በአማራ ክልል ግጭት ምክንያት ነዋሪዎች በትራንስፖርትና መድኃኒት እጦት እየተሰቃየን ነው አሉ

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ግጭት ምክንያት በትራንስፖርት እና በመድኃኒት እጥረት ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸውን ተናገሩ።

በላሊባላ ደብረ ማርቆስ እና ሸዋሮቢት የሚገኙ ነዋሪዎች በቀጠለው ግጭት ምክንያት የትራንስፖርት ችግር፣ የመድኃኒት እጥረት እና መሰረታዊ ፍጆታዎች እጥረት እንዲሁም ዋጋቸውም መናሩን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎችም በመድኃኒት እጥረት ህሙማን ለከፋ አደጋ መጋለጣቸውንም ነው ነዋረዎች የሚናገሩት።

ከሰሞኑ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር የሚገኘው የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት ሥራ አቋርጦ እንደነበር ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ከሆስፒታሉ ሠራተኞች እና ከዩኒቨርስቲው ኃላፊ ለማረጋገጥ እንደቻለው ሆስፒታሉ የተለመደ መደበኛ ሥራውንም እየሰራ አልነበረም።

የአማራ ክልል መንግሥት ሰላም እየሰፈነ እና የአካባቢዎቹም የንግድ እንቅስቃሴ ወደቀደመ ሁኔታ እየተመለሰ ነው ይላል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የላሊበላ ነዋሪ በአካባቢያቸው ውጊያዎች እየተካሄደ እንደሆነ ገልጸዋል።

ብልባላ፣ አይና ቡግና፣ ኩል መስክ እና ጋሸና የተሰኙት አካባቢዎች ከቀናት በፊት ውጊያዎች ማስተናገዳቸውን ይናገራሉ።

እንቅስቃሴም በመገደቡ ከከተማ ውጭ ሰዎች መንቀሳቀስ የማይችሉበት ሁኔታም ተፈጥሯል።

በተለይም በላሊበላ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች ወደከተማዋ መግባት እና መውጣት በመከልከላቸው የግብርና ምርቶች በሶስት እና አራት እጥፍ ማሻቀባቸውንም እኚሁ ነዋሪ ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ውጊያዎች እየተካሄደባቸው ካሉ ስፍራዎች የሚመጡ አርሶአደሮች ወደ ከተማ ገብተው ምርቶቻቸውን መሸጥ በአሁኑ ወቅት አልቻሉም።

“ለፋኖ ድጋፍ ይሰጣሉ እንዲሁም ታጣቂዎቹ ከእነዚህ አርሶ አደሮች ጋር ተቀላቅለው ይገባሉ” በሚል ስጋትም ወደ ከተማዋ መግባት ተከልክለዋል።

አርሶ አደሮቹ ወደ ከተማዋ ከመጡም ድብደባና እንግልት እንደሚደርስባቸውም እኚሁ ነዋሪ ያስረዳሉ።

በዚህም ምክንያት ምርቶቹ በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋቸው መናሩን እንዲሁም እጥረት በማጋጠሙ የአካባቢው ነዋሪ ተቸግሯል ይላሉ።

አካባቢዎቹ ለሳምንታት እና ወራት እንቅስቃሴ በመገደቡም የገቢ ምንጭ መቀዝቀዙን እና የአካባቢውም ምጣኔ ኃብት እያሽቆለቆለም እንደሆነ ነው ነዋሪዎች የሚናገሩት።

በደብረ ማርቆስ አካባቢም ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪ “በሰላም ገብተን መውጣታችንንም አናውቅም” ይላሉ።

ከተማዋን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚያገናኙ አገር አቋራጭ ትራንስፖርቶች ከተቋረጡ መሰነባበታቸውን ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል።

ከእንቅስቃሴዎች ገደብ እና ከትራንስፖርት መቋረጥ ጋር ተያይዞም ከፍተኛ የመድኃኒት እጥረት ገጥሟል ይላሉ።

“ከመድኃኒት እጦት ጀምሮ ይሄ ነው ተብሎ መግለጽ አይቻልም፤ ቃላት ያጥራል። በመድኃኒት እጦት ምክንያት እናቶች ህይወታቸው አልፏል። ህክምና ባለማግኘታቸው ሰዎች እየሞቱ ነው” ይላሉ።

በአካባቢው በተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በከፊል ስራ ቢኖርም ውስን እንደሆነ ቢቢሲ ያናገራቸው የሸዋሮቢት ነዋሪ ገልጸዋል።

ኑሯቸው በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደገባ የሚናገሩት እኚህ ነዋሪ በከተማዋ ውጊያ ባይኖርም አካባቢው በግጭት እና በደህንነት እጦት ምክንያት እየተፈተነ እንደሆነ ይናገራሉ።

በአካባቢው የትጥቅ ትግል እየተካሄደ በመሆኑም እንቅስቃሴ ተገድቧል፤ መኪኖች በነጻነት መንቀሳቀስ አልቻሉም ይላሉ።

ነዋሪዎች በግጭት ምክንያት የአካባቢው ምጣኔ ኃብት ተቀዛቅዟል፣በኑሮ ውድነት እና በጸጥታ እጦት እየተፈተንን ነው ቢሉም የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንገሻ ፈንታው ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ በክልሉ የሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ሰላማቸው እየተመለሰ ነው ብለዋል።

በጸጥታ ችግር ተገድበው የነበሩ የንግድ እንቅስቃሴዎችም አሁን በተሻለ ሁኔታ ይገኛሉ ሲሉ ተደምጠዋል።

ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት በክልሉ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ መታወጁ ይታወቃል።

እስካሁንም ድረስ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ግጭቶች መቀጠላቸው ተዘግቧል። በዚህም ሳቢያ መደበኛ እንቅስቃሴዎች በመተስጓጓላቸው በጤና እና በአግልግሎት አቅራቢ ተቋማት ላይ ጫና መፈጠሩን ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው።