።

ሲመዘገቡ ገና ወንደላጤ ነበሩ አሁን ሁሉ ተቀይሮ ትዳር ይዘዋል። የሁለት ልጆች አባት ሆነዋል፤ ሆኖም የተመዘገቡት ኮንዶሚኒየም የውሃ ሽታ በመሆኑ "ላም አለኝ በሰማይ..." ሆኖባቸዋል።

ለአመታትም የኮንዶሚኒየም ዕጣ ሲወጣ በጉጉት ይጠብቃሉ። ይከታተላሉ ግን አልሆነም። የሚያውቋቸው ሰዎች ቤት አግኝተው ሳይኖሩበት ወይ ሲሸጡት ሲያዩ እርሳቸው በኪራይ ቤት መንከራተት ያሳዝናቸዋል።

በተከታታይም ቤቶች ልማት ሄደው ሲጠይቁም የተመዝጋቢዎች ዝርዝር ውስጥ እንዳሉ ይነግሯቸዋል።

"ሌሎች ሰዎች እየደረሳቸው ነው እንዴት ነው ነገሩ ብለን ስንጠይቅም 'ያው ስምህ አለ'" ከማለት ውጭ ሌላ ምላሽ ለዓመታት አልተሰጣቸውም።

"ጠብቅ" የሚለውም ምላሽ ተስፋ እያስቆረጣቸው እንደመጣ የሚናገሩት እኚህ ግለሰብ፤ ከሰሞኑ ደግሞ ከህገወጥ መሬት ወረራና ኢ-ፍትሃዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላ ጋር ተያይዞ በሚሰሙ መረጃዎች የነበረቻቸውም ትንሽ ተስፋ ተሟጠጠች።

"በጣም ያሳዝናል፤ ያሳፍራል፤ ከዚህ በኋላ ተስፋ አላደርግም" ይላሉ።

ቤት (መጠለያ) መሰረታዊ ጥያቄና መብት ቢሆንም በኢትዮጵያ ባሉ ትልልቅ ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ ሰዎች የግል ቤት መኖር ማለት እንደ ቅንጦት የሚታይበት ነው።

በርካቶች በማይቀመስ ኪራይ ብራቸውን እየገፈገፉ ለመኖርም ተገደዋል።

ገዝቶ የቤት ባለቤት መሆን የሚታሰብ ባይሆንም የጋራ መኖሪያ ቤቶች የጥራትና ሌሎች ጉድለቶች ቢኖርባቸውም፤ ለብዙዎች የቤት ባለቤት የመሆን ተስፋቸው ሆኖ ቆይተዋል።

ሆኖም ለዓመታት ጠብቀው ቤት ሳያገኙ የቀሩ እንዲሁም ቤቱ ደርሷቸው ያልተቀበሉ በርካቶች አሉ።

ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ በ40/60 የቁጠባ ፕሮጀክት ተመዝግበው በሁለተኛው ዙር የቤት እጣ እድለኛ እንደሆኑ ተነገሯቸው።

ከስድስት ዓመታት በፊት ተመዝግበው ዕጣው ወጥቶ ቤቱ ከደረሳቸው በኋላ፤ በድልድሉ መሰረት ውል ቢዋዋሉም ቤቱን ሳይረከቡ አንድ ዓመት አለፋቸው።

ሙሉውን መክፈል የሚችሉ መቶ በመቶ እንዲከፍሉ ካለበለዚያ ደግሞ በወጣው እቅድ መሰረት አርባ በመቶ ከፍለው ቀሪውን ደግሞ ከባንክ ጋር ውል ተፈፅሞ ቤታቸውን እንዲረከቡ ነበር።

የዛሬ ዓመትም የሚጠበቅባቸውን አርባ በመቶ ክፍያ ከፈፀሙ በኋላ ቁልፍ ለመረከብና ከቤቶች ልማትም ቤታቸውን ሊረከቡ የደረሳቸው ነገርም የለም።

በቅርቡ እንዲሁ እጣ የደረሳቸው ሰዎች በማህበር ሲደራጁ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲነገሩም ቤቱ አልቋልና ተረከቡ ተብለው ወደደረሳቸው አካባቢ ሄዱ።

በሁለተኛው ዙር 18 ሺህ ያህል እድለኞች መኖራቸውን የሚናገሩት እኚሁ ግለሰብ "ልንረከብ ሄደን ቤቱ አላለቀም፤ ቁልፍ ልንረከብ ሄደን ጭራሽ ቤቱ በር የለውም፤ ይሄ እንዴት ይሆናል? የማይሆን ሥራ ነው እየሰሩብን ያሉት" ብለዋል።

የአያት አካባቢ ነዋሪ የሆኑት እኚሁ ግለሰብ በሚኖሩበት አካባቢ የሚገኙ መሬቶች በአስደናቂ ፍጥነት መታጠራቸው ጥያቄያቸውን አጭሮታል።

በሳምንቱ መጀመሪያ፣ ሰኞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተባባሰ የመጣ፣ የመንግሥታዊ መዋቅሮች ድጋፍ ያለው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላ እንዳለ ባካሄድኩት ጥናት ደርሼበታለሁ ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።

የጋራ ቤቶችን በተመለከተም የከተማው አስተዳደር ባወጣው ደንብ መሰረት "በምንም መስፈርት የቤት ተጠቃሚ ሊሆኑ የማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤትና የነዋሪነት መታወቂያ ተሰጥቷቸዋል" ሲል በጋራ የመኖሪያ ቤቶች በኩል አሉ ያላቸውን የአሰራር ችግሮች ጠቅሷል።

ጥናቱ እንዳለው በከተማዋ የተለያየ አይነት ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ተግባራት እንደተከናወኑ አመልክቶ፤ እነዚህም በጅምር ቤት ስም ከባለ ይዞታዎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በመግዛት ግንባታ የማካሔድ፣ ባዶ መሬቶችን በቡድንና በግለሰብ ደረጃ በማጠር የመያዝ እንዲሁም ለሌላ ወገን የማስተላለፍ በተጨማሪም "በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በተዘረጋው ሰንሰለት በጥቅም ተጋሪነትና በዝምድና" ሠፋፊና ቁልፍ ቦታዎችን መያዝ በከተማዋ ውስጥ መታየቱን ገልጿል።

የቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የአሁኑ የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፤ በቀጥታ የኢዜማን ጥናት ባይጠቅሱም ማክሰኞ ዕለት በፌስቡክ ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ የቀረበውን ሪፖርት " ሐሰተኛ" ብለውታል።

አቶ ታከለ እንዳሰፈሩት "የመሬት ወረራን በተመለከተ ከመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ እለት ድረስ ጠንካራ የሆነ እርምጃ ስንወስድበት የቆየንበት ጉዳይ ነው" ብለዋል።