ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከወሊድ በኋላ ከ12 ሴቶች አንዷ ላይ የሚከሰተው የማህፀን መውረድ
ሔለን ላድዊክ "ለምንድን ነው ውስጤ እየፈረሰ እንዳለ የሚሰማኝ?" ብላ ጎግል ላይ መልስ ስትፈልግ ሕይወቷን የሚቀይር ነገር ያገጥመኛል ብላ አልጠበቀችም ነበር።
የቀድሞ የቢቢሲ 5 ላይቭ ጋዜጠኛ እና ፖድካስተር የሆነችው ሔለን የማህፀን መውረድ (ፔልቪክ ፕሮላፕስ) በተባለ ሕመም ተጠቅታለች።
ይህ ከ12 ሴቶች መካከል አንዷን የሚያጠቃው ሕመም በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ አይደለም።
የማህፀን መውረድ (ፕሮላፕስ) የሚከሰተው በዳሌ አካባቢ የሚገኝ የአካል ክፍል የሽንት ፊኛ፣ ወይንም ማኅፀን ከተለመደው ስፍራቸው ሲለቅቁ እንዲሁም በሴቶች መራቢያ አካባቢ እብጠት ሲፈጠር ነው።
ሕመሙ ሕይወትን አደጋ ላይ የሚልጥል ባይሆንም በዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ፣ በግንኙነት እንዲሁም በአእምሮ ጤና ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ ያሳርፋል።
ሔለን ሁለተኛ ልጇን ከወለደች ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው በዚህ ሕመም የተጠቃችው።
"ከሶፋ ላይ ተነስቼ መሄድ ስጀምር በድንገት ነገሮች ሲቀየሩ ተሰማኝ" በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።
"የንጽህና መጠበቂያ በትክክል ሳይቀመጥ ቀርቶ የሆነ ነገር ትክክል እንዳልሆነ እንደሚሰማ ዓይነት" ስትል የነበረውን ሁኔታ ትገልጸዋለች።
ግራ በመጋባት እና በፍርሃት ተውጣ፣ የሆነውን ለማየት መስታወት እና ስልኳን አነሳች።
"ከዚህ በፊት የማህፀን መውረድ (Pelvic Organ Prolapse) የሚለውን ቃል ሰምቼው አላውቅም ነበር" የምትለው ሔለን፣ ስለ ጉዳዩ በግልፅ ካወራች ጀምሮ ብዙ ጊዜ የተለመደ ቢሆንም "ነውር" ርዕሰ ጉዳይ እንደሆነ ተረድታለች።
ሔለን በሕመሙ ዙሪያ ያለው ሃፍረት እና መገለል በሴቶች እና በጤና ባለሙያዎች ላይ የግንዛቤ እጥረት እንዳስከተለ ታምናለች፤ በዚህም የተነሳ ያንን ለመለወጥ እየታገለች ነው።
ሔለን ምርመራ ከተደረገላት በኋላ ውጤቷን ተከትሎ "ማብራሪያ ለማግኘት ተስፋ ባደርግም፣ ለማስተካከል ወይም አንዳንድ ቶሎ መፍትሄ የሚሰጡ ነገሮች እንደሚኖሩ ብጠብቅም፣ በምትኩ ችላ በመባሌ" ግራ መጋባት እና ፍርሃት እንደወረራት ተናግራለች።
የመጀመሪያ ምክር የተሰጣት እንደ መሮጥ፣ መዝለል ወይም እቃ ማንሳትን የመሳሰሉ የከፋ ጉዳት ሊያስከትሉባት የሚችሉ ነገሮችን እንዳትሰራ ነበር።
"ምክሩ ሕይወትሽን አትኑሪ የሚል ስሜት ፈጥሮብኝ ነበር" ትላለች።
ምናልባትም ከአካላዊ ምልክቶቹ የበለጠ የሚያዳክም እና የመገለል ስሜት የሚፈጥር ነበር ትላለች።
"ከሕመሙ ጋር በመሸማቀቅ፣ በዝምታ፣ በሀፍረት እና በመገለል ትኖራለህ" ትላለች።
አክላም "ስለ ጉዳዩ ስለማትናገር፣ በዓለም ላይ ይህ የሆነበት ሰው አንተ ብቻ እንደሆንክ ታስባለህ" ብላለች።
ሔለን ድጋፍ ለማግኘት መጀመሪያ ወደ ኢንስታግራም አመራች።
በማኅበራዊ መድረክ ላይ በተመሳሳይ የተጨነቁ እና ግራ የተጋቡ እና በአንዳንድ ሁኔታዎች እርዳታ ለመጠየቅ በጣም የተሸማቀቁ ሰዎችን ማግኘቷ በመጨረሻ ፖድካስት እንድትጀምር እና 'ኋይ ማምስ ዶንት ጃምፕ (እናቶቸ ለምን አይዘሉም) በሚል ርዕስ መጽሃፍ እንድትጽፍ አነሳሳት።
ዓላማዋ ሴቶች ታሪኮቻቸውን የሚለዋወጡበት መድረክ መፍጠር እና በማህፀን ጤና ዙሪያ ያለውን ዝምታ መስበር ነበር።
"ስለ ጉዳዩ ማንም ስላልተወራ ተናደድኩ። ስለዚህ እንደማደርገው ወሰንኩ። ለሴቶች ለመድረስ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ያገኘሁትን እውቀት ለማዳረስ እና ብቻቸውን እንዳልሆኑ በማወቄ ማፅናኛን መስጠት ፈልጌ ነበር።"
የሴቶች ጤና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ኒግሃት አሪፍ የሔለን ሕመም በበርካታ ሴቶች ላይ የሚያጋጥም ቢሆንም ምልክቶቹ ሁል ጊዜ የማይታዩ በመሆናቸው መወያያ አለመሆናቸውን ይናገራሉ።
"አንዳንድ ጊዜ በግልጽ የሚታይ ምንም እብጠት የለም፤ የግፊት ስሜት ብቻ ይኖራል እና ምናልባት በታችኛው ጀርባ፣ ከፊት ወይም ትንሽ ከፍ ብሎ ከሆድ አጠገብ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።
"ምልክቶቹ በጾታ ግንኙነት ወቅት በይበልጥ ሊገለጡ ይችላሉ፤ ይህም በጣም የሚያሳፍር ያደርገዋል።"
የማህፀን መውረድ (Pelvic Organ Prolapse) በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል።
ለምሳሌ በወሊድ፣ ከባድ ዕቃ በማንሳት፣ ከመጠን በላይ በመወፈር ወይም የማህፀን ቀዶ ጥገና ከተደረገ በኋላ ይከሰታል። አልፎ አልፎ በወንዶች ላይም ሊከሰት ይችላል።
የማህፀን መውረድ ምክንያቶች
በተፈጥሮአዊ መንገድ በምጥ መውለድ ለማህፀን መውረድ ዋነኛ አጋላጭ ምክንያት ሲሆን በተለይም ደግሞ ክብደታቸው ከፍ ያለ ልጆችን መውለድ፣ ብዙ ልጆችን በምጥ መውለድና የምጥ መራዘም ዋና ዋና አጋላጫቾች ናቸው።
ሌላው እድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የማህፀን ደጋፊ ጡንቻዎች እየደከሙ ይመጣሉ። ይህም እድሜያቸው በገፉ ሴቶች ላይ የማህፀን መውረድ በስፋት እንዲከሰት አድርጎታል።
የማህፀን ሐኪም የሆኑት ዶክተር ክርስቲን ኤኬቺ የፕሮላፕስ ችግር ያለባቸው ሴቶች በብልታቸው ውስጥ እብጠት ወይም እጢ ሊያስተውሉ ይችላሉ "በመሰረቱ የሆነው ነገር በዳሌው ወለል ውስጥ ያሉት ጅማቶች ለምሳሌ ፊኛን የሚያንቀሳቅሱ መዳከም ስላለ ነው" ብለዋል።
በሦስተኛነት የሚጠቀሰው ደግሞ ሴቶች በመውለጃ ጊዜያቸው መጨረሻ ላይ የኤስትሮጂን ሆርሞን እየቀነሰ መሄድ ነው። ይህም የማህፀን ደጋፊ ጡንቻዎችና ሊጋሜንቶች እንዲረግቡ ያደርጋል።
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ክብደት መጨመር በተለይም ደግሞ ቢኤምአይ ከ25 በላይ የሆኑ ሴቶች በማህፀን መውረድ የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ ነው።
የሆድ እቃ ጫናን የሚፈጥሩ ሁኔታዎች በተለይም ደግሞ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሳል፣ የሚያስምጥ የሆድ ድርቀት ፣ ጫና ያለው የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ (ክብደት ማንሳት) ለማህፀን መውጣት/መውረድ አጋላጭ ሁኔታዎች ናቸው።
ማንኛዋም ሴት የብልት አካባቢ የመክበድና የመውጣት ስሜት የሚሰማት ከሆነ የሕክምና ባለሙያዎችን ማማከር ያስፈልጋታል።
እንደ ማህፀን መውረድ ደረጃው የሚለያይ ሲሆን የፊተኛው ፣ የኋለኛው እንዲሁም የማህፀን ጫፍ በተለያየ ደረጃ ይወጣሉ። በውስጠኛው የብልት ክፍል ብቻ ከመታየት እስከ ሙሉ ለሙሉ ማህፀን መውጣት ምልክት ሊታይ ይችላል።
የሕክምና አማራጮች
ቀለል ያለ ወይም ምልክት የማያሳይ የማህፀን መውረድ ከሆነ የማህፀን ስፖርት (kegel Exercise) በማድረግ በቀላሉ መስተካከል ይችላል።
ሌላው የፕላስቲክ ድጋፎች (Pessaries) አነስተኛ መጠን እና በተለያየዑ ቅርጽ የተሰሩ ድጋፎችን በብልት ውስጥ በማስገባት ማስተካከል ይቻላል። ይህ የሕክምና ዓይነት የቀዶ ህክምና ለማይፈልጉ እና ለዚህ ዓይነት ሕክምና ብቁ ላልሆኑ ሴቶች አንደ አማራጭ ሆኖ ያገለግላል።
ሙሉ ማህፀን ማውጣት ፤ የላላውን ክፍል ማስተካከል/ማጥበቅ ፣ ከዳሌ አጥንት ጋር ማጣበቅ እንዲሁም በደጋፊ መሽ (mesh) ማስተካከል ዋና ዋናዎቹ የቀዶ ሕክምና ዓይነቶች ናቸው።
አልፎ አልፎ የወሲብ ግንኙነት ማድረግ የማይፈልጉና እድሜያቸው የገፍ ሴቶች ላይ የብልት ቀዳዳን ሙሉ በሙሉ የመድፈን ቀዶ ህክምና (vaginal colpocleisis) ሊሠራ ይችላል።
ሔለን ከ15 ዓመታት በፊት በብቸኝነት በጎግል ማሰሻ ላይ ትጠይቅ የነበረው ጥያቄ አሁን በጣም የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል ትላለች።
ሴቶች ችግር ሲገጥማቸው እንዲያውቁ እና እርዳታ እንዲፈልጉ እየረዳቸው ነው።
የእርሷን የጤና ሁኔታም ስትናገር አዝጋሚም ቢሆን ትንሽ ለውጥ አለው ትላለቸ።
"ለእኔ እያዘገመ የሚሄድ መሻሻል ነው። የድህረ ወሊድ (ወዲያውኑ ከእርግዝና በኋላ) የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ፣ አንዳንድ የጥንካሬ ስራዎችን በመሥራት የሚገኝ ረዥም ሂደት የሚወስድ ማገገም ነበር።"
በመጨረሻ እንደገና መሮጥ እንድትጀምር የረዳት ፊዚዮቴራፒ አገኘች። ሔለን ይህ በጣም ትልቅ ወቅት ነበር ብላለች።
አሁን ሔለን ከምታስበው በላይ እየሠራች ሲሆን ለ10ሺህ ኪሎ ሜትር ሩጫ ተመዝግባለች።
"ጥሩ ስሜት ይሰማኛል እና ምልክቶቼን እንዴት መቆጣጠር እንዳለብኝ ተምሬያለሁ። አሁንም ፕሮላፕስ አለብኝ። ነገር ግን ሕይወቴን ቀደም ሲል በነበረው መንገድ አይመራውም፤ ግን ጦርነቱን እንደማሸነፍ ይሰማኛል።"