አብሯቸው ሲጓዝ የነበረ ስደተኛን አስከሬን የያዙ ሁለት ኤርትራውያን በቤላሩስ ድንበር ላይ ተገኙ

በቤላሩስ ድንበር ላይ አብሯቸው ሲጓዝ የነበረ ኤርትራዊ ስደተኛን አስከሬን የያዙ ሁለት ኤርትራውያን ስደተኞች ተገኙ።

የቤላሩስ የድንበር ጠባቂዎች ሁለት ኤርትራውያን ስደተኞች አብሯቸው ሲጓዝ የነበረውን ኤርትራዊ አስከሬን ይዘው እንዳገኟቸው አስታውቀዋል።

ቤላሩስን ከላቲቪያ በሚያዋስነው ሰሜናዊ ግዛት ብራስላቭ የኤርትራዊው አስከሬን መገኘቱን ኤስቢ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

ኤርትራውያን መሆናቸውን በአስተርጓሚ የገለጹ ስደተኞች እንደተናገሩት፤ ላቲቪያ ከገቡ በኋላ የወታደር ልብስ በለበሱ ሰዎች ድብደባ ደርሶባቸዋል።

እነዚህ ግለሰቦች ስልካቸውን እንደወሰዱባቸው፣ በመሣሪያ እንዳስፈራሯቸው እና ቤላሩስ ድንበር ላይ ጥለዋቸው እንደሄዱ ስደተኞቹ ተናግረዋል።

ኤርትራውያኑ ስደተኞች ለቤላሩስ ፖሊስ እንደገለጹት፤ አብሯቸው ይጓዝ የነበረው የ29 ዓመት ኤርትራዊ ስደተኛ በደረሰበት ድብደባ መንገድ ላይ ሳሉ ሕይወቱ አልፏል።

የብራስላቭ ግዛት መርማሪዎች በመንገድ ላይ የነበረው ስደተኛ እንደሞተ እና በአስከሬኑ ላይ ምርመራ እየተደገ መሆኑን ገልጸዋል።

የግዛቱ የምርመራ ኮሚቴ እንዳለው ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ በተከሰተው "የስደተኞች ቀውስ" ምክንያት በቤላሩስ እና በላቲቪያ ድንበር 35 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

ቤላሩስ በምሥራቅ በኩል ከሩሲያ፣ በደቡብ በኩል ከዩክሬን፣ በሰሜን በኩል ከላቲቪያ፣ በምዕራብ በኩል ከፖላንድ እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ በኩል ከሉትዌንያ ጋር ትዋሰናለች።

ከቱርክ የሚነሱ ስደተኞች በቡልጋሪያ፣ በሮማንያ፣ በማልዶቫ እና በዩክሬን በኩል አቋርጠው ወደ ስዊድን እና ኖርዌይ ለመግባት ቤላሩስን እንደ መሸጋገሪያ ይጠቀማሉ።

ስደተኞች በሕጋዊ መንገድ ሩሲያ ከገቡ በኋላ ወደ ቤላሩስ፣ ፖላንድ፣ ጀርመን እና ሌሎችም የአውሮፓ አጋራት ይሻገራሉ።

የሜድትራኒያን ባሕርን አቋርጠው በሊቢያ በረሃ ወደ አውሮፓ የሚጓዙ ስደተኞች ለግድያ፣ ለስቅይት እንዲሁም ለገንዘብ እና ለሥነ ልቦና ብዝበዛ እንደሚጋለጡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ያወጧቸው ተደጋጋሚ ሪፖርቶች ያሳያሉ።

በሊቢያ በረሃ ያለውን እንግልት ለመሸሽ ስደተኞች የምሥራቅ አውሮፓ እና የማዕከላዊ አውሮፓን መንገድ እንደ አማራጭ ይጠቀማሉ።

በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች በሊቢያ በኩል በባሕር እንዲሁም በተጎራባች አገራት በኩል በድንበር በሚያደርጓቸው ጉዞዎች በተደጋጋሚ ለሞት እየተዳረጉ መሆናቸውን የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።