በጂንካ ከተማ የተከሰተውን በሽታ "ሲያክሙ የነበሩ" ሁለት የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ሞቱ

የጂንካ ሆስፒታል በር

የፎቶው ባለመብት, Fikreab Lukas

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጂንካ ከተማ በተከሰተው በውል ያልታወቀ በሽታ ለተያዙ ሰዎች "ሕምክና ሲሰጡ የነበሩ" ሁለት የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ለቢቢሲ ገለጸ። የበሽታውን ምልክታ ባሳዩ ታካሚዎች ላይ "በፍጥነት የኩላሊት ሥራ የማቆም (fail)" ሁኔታ እንደታየም ተገልጿል።

የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጂንካ ከተማ "ምንነቱ በመረጋገጥ ላይ ያለ የሔሞራጂክ ፊቨር" በሽታ መከሰቱን ያስታወቁት ትናንት ረቡዕ ሕዳር 3/2018 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት መግለጫ ነው። በሽታው መከሰቱን ያመለከቱት "የቅኝት መረጃዎች" መሆናቸውን የገለጸው መግለጫው፤ ስምንት ሰዎች "በበሽታው እንደተጠረሩም" ገልጿል።

"በሔሞራጂክ ፊቨር" የተያዘው የመጀመሪያው ሰው ወደ ጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል የመጣው "ከሦስት ሳምንት ገደማ" በፊት እንደነበር የሕክምና ተቋሙ ተወካይ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሰላሙ ታደሰ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የወባ በሽታ እንደሆነ በመጠርጠሩ በሌላ የጤና ተቋም ሕክምና ሲያገኝ እንደነበር የገለጹት ዶ/ር ሰላሙ፤ ወደ ጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል የመጣው ሁኔታው "በጣም ከባድ" ሲሆን መሆኑን አስረድተዋል።

ተወካይ ሜዲካል ዳይሬክተሩ እንደሚናገሩት ታካሚው ወደ ሆስፒታሉ ከመጣ በኋላ ሕመሙ "አስጊ" ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን ቀጥሎም በሆስፒታሉ "አንድ ቀን ገደማ" ከቆየ በኋላ ሕይወቱ አልፏል። ይህ ከተፈጠረ ከአንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ተመሳሳይ ምልክቶችን አሳይተው ለሕክምና መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ላብራቶሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቫይራል ሔሞራጂክ ፊቨር ለተለያዩ የቫይረስ ሕመም ዓይነቶች የተሰጠ የወል ስም ሲሆን በዚህ ስር ካሉ በሽታዎች ውስጥ ቢጫ ወባ፣ የደንጊ ትኩሳት (dengue fever) እና ኢቦላ ተጠቃሽ ናቸው

"ከሳምንት በኋላ፤ ከዚያ ታካሚ ጋር በተለያየ ምክንያት ጉርብትና፣ አንድ ላይ የነበሩ ጓደኞቹ ከእርሱ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ምልክት ማሳየት ጀመሩ" ሲሉ ያጋጠመውን ተናግረዋል። በሌሎች ታካሚዎች ላይ ተመሳሳይ ምልክት መስተዋሉን ተከትሎ ሆስፒታሉ ናሙናዎችን ወደ አዲስ አበባ መላኩን አስረድተዋል።

ዶ/ር ሰላሙ እንደሚገልጹት የዚህን በሽታ ምልክት በማሳየታቸው በሆስፒታሉ ሕክምና የተደረገላቸው "ስምንት ገደማ ሰዎች" ናቸው። ከእነዚህ ታካሚዎች ውስጥ ለበለጠ ሕክምና ወደ ሐዋሳ እና ወላይታ ሶዶ ከተማዎች የተላኩ እንዳሉበት ጠቅሰዋል።

ታካሚዎች ሪፈር የተደረጉበት አንዱ ምክንያት በግለሰቦቹ የታየው "ኩላሊት በፍጥነት የመክሸፍ (ፌል)" የማድረግ ሁኔታ እንደሆነ አስረድተዋል። "የኩላሊት ሁኔታቸው በጣም ቶሎ ነበር ሥራ የማቆም (fail) የማድረግ ደረጃ የደረሰው። አንዳንዶቹ normal range የነበሩት ሰዎች በሁለት በሦስት ቀን ስታይ 4፣ 5 የመሆን፤ ከዚያም ሰባት የመሆን [ነገር ነበር]። ከሚጠበቀው በላይ ኩላሊት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ነበር" ሲሉ በታካሚዎች ላይ የታየውን ሁኔታ አስረድተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከወባ በሽታ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ታካሚዎች ላይ "የትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ሆድ ሕመም፣ ማስመለስ እና ማስቀመጥ" ምልቶች መታየታቸውን ዘርዝረዋል።

ተወካይ ሜዲካል ዳይሬክተሩ እንደሚያስረዱት፤ ወደ የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል የመጡ ታካሚዎች "በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በጣም አስጊ (critical)" ደረጃ ላይ የመድረስ ሁኔታ ታይቶባቸዋል። ከዚህ በሽታ ጋር በተያያዘ ወደ ሆስፒታሉ ከመጡት ስምንት ሰዎች ውስጥ ስድስቱ ሕይወታቸው እንዳለፈ ተናግረዋል።

ከሞቱት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ በበሽታው ለተያዙ ሰዎች ሕክምና ሲሰጡ የነበሩ ዶክተር እና ነርስ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ሌላ ሆስፒታሉ ምንጭም ይህንኑ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የሕክምና ባለሙያዎቹ ለበሽታው የተጋለጡት በታካሚዎች ጋር በነበራቸው ንክኪ "ሊሆን ይችላል" የሚል ግምት እንዳላቸው ዶ/ር ሰላሙ ተናግረዋል።

አብዛኛዎቹ ታማሚዎች ሕይወታቸው ያለፈው ባለፈው ሳምንት በነበሩት ቀናት ውስጥ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በአሁኑ ሰዓት ሁለት ሰዎች በሆስፒታሉ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝም አክለዋል።

የጤና ሚኒስቴር በሽታውን ለመቆጣጠር የተላከው ግብረ ኃይል በዛሬው ዕለት ጂንካ ከተማ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዶ/ር ሰላሙ አስረድተዋል።

ተወካይ ሜዲካል ዳይሩክተሩ እንደሚገልጹት፤ ባለሙያዎቹ ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎችን በመኖሪያ ቤታቸው እና በሆስፒታሉ የመለየት ተግባር ይከናወናል። ምልክቱ ለታየባቸው ሰዎች ማቆያ የሚሆኑ ቦታዎች እየተዘጋጁ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የበሽታው መከሰት ሪፖርት ከተደረገለት በኋላ ለምርመራ፣ ለመከላከል እና ሕሙማንን ለማከም የሚያግዙ ባለሙያዎች እና ቁሳቁሶችን ማቅረቡን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ኢትዮጵያዊው ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እንዳመለከቱት ለአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ የሚውል 300 ሺህ ዶላር የመጠባበቂያ ድጋፍ እንዲሰጥ መፍቀዳቸውን አመልክተዋል።

ቫይራል ሔሞራጂክ ፊቨር ምንድን ነው?

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ቫይራል ሔሞራጂክ ፊቨር (Viral haemorrhagic fever) ለተለያዩ የቫይረስ ሕመም ዓይነቶች የተሰጠ የወል ስም ነው። ቢጫ ወባ፣ የደንጊ ትኩሳት (dengue fever) እና ኢቦላ ተጠቃሽ ናቸው።

ክሪሚያን-ኮንጎ ሔሞረጂክ ፊቨር (Crimean–Congo haemorrhagic fever) እና ሪፍት ቫሊ ፊቨር (Rift Valley fever) የተባሉት በሽታዎችም እዚህ ውስጥ እንደሚካተቱ የዓለም የጤና ድርጅት በድረ ገጹ ያሰፈረው መረጃ ያስረዳል።

ሔሞራጂክ ፊቨር፤ በዋናነት የሰውነትን የደም ዝውውር (vascular system) የሚጎዳ እና ሰውነት ራሱን የሚቆጣጠርበትን አቅም የሚያሳጣ ነው። ሕይወትን እስከመቅጠፍ የሚደርስ ሕመም እንደሆነም ተገልጿል።

የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትናንት ባወጡት መግለጫ፤ በጂንካ ከተማ የተከሰተው ሔሞረጂክ ፊቨር "ምንነቱ በመረጋገጥ" ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ተወካይ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሰላሙም በተመሳሳይ በጂንካ የተከሰተው የትኛው የበሽታው ዓይነት እንደሆነ የሚታወቀው በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላብራቶሪ ምርመራ ከተደረገ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል።

"[ምርመራው] እየተሠራ ነው፤ የትኛው እንደሆነ ይፋ ይደረጋል። እኛም በትዕግስት እየጠበቅን ነው" ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር እና ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም "የላብራቶሪ ምርመራዎች" እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል። በተጨማሪም፤ "የበሽታውን መንስኤ ለማወቅ እና ተጨማሪ ስርጭትን ለመግታት እንዲሁም ለመቆጣጠር ፈጣን ምላሽ ሰጩ ቡድን ወደቦታው በመላክ" የመስክ ግምገማ እንደሚያደረግ ገልጸዋል።

የፌደራል መንግሥት ተቋማቱ የተላከው ግብረ ኃይል በዛሬው ዕለት ጂንካ ከተማ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዶ/ር ሰላሙ አስረድተዋል።

ወባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቫይራል ሔሞራጂክ ፊቨር ስር ከሚካተቱ በሽታዎች አንዱ የሆነው የደንጊ ትኩሳት (dengue fever) በወባ አማካኝነት የሚተላለፍ ነው

የሕመሙ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ሁለቱ የፌደራል መሥሪያ ቤቶች ባወጡት መግለጫ ላይ የሕመሙ ምልክቶች እንደሆኑ ከዘረዘሯቸው ውስጥ "በአፍ፣ አፍንጫ እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች መድማት" የሚለው ይገኝበታል። "ትኩሳት፣ ማስቀመጥ እና ማስመለስም" በምልክትነት ተጠቅሰዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ድንገተኛ የጡንቻ ሕመም፣ ራስ ምታት እንዲሁም እና ከደም መፍሰስ ጋር የተያያዘ ሾክን በተጨማሪ ምልክትነት አስፍሯል። ሕመሙ የሰውነት ክፍሎችን መደበኛ ሥራ የሚያስተጓጉል (organ failure የሚያስከትል) እንደሆነም የተቋሙ መረጃ ያሳያል።

የሕመሙ የመጀመሪያ ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ የጡንቻ ሕመም እና ምቾት አለመሰማት ናቸው። ሕመሙ እየተባባሰ ሲሄድ የሆድ ሕመም፣ ማስመለስ፣ ማስቀመጥ፣ የቆዳ መቆጣት እንዲሁም ፊት እና ደረት ላይ የሚሰማ ሙቀት ያስተዋላል።

ሕመሙ በተባባሰባቸው ሰዎች ላይ ከመጠን ያለፈ ደም መፍሰስ (haemorrhaging) ይከሰታል። ከአፍ እና ከአፍንጫ እንዲሁም ከሌሎች የሰውነት ክፍሎችም ደም ይፈሳል።

የሕመሙ የመጀመሪያ ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ የጡንቻ ሕመም እና ምቾት አለመሰማት ናቸው።

ሕመሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከፍተኛ ደም መፍሰስ እና ሞት ያስከትላል።

እንዴት ይተላለፋል?

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፤ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ቀጥተኛ የአካል ንክኪ ወይም በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ሰውነት የሚወጣ ፈሳሽ ወይም ደም መንካት ሕመሙ እንዲተላለፍ ያደርጋል።

ክሪሚያን-ኮንጎ ሔሞረጂክ ፊቨር እና ሪፍት ቫሊ ፊቨር በተባሉት የሕመሙ ዓይነቶች በበሽታው የተያዙ እንሰሳትን ጥሬ ሥጋ እና ወተት መመገብ ለበሽታው እንደሚያጋልጥ ተጠቅሷል።

እንደ ሪፍት ቫሊ ፊቨር እና ደንጌ ፊቨር ባሉት የሕመሙ ዓይነቶች ደግሞ የወባ ትንኝ ንክሻ በሽታውን እንደሚያስተላልፍ ተገልጿል።

'rodents' የተባሉት የአይጥ ዝርያዎችም በሽታውን እንደሚያስተላልፉ ተጠቅሷል።

ሕመሙን እንዴት መከላከል ይቻላል?

ትናንት ማምሻውን የወጣው መግለጫ፤ "ምልክት ከታየበት ሰው ጋር ንክኪ በሚኖርበት ጊዜ ራስን የመከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም" እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። "ሁልጊዜ እጅን በሳኒታይዘር ወይም በውሃ እና ሳሙና በመታጠብ ማጽዳት" እንደሚያሻም ተገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት 'viral haemorrhagic fevers' ወይም በምጽሐረ ቃሉ 'VHFs' በሚል አጠቃላይ መጠሪያ የጠቀሰውን ሕመም "በመላው ዓለም እየተባባሰ የመጣ ስጋት ነው" ሲል ይገልጸዋል።

አጠቃላይ የሕመሙን ዓይነቶች ለማከም የሚውል መድኃኒት እንደሌለ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።

ሆኖም ግን የቢጫ ወባ እና ኢቦላ ክትባቶች የሕመሙን ዝርያዎች ለመከላከል እንደሚረዱ ተገልጿል። በሕመሙ የተያዙ ሰዎች ትኩሳታቸው እንዲቀንስ በማድረግ፣ የመተንፈሻ አካላቸው በአግባቡ እንዲሠራ ኦክስጅን በመስጠት እና በሌሎችም መንገዶች የሕክምና እርዳታ ይሰጣቸዋል።