የቻይናው ዊቻት ምንድነው? ኢላን መስክ ዊቻትን መቅዳት የፈለገውስ ለምን ይሆን?

ባለፈው ሳምንት ኢላን መስክ የትዊተርን አርማ ከወፊቱ ምስል ወደ እንግሊዝኛው ፊደል [X] ኤክስ ቀይሮታል።

የቢሊየነሩ ዓላማ እንደ ቻይናው ዊቻት ያለ ሁሉን አቀፍ ‘አፕ’ አሊያም መተግበሪያ መፍጠር ነው።

ኢላን መስክ፤ ባለፈው ዓመት በ44 ቢሊዮን ዶላር የገዛውን ማኅበራዊ ሚድያ ወደ አንድ ታላቅ መድረክ መቀየር እንደሚሻ ሁሌም ይናገራል።

ከዚህ ቀደም ቱጃሩ የቴክኖሎጂ ሰው፤ “ሁሉን አቀፍ” በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው ዊቻት የተባለውን የቻይና መተግበሪያ ሲያደንቅ ተሰምቷል።

በዊቻት ቻይናውያን መነጋገር ይችላሉ፣ የፍቅር ጓደኛ ማፈላለግም ቀላል ነው፣ ክፍያ ለመፈፀም ይውላል፣ ማኅበራዊ ሚዲያነቱም አይረሳም።

“በትዊተር ይህን ለማድረግ መቃረብ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው” ሲል ተሰምቷል - መስክ።

በዚህ ሳምንት መስክ ኤክስ (በቀድሞው ትዊተር) ላይ በለጠፈው መልዕክት በመጪዎቹ ወራት “ጠንካራ የሆነ የግንኙነት ማዕከል የእርስዎን የፋይናንስ ዓለም መቆጣጠር የሚችል አቅም እንፈጥራለን” ብሏል።

እሱ ተስፋ እንደሚያደርገው ኤክስ እያደገ መጣ ማለት ገቢው አደገ ማለት ነው።

ኩባንያው በኢላን መስክ ከተገዛ በኋላ ከማስታወቂያ የሚያገኘው ገቢ ቢያንስ ግማሽ ያህሉን አጥቷል፤ በዕዳ ተዘፍቆ እየተንገላታም ይገኛል።

ዊቻት ምንድነው? ኢላን ሊቀዳው የሞከረውስ ለምን?

ቱንሴንት በተባለው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ በፈረንጆቹ 2011 የተቋቋመው ዊቻትን ከቻይና 1.4 ቢሊዮን ሕዝብ አብዛኛው ይጠቀመዋል።

ይህ መተግበሪያ ከሁሉ የላቀ አሊያም ‘ሱፐር አፕ’ ቢባል የሚገርም አይደለም።

ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል መልዕክት መላላክ፣ በድምፅ እና በምስል መደዋወል፣ ማኅበራዊ ሚድያ፣ ምግብ ማዘዝ፣ በሞባይል ስልክ ክፍያ መፈፀም፣ የሞባይል ‘ጌም’፣ ዜና እና የፍቅር ጓደኛ ማፈላለግ ይገኝበታል።

ዋትስአፕ፣ ፌስቡክ፣ አፕል ፔይ፣ ኡበር፣ አማዞን፣ ቲንደር እና ሌሎች መተግበሪያዎች አንድ ላይ ተጨፍልቀው የተሠሩበት እንደ ማለት ነው።

የቻይና ማኅበረሰብ እዚህ አፕ ላይ እጅግ ጥገኛ ከመሆኑ የተነሳ ያለዊቻት መኖር ከባድ ነው ማለት ማጋነን አይሆንም።

ልክ ከታች እንደምትመለከቱት ፎቶ እያንዳንዱን አገለግሎት መለየት ከባድ አይደለም።

ዊቻት መጀመሪያ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ልክ እንደ ዋትስአፕ መልዕክት መላላኪያ ነበር።

እንደ ዋትስአፕ መልዕክት መለዋወጫው ‘ቻትስ’ እና እንደ ፌስቡክ ያለው ‘ሙመንትስ’ ታዋቂ አገልግሎቶቹ ነበሩ።

ከዚያ ከባንክ ካርዶች ጋር መገናኘት ሲጀምር በርካታ የቻይና ሱቆች እና ምግብ ቤቶች ዊቻትን ለክፍያ መቀበል ጀመሩ።

ተጠቃሚዎች ክፍያ ለመፈፀም ‘ኪውአር ኮድ’ የተባለውን መንገድ ‘ስካን’ ማድረግ ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው።

ከዚህም አልፎ ተጠቃሚዎች የመብራት እና የውሃ አገልግሎትን ለመክፈል፣ ኢንቨስትመንት መፈፀም፣ በተጨማሪም ከዊቻት ብድር መውሰድ ጀመሩ።

ዊቻት ላይ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪዎች ይገኛሉ። ለትራፊክ ቅጣት እና ለሆስፒታል አገልግሎት ክፍያ ማድረግ ተፈቀደ።

በተለይ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ይህ አፕ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ብቅ አለ። በተለይ ቻይና ጠበቅ ያለ የእንቅስቃሴ ማዕቀብ በጣለችበት ወቅት እዚህ አፕ ላይ የተጫነውን ‘የጤና ኮድ’ ሳያሳዩ መንቀሳቀስ ከባድ ሆነ።

ቢሆንም በአንድ አፕ እነዚህ ሁሉ አገልግሎቶች ተጨፍልቀው መምጣታቸው የራሱ የሆነ አሉታዊ ጎን አለው።

ለምሳሌ ዊቻት በጣም ብዙ መረጃ ስለሚይዝ [እስከ አስራዎቹ ጊጋባይት የሚሆን መረጃ ይይዛል] የሞባይል ስልኮች ቋት ይጨናነቃል።

ከዚያ በተጨማሪ ዊቻት እያንዳንዱ ቻይናዊ ቤት መግባቱ የመንግሥት ሳንሱር፣ ክትትል እና ሌሎች የግላዊ መረጃዎች ጉዳይ አደጋ ላይ መውደቅ አሳሳቢ ይሆናል።

ቻይና ውስጥ በርካታ የሌሎች አገራት መተግበሪያዎች ፈቃድ የላቸውም። ከቢቢሲ ጀምሮ እንደ ፌስቡክ እና የኢላን መስክ ኤክስ [የቀድሞው ትዊተር] የተከለከሉ ናቸው።

መንግሥት ይህን ሁሉ ነገር በአንድ ቋት መቆጣጠሩ ሰዎች ዊቻትን ተጠቅመው ተቃውሟቸውን እንዳያሰሙ ያደርጋቸዋል።

አንዳንድ ተጠቃሚዎች በዊቻት አማካይነት ተቃውሞ በማሰማታቸው ገፃቸው ለቀናት አሊያም ለሳምንታት መዘጋቱ እንግዳ አይደለም።

ሌላው ቀርቶ ብዙም አወዛጋቢ የማይባል ነገር በዊቻት የለጠፉ ሰዎች ገፃቸው ሲዘጋ ይስተዋላል።

በምዕራቡ ዓለም ይሠራ ይሆን?

የቻይና ሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲው ኬቼንግ ፋንግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዊቻት ቻይና ውስጥ ስኬታማ የሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው።

አንደኛው በርካታ የቻይና ነዋሪዎች ዊቻትን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ማግኘት መቻላቸው ነው። ይህ ደግሞ ቻይና በተነፃፃሪ ዘግየት ብላ የኢንተርኔት ትስስር መረብን በመቀላቀሏ የተፈጠረ ነው።

“ሁሉን አቀፍ መተግበሪያ ኮምፒውተር ላይ ከማድረግ ስልክ ላይ ማድረግ እጅግ ይቀላል” ይላሉ።

ፋንግ አክለው እንደሚገልጡት ቻይና ከምዕራባውያን አገራት በተፃራሪ ውድድር ስለሌላት እንደ ዊቻት ያሉ መተግበሪያዎች ሌሎች ተፎካካሪዎችን በልጠው እንዲገኙ አስችሏቸዋል።

ታዎባዎ የተሰኘው የመበገያያ መተግበሪያ እና የቪድዮ አፕ የሆነው ዱዎይን ተፎካካሪ ተደርገው ይጠቀሳሉ።

ኢላን መስክ እንደ ዊቻት ያለ አፕ ከቻይና ውጭ ሊሠራ ይችል ይሆንን? ጊዜ ይፈታዋል። ባለሙያዎች ግን ስኬታማነቱ ዲጂታል ክፍያን የተንተራሰ ነው ይላሉ።

ዊቻት ቻይና ውስጥ ስኬታማ የሆነበት ምክንያት ለዕለት ተለት ኑሮ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ነው።

ኤክስ (ትዊተር) በዚህ ረገድ ስኬታማ እንዲሆን “ይህን ምሥጢራዊ ቅመም ማግኘት” አለበት ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

ምንም እንኳ የቻይና ሱቆች ጥሬ ገንዘብ እንዲቀበሉ በሕግ ቢገደዱም አብዛኛው ማኅበረሰብ ዲጂታል ክፍያን ይመርጣል።

የምዕራቡ ዓለም በምን ያህል ፍጥነት ጥሬ ገንዘብን እርግፍ አድርጎ ወደ ዲጂታል ግብይት ይሄዳል የሚለው ለኢላን መስክ ስኬት ትልቁ ምሥጢር ነው።