በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ይቅርታ ላይ ከትግራይ የተሰጠ ምላሽ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ የሚጠበቅበትን ባለመወጣቱ ያቀረበው ይቅርታ ጥሩ ጅምር መሆኑን በክልሉ የሚገኙ አባት ተናገሩ።
የሽረ እንደ ሥላሴ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ እና በመንበረ ሰላማ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑትን ንቡረእድ ተስፋይ ተወልደ “ይቅርታ ጥሩ ጅምር ቢሆነም፣ በቂ ግን አይደለም” በማለት ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ያካሄደውን ጉባኤ ተከትሎ፣ በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ወቅት የቤተክርስቲያኗን አባቶች እና ምዕመናንን ደኅንነት በመተመለከተ አስፈላጊውን ሁሉ ባለማድረጉ ይቅርታ መጠየቁን ገልጿል።
ለሁለት ዓመታት በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጦርነቱን በመደገፍና በትግራይ በደረሱ ጥፋቶች ዝምታን መርጣለች በሚል በትግራይ አባቶች እና ምዕመናን በኩል በጥብቅ ስትተች ቆይታለች።
“ይቅርታ መጠየቅ በቤተክርስቲያናችን የሚደገፍ ነው” ያሉት ንቡረእድ ተስፋይ ተወልደን “ቤተክርስቲያን ይቅር ባይ ናት። ይሁንና እኔ የአስተሳሰብ ለውጥ አድርገዋል ብዬ አላስብም። ጅምሩን ግን በበጎ ነው የምንመለከተው” ብለዋል።
“ይቅርታው የደረሰውን ጉዳት እና የመብት ጥሰት አይመልሰውም። የፈሰሰውን እንባን አያብሰውም። የፈሰሰውን ደም አይተካውም። እንዲያውም ይህ ይቅርታ ከልብ አይደለም። ስልታዊ ነው ይቅርታው።”
ጦርነቱ ከቆመ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ ክልል ካሉ አባቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ እና ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ባወጣው መግለጫ በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ወቅት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን “ጦርነቱ እንዲቆም በወቅቱ መግለጫ ባለመስጠቷ፣ በጦርነቱ መካከል ወደ ትግራይ ክልል መግባት እና መውጣት በሚቻልበት ወቅትም በክልሉ የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን እና መላው ሕዝበ ትግራይን በአካል በቦታው ተገኝታ ባለመጠየቋ እንዲሁም ባለማጽናናቷ” ይቅርታ እንደምትጠይቅ ሲኖዶሱ ገልጿል።
ንቡረእድ ተስፋይ “ይቅርታው ዘግይቷል” በማለት ለምን ይህን ያህል ጊዜ እንደቆየ ጠይቀዋል።
በትግራይ የተደረገው ጦርነት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ምን ያገናኛቸዋል ተብለው የተጠየቁት ንቡረእድ ተስፋይ “በገንዘብ በሞራል፣ እስከ ድንበር በመሄድ ነው ድጋፍ የሰጡት። ቤተክርስቲያኒቱ የእነርሱ አጋዥ ነበረች” በማለት አባቶች ጭምር በጦርነት ቅስቀሳ ውስጥ ተሳትፈዋል ሲሉ ከሰዋል።
ጨምረውም “ሰይጣን የሰላም ጸር እንደሆነ ነው በመጽሐፋችን የተቀመጠው እያለ፤ እነሱ ከሚመሩን ሰይጣን ይምራን ይሉ ነበሩ” እስከ ማለት ተደርሶ እንደነበር ገልሰዋል።
በግለሰቦች አባቶች የተባለ ነገር ቤተክርስቲያኒቱን እንዴት ሊወክል ይችላል ተብለው የተጠየቁት ንቡረእድ ተስፋይ “እነዚህ እኮ የሲኖዶሱ አባላት ናቸው። ይህን አስተያየት የሰጡት ግለሰቦች ናቸው፤ አስተያየታቸው እኛን አይወክልም ብላ ቤተክርስቲኗ መግለጫ አልሰጠችም” ብለዋል።
“ቀሳውስት እና መነኮሳት በየገዳማቱ ሲደፈሩ ዝም ብለዋል። ይህን ያደረጉት ግለሰቦች ናቸው አንልም። ለዚህም ነው ይህ ይቅርታ ስልታዊ ይቅርታ ነው የምንለው። ያም ሆኖ በበጎ ነው የምንመለከተው።”
ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና በአንድ ኢትዮጵያ ሁለት ቤተ ክርስቲያን ሊኖር ይችላልን? ተብለው የተጠየቁት ንቡረእድ ተስፋይ፣ የትግራይ አባቶች ተገፍተው እዚህ መድረሳቸውን በመጥቀስ “እነሱ ናቸው እኛን የነጠሉን። ሁሉ ጥፋቱም በነርሱ የመጣ ነው። የእኛ አይደለም። ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ይኑሩ ያልነው እኮ እኛ አይደለንም።”
ጨምረውም የክልሏ ቤተክርስቲያን ያለ መሪ፣ ያለ በጀት ለሦስት ዓመት ተዘንግታ እንደቆየች በማንሳት “አሁን ሕዝባችንን ማገልገል የእኛ ፋንታ ነው ብለን ተነስተናል። ይቅርታው የመጣው ይህን ጊዜ ነው” ብለዋል።
ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ፓትሪያርኩ አቡነ ማቲዮስን መሪያቸው መሆናቸውን እንደሚቀበሉ የገለጹት ንቡረእድ ተስፋይ፣ ይቅርታው ለመንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ያልተጠበቀ መሆኑን አንስተው “ጥሩ ጅማሮ ነው። ነገር ግን በቂ ነው አንልም” ብለዋል።
በመጨረሻም መንበረ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ወደፊት የራሱን ፓትሪያርክ ይመርጥ ይሆን? ተብለው የተጠየቁት አባት “ይህን መቼም እስከዛሬ ተነጋግረንበት አናውቅም። ሐሳቡም የለም። ፓትሪያርካችን ቅዱስነታቸው አቡነ ማቲያስ ናቸው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ “ጦርነቱ ቁሞ ሰላም ከወረደበት ጊዜ ጀምሮ ለደረሰው ጉዳት በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን ሰብአዊ ድጋፍ በውሳኔው መሠረት በወቅቱ ማድረስ ባለመቻሏ፣ በዚሁም የተነሳ በቤተ ክርስቲያኗ እና በመላው ሕዝበ ትግራይ መካከል ለተፈጠረው ቅሬታ እና አለመግባባት ቅዱስ ሲኖዶስ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።”
ይህ የቅዱስ ሲኖዶሱ ይቅርታ የቀረበው የቤተ ክርሰቲያኗ መሪዎች በትግራይ ክልል ካሉ አባቶች ጋር ለመነጋገር እና ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ለመሻት በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወደዚያው እንደሚያመሩ ከተገለጸ በኋላ ነው።












