የቢቢሲ ጋዜጠኛ ወሲባዊ ይዘት ላላቸው ፎቶዎች ለታዳጊ መክፈላቸው ተጠቆመ

የቢቢሲ የቴሌቭዥን መርሃ ግብር አቅራቢ አንድ ታዳጊ ወሲባዊ ይዘት ያለው ፎቶግራፍ እንዲልኩ ገንዘብ መክፈላቸውን ዘ ሰን ዘገበ።
ማንነታቸው እንዲሁም ፆታቸው ያልተገለጸው ጋዜጠኛ ማንነታቸው እንዲሁም ፆታቸው ያልተገለጸ ታዳጊን ከ17 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ልቅ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ፎቶዎች እንዲልኩ በአስር ሺህ ፓውንዶች የሚቆጠር ገንዘብ መክፈላቸውን የጋዜጣው ሪፖርት ይጠቁማል።
ቢቢሲ ይህንን ጉዳይ እየመረመረ ሲሆን የቴሌቭዥን አቅራቢው በቀጣይ ቀናት በቴሌቭዥን አይቀርቡም።
ዘ ሰን እንደዘገበው የታዳጊ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ቅሬታቸውን ግንቦት ላይ አስገብተዋል።
ጋዜጠኛው ቴሌቭዥን ላይ መቅረብ በመቀጠላቸው ቤተሰቡ ሐዘን እንደተሰማው ተገልጿል።
እናትየው ለጋዜጣው እንደተናገሩት፣ ልጃቸው ከ17 ዓመት እስከ 20 ዓመት በዚህ ሂደት አልፈው፣ ከጋዜጠኛው የተከፈለን ገንዘብ ኮኬይን መግዣ ሆኗል።
“ደስተኛ ልጄን በአደገኛ ዕጽ ውስጥ አገኘሁ” ሲሉ የሦስት ዓመታት ሐዘናቸውን ተናግረዋል።
ተቋሙ ጉዳዩ “በፍጥነት እንደሚመረመር” መግለጹም ተዘግቧል።
የቢቢሲ ቃል አቀባይ “ማንኛውንም ክስ በቁም ነገር ነው የምንወስደው። ይህንን የሚመለከት አሠራርም አለን” ሲሉ ተናግረዋል።
“ተጨማሪ ምርመራ ወይም ክትትል የሚያስፈልገው ክስ ሲደርሰን ያንን በማድረግ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉም አክለዋል።
ይህ ሂደትም “መረጃውን የሰጡ ሰዎችን ማነጋገርና ተጨማሪ መረጃ አግኝቶ ነገሩን በጥልቀት መረዳት” እንደሚያካትት ገልጸዋል።
መረጃ የሰጠው አካል “ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ሙከራ ሲደረግ ምላሽ ካላገኘን ወይም ምርመራውን ለመቀጠል እንቸገራለን። ይህ ማለት ግን ምርመራውን እናቆማለን ማለት አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በተጨማሪም “በማንኛው ሰዓት በጋዜጣ የወጣ ዘገባን ጨምሮ አዲስ መረጃ ስናገኝ ውስጣዊ አሠራር ተከትለን በተገቢው መንገድ ምላሽ እንሰጣለን” ብለዋል።












