ፕሬዚዳንት ባይደን ለዩክሬን አወዛጋቢ የጦር መሳሪያዎችን ለመላክ ወሰኑ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ንጹሃን ዜጎችን በመፍጀት ታሪክ ያላቸውን የክላስተር ቦምቦችን ለዩክሬን ለመላክ ወሰኑ።
ፕሬዚዳንቱ “አስቸጋሪ” ያሉትን ይህንን ውሳኔ ደግፈው በጽኑ ተሟግተዋል።
ፕሬዚዳንቱን ይህንን ውሳኔ አምኖ ለመፈጸም ትንሽ ጊዜ እንደፈጀባቸው በግልጽ ተናግረዋል።
ነገር ግን ለዚህ ቆራጥ እርምጃ ያደረሳቸው “የዩክሬናውያን ጥይት” በማለቁም እንደሆነ ነው ያስታወቁት።
የዩክሬኑ መሪ “ወቅቱን የጠበቀ” እርምጃ በማለት ሲያሞኳሹ የሞስኮ ልዑክ ደግሞ የአሜሪካን ውሳኔ ነቅፈውታል።
ክላስተር ቦምቦች ከ120 በሚበልጡ አገሮች ታግደዋል።
ፕሬዚዳንት ባይደን ይህንን ውሳኔያቸውን አስመልክቶ ከምዕራባውያን አጋሮቻቸውን ጋር መወያየታቸውን ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት በሉቴኒያ በሚደረገው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጉባኤም አገራቱ በዋነኛነት ከሚያነሷቸው አጀንዳዎች አንዷ ዩክሬን ናት።
የአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ባለስልጣናቱ ያልከሸፉ የክላስተር ቦምቦች “ለሰላማዊ ዜጎች አደጋ እንደሚጋርጡ ይገነዘባሉ” ብለዋል።
አማካሪው ይህንን ያሉት ዓርብ ዕለት በነበረው ዕለታዊ የዋይት ሃውስ መግለጫ ላይ ነው።
“ለዚህም ነው የምንችለውን ያህል እነዚህን መሳሪያዎች የመስጠት ውሳኔን ያራዘምነው” ብለዋል።
ጄክ ሱሊቫን እንዳሉት ዩክሬን ያላት የጦር መሳሪያ እየተመናመነ ነው።
አሜሪካ የሃገር ውስጥ ምርቷን ለመጨመር እቅድ በያዘችበት በአሁኑ ወቅት የጦር መሳሪያ አቅርቦት ዩክሬን በሰፊው እንዲዘረጋላት ትፈልጋለች።
“በዚህ የጦርነት ወቅት ዩክሬንን መከላከያ አልባ እንድትሆን አንተዋትም” ሲሉም ሱሊቫን ተደምጠዋል።
የክላስተር ቦምቦች በዓለም ላይ ከፍተኛ ውዝግብን በማስነሳት ይታወቃሉ።
ቶሎ ባለመፈንዳት የሚታወቁት እነዚህ ትናንሽ ቦምቦች ለዓመታት መሬት ላይ ቆይተው ባልተጠበቀ ጊዜ በመፈንዳት የንጹሃንን ህይወት ይቀጥፋሉ።
ሱሊቫን በበኩላቸው ወደ ዩክሬን የሚላኩት የአሜሪካ የክላስተር ቦምቦች ሩሲያ ቀደም ሲል በጦርነቱ ከተጠቀመቻቸው በተሻለ ደህንነታች የተጠበቀ ነው ሲሉም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።












