ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደብረ ማርቆስ ከተማ በነበረ ግጭት ምክንያት በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተነገረ
በአማራ ክልል፣ ደብረ ማርቆስ ከተማ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በተከሰተ ግጭት ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ።
በአማራ ክልል ካሉ ትላልቅ ከተሞች አንዷ በሆነችው የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ደብረ ማርቆስ ሐሙስ ጥቅምት 08/2016 ዓ.ም. በተከሰተው የተኩስ ልውውጥ የሰዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በከተማዋ ነዋሪ የሆኑት እነዚህ ግለሰቦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በመከላከያ ኃይል እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በነበረው ተኩስ ቢያንስ አምስት ሰዎች ሞተዋል።
ካለፈው ዓመት ማብቂያ አንስቶ በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ የፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ሞቅ ቀዝቀዝ እያለ በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች ውስጥ እየተካሄደ ነው።
በዚህም ሳቢያ መደበኛ እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸው የሸቀጦች እና የመድኃኒት አቅርቦት በአንዳንድ አካባቢዎች መከሰቱን ነዋሪዎች ሰሞኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በመከላከያ ሠራዊት እና በታጣቂዎቹ መካከል የሚካሄደው ግጭት ከገጠሩ የአማራ ክልል አካባቢ በተጨማሪ በከተሞች እና በከተሞች ዙሪያ በተደጋጋሚ ተከስተዋል።
ሐሙስ ዕለት በደብረ ማርቆስ ያጋጠመውም ይኸው ሲሆን በግጭቱ በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ካልፈቀዱት ነዋሪዎች መካከል አንደኛው ቢያንስ አራት ሰዎች በግጭቱ ምክንያት በጥይት ተመትተው መሞታቸውን እንደሚያውቁ ሲናገሩ፣ ሌላኛው ደግሞ የሦስት ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው አርብ ጥቅምት 09/2016 ዓ.ም. መፈጸሙን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አምስት መውጫ በሮች እንዳሏት የሚናገሩት ነዋሪ በሦስቱ መውጫዎች በኩል የከባድ መሳርያ ተኩስ ሐሙስ ሙሉ ቀን ሲካሄድ መዋሉን ጨምረው ተናግረዋል።
ከተማዋ በፌደራል መንግሥቱ ጦር ሠራዊት ቁጥጥር ስር እንደሆነች የገለጹት ግለሰቡ፣ ወደ ከተማዋ የፋኖ ታጣቂዎች መጥተዋል በሚል ተኩስ እንደተከፈተ ይናገራሉ።
ላለፉት ወራት በተደጋጋሚ ግጭት በተከሰተባት እና መደበኛ እንቅስቀሴዋ በተስተጓጎለባት ከተማዋ፣ ለሰዓታት በዘለቀው የተኩስ ልውውጥ እና የከባድ መሣሪያ ተኩስ ቢያንስ አራት ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሞት ጉዳት ማድረሱን እንደሚያውቁ ነዋሪዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት በክልሉ ደፍርሶ የነበረው ሰላም እየተመለሰ ነው ቢልም፣ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች አሁንም ግጭቶች እንዳሉ እና የነዋሪው መደበኛ ሕይወት መስተጓጎሉን ነዋሪዎች እየገለጹ ነው።
ሐሙስ ዕለት በደብረ ማርቆስ ከተማ ግጭት መከሰቱ የተሰማውም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና ሌሎች የፀጥታ ባለሥልጣናት ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ከተዘገበ ከቀናት በኋላ ነው።
“ሐሙስ ጠዋት በግምት 3፡30 ላይ ገደማ ነው ተኩሱ የጀመረው። መቃ ወይንም ጉተራ የሚባል ሰፈር አካባቢ የተወሰነ የተኩስ ልውውጥ ነበር። ከሦስት አቅጣጫ ነበር ተኩስ የነበረው” ይላሉ ቢቢሲ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አንዱ።
ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው እኚሁ ግለሰብ ያሉትን አጠናክረው፣ ማለዳ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ በሮብ ገበያ መውጫ በኩል የከባድ መሳርያ ተኩስ መጀመሩን እና ለሰዓታት በመቀጠሉ ነዋሪዎች በጣሙን ተረብሸው እንደነበር ገልጸዋል።
ከዚያ በኋላ ደግሞ ከተወሰነ ጊዜ በኋለ ከከተማዋ በስተ ሰሜን በኩል በሚገኘው ወደ ክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር መውጫ ላይ ተኩስ መከፈቱን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
ጠዋት በተለያዩ የከተማዋ አቅጣጫዎች የተጀመረው ተኩስ ጋብ ሳይል ከሰዓት በኋላ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ደግሞ ጊቤ መውጫ ላይ ተኩስ መጀመሩን አክለዋል።
በከተማዋ የነበረው የተኩስ ልውውጥ በከባድ መሳርያ የታገዘ ነበር ያሉት እነዚህ ነዋሪዎች፣ ዙ 23 ወይንም ደግሞ የሞርታር ደምጽ ነበር ስንሰማ የነበረው ብለዋል።
“በተለይ የመንግሥት ወታደሮች የከፈቱት ተኩስ በከባድ መሳርያ ነበር። አብዛኛው የተተኮሰው ቤቶች ላይ ነው ያረፈው” ሲሉም ያክላሉ።
የተተኮሱ ከባድ መሳርያዎች በሰላማዊ ሰዎች መኖርያ ቤቶች ላይ መውደቁን ጨምረው የገለጹት ሌላኛው ነዋሪ፣ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ የፋኖ ታጣቂዎች ሲያፈገፍጉ መከላከያ ከተማዋን እንደተቆጣጣረ ቀርቷል ብለዋል።
ዛሬ አርብ በከተማዋ ያለው እንቅስቃሴ ቀዝቃዛ እንደበር የሚናገሩት ነዋሪዎቹ የጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ዝግ ሆነው መዋላቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ከክልሉ አስተዳደር፣ ከደብረ ማርቆስ ከተማዋ እንዲሁም ከህክምና ተቋማት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የፌደራል መንግሥት በየክልሉ ያሉ ልዩ ኃይሎችን ለመበተን እና ኢመደበኛ ያላቸውን ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት መንቀሳቀሱን ተከትሎ በአማራ ክልል ይፋ የወጣ ግጭት የተቀሰቀሰው ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ነው።
በዚህም ሳቢያ ያለው ሁኔታ ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ተጠይቆ የአስቸአኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ሠራዊቱን በክልሉ ውስጥ አሰማርቷል።
ክልሉ ባለፉት ሦስት ወራት ያለመረጋጋት ውስጥ የቆየ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት መደበኛ እንቅስቃሴዎች ከመደናቀፋቸው በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙ ግጭቶች በሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ከማጋጠሙ በተጨማሪ የንብረት ውድመት ደርሷል።