"አሁንም ጸጸት አለቀቀኝም" - ነፍሰ ጡር እናት ጭኖ ጭቃ ውስጥ የገባውን አምቡላንስ ለማውጣት የታገለው ሹፌር

ሀብታሙ ጭቃ ውስጥ ቁጭ ብሎ እና ጭቃ ውስጥ የገባውን አምቡላንስ የሚያሳዩ ፎቶዎች

የፎቶው ባለመብት, Habtamu Dergu

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ምጥ ላይ የነበረች እናትን ጤና ጣቢያ ለማድረስ ዋጋ የከፈለው አምቡላንስ ሹፌር በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች መነጋገሪያ ሆኗል።

ሀብታሙ ደርጉ የተባለው ወጣት በጎፋ ዞን መሎ ጋዳ ወረዳ ለሁለት ዓመታት የአምቡላንስ ሹፌር ሆኖ ሠርቷል።

ባለፉት ዓመታት በሥራው ላይ ካጋጠሙት ክስተቶች እጅጉን አሳዛኙ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ጥቅምት 1/2018 ዓ.ም. ያጋጠመው እንደሆነ ይናገራል። "አሁንም ድረስ ሳስታውሰው አለቅሳለሁ" ይላል።

ሀብታሙ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ ወደ የጤና ተቋም መወሰድ ያለባትን ምጥ ላይ ያለች እናት በተቻለ ፍጥነት እንዲያደርስ የተነገረው ስምንት ሰዓት አካባቢ ነበር።

ምጥ ላይ ወዳለችው ሴት ቤት ለመድረስ በአስቸጋሪው የመሎ ጋዳ የገጠር መንገድ 81 ኪሎሜትር ተጉዟል።

ወደ መኖሪያ ቤቱ የደረሰው አመሻሽ ላይ ነበር። ምጥ ላይ ያለችውን እናት፣ ባለቤቷን እና የጤና ባለሙያዎችን ጭኖ ወደ ጤና ተቋሙ ጉዞውን ጀመረ።

ጥቂት እንደተጓዙ ግን አምቡላንሱ በጭካ መያዙን ሀብታሙ ይናገራል።

"ትንሽ እንደተጓዝኩ አምቡላንሱ ጭቃ ውስጥ ተቀረቀረ። አእምሮዬ ውስጥ ምጥ ላይ ያለቸው እናት አለች። ከመኪናው ወርጄ ከሥር ያለውን ጭቃ እየዛቅኩ ማውጣት ጀመርኩ" ይላል።

አምቡላንሱን ከጭቃ ለማውጣት የተደረገው ጥረት ግን የሚፈለገውን ውጤት አላስገኘም። ሌሊት ስለነበር አምቡላንሱ ውስጥ ከተሳፈሩት ሰዎች ውጪ ሊያግዝ የሚችል ሰው ማግኘት አልተቻለም።

"ሌላ ሰው ካለ ብዬ የአምቡላንሱን ሳይረን ሳስጮህ ነበር። አካባቢው ጫካ ስለሆነ ማንም በአቅራቢያ አልነበረም" በማለት ያደረገውን ጥረት ይናገራል።

መኪናውን ከጭቃ አውጥቶ ምጥ ላይ ያለችውን እናት ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ በሌሊቱ ጨለማ ውስጥ ለሰዓታት ለፍቷል። ሁኔታው ግን ተስፋ አስቆርጦት ነበር።

"ጭቃው ውስጥ እንዳለን ምጥ ላይ ያለችው እናት አምቡላንሱ ውስጥ ወለደች። ነርሷ ረድታት፤ እዟው ተገላገለች" ይላል።

በሚያሳዝን ሁኔታ ግን የተወለደው ጨቅላ በሕይወት አልነበረም። ሌሊት ስምንት ሰዓት አካበቢ ይህ ሲፈጠር ሀብታሙ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገብቶ ነበር።

አምቡላንሱን ከጭቃ መውጣት አለመቻሉ እና የተወለደው ልጅ ሞት የተደራረቡበት ሀብታሙ፤ መኪናው ፊት ለፊት ጭቃ ውስጥ ቁጭ ብሎ አለቀሰ።

ሀብታሙ ጭቃ ውስጥ ቁጭ ብሎ

የፎቶው ባለመብት, Habtamu Dergu

"በማንኛውም መንገድ ወደ ሆስፒታል ለማድረስ እያሰብኩ ነበር። ግን አልቻልኩም። ሕጻኑ ሲሞት ስሜቴን መቆጣጠር አልቻልኩም፤ አለቀስኩ" ሲል የተሰማውን ያስታውሳል።

በዚህ መልኩ ሌሊቱን ጭቃ ውስጥ ካሳለፉ በኋላ ንጋት ላይ ለአለቃው ደውሎ የተፈጠረውን ሪፖርት አደረገ። ጠዋት ላይ ሌላ አምቡላንስ መጥቶ ወላዷ እናት ወደ ሳውላ ሆስፒታል መወሰዷን ተናግሯል።

ይህ ክስተት ከተፈጠረ ከሳምንት በኋላ እንኳን አሁንም ሲያስታውሰው እንባው እንደሚመጣ ይናገራል። ይህ ሁሉ የተፈጠረው በአካበቢው ባለው የመንገድ ችግር ምክንያት መሆኑን ይገልጻል።

"መንገዱ የተሠራው ከዓመታት በፊት ነው። መንገድ ነው ለማለት እንኳን ያስቸግራል። በጣም ከባድ ነው። መንገዱ ጥሩ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ዓይነቱ ነገር አይፈጠርም ነበር" ይላል ጸጸት በሞላው ድምፀት።

በአካባቢው የነበረ አንድ ሞተረኛ፤ ሌሊቱን ሙሉ አምቡላንሱን ከገባበት ጭቃ ለማውጣት ሲጥር የነበረው ሀብታሙን ፎቶ አንስቶታል።

አምቡላንሱ ፊት ለፊት ቁጭ ብሎ ሲያለቅስ የሚያሳየው ፎቶ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ከተለቀቀ በኋላ ምጥ ላይ ያለችውን እናት ሕይወት ለማትረፍ ያደረገው ጥረት አድናቆትን አስችሮታል።

ሀብታሙ ግን አሁንም ቢሆን በአምቡላንሱ ጭቃ ውስጥ መግባት ምክንያት የተፈጠረው የጨቅላ ሕጻን ሞት እና የወላዷ እናት ስቃይ ካስከተለበት ጸጸት አልተላቀቀም።