ተቃውሞ የቀረበበት ድንጋጌ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ እንዲወጣ ተደረገ

አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለ'ፖለቲካል አድቮከሲ' እና ከምርጫ ጋር የተያያዙ ስራዎችን ለመስራት ከውጭ የፋይናንስ ምንጭ ገንዘብ እንዳይቀበሉ የሚከለክለው ድንጋጌ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ማሻሻያ እንዲወጣ ተደረገ።
ቢቢሲ የተመለከተው የማሻሻያው 'የመጨረሻ ረቂቅ' አገር በቀል ድርጅቶች ማንኛውም ከምርጫ ጋር የተያያዘ ስራ ላይ ለመሰማራት "ቅድሚያ [ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች] ባለስልጣን የድጋፍ ደብዳቤ ማግኘት" እንዳለባቸው ያትታል።
ማሻሻያ እየተደረገበት የሚገኘው በስራ ላይ ያለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ የጸደቀው ከስድስት ዓመት በፊት ነበር።
አዋጁ ከ16 ዓመት በፊት ወጥቶ የነበረውን እና 'አፋኝ ነው' በሚል የሚተቸውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ሙሉ በሙሉ የሻረ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ሲወጡ እንደነበረው ተስፋ ሁሉ ከስድስት ዓመት በፊት የወጣው አዋጅም ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል ግምት ነበር።
ከስድስት ወራት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን 'የመስክ ምልከታ' አድርጎ ነበር።
በዚህ 'የመስክ ምልከታ' ባለስልጣኑ "አላሰራ ያሉ አዋጆችን" እንዲያሻሽል "አቅጣጫ" አስቀምጧል።
በወቅቱ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ "[ባለስልጣን] መስሪያ ቤቱ የሚሰራቸው ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዳይሆኑ የሚያደርግ የሕግ ክፍተት" መኖሩን ጠቁመው ነበር።
ከዚህ 'የመስክ ምልከታ' በኋላ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ውይይት ተደርጎበታል።
ሂዩማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የመብት ተሟጋቾች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጁ ላይ በተካተቱ በርካታ ድንጋጌዎች ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ነበር።
የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሽያ ባደር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ "እነዚህን ማሻሻያዎች መቀበል ለአገሪቱ ሲቪል ማኅበረሰብ እና የሲቪክ ምሕዳር ጉዳት ነው" ብለዋል።
ከእነዚህ ድንጋጌዎች መካከል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን 'የሥራ ነጻነት' የሚመለከተው አንቀጽ አንደኛው ነው።
ቀደም ብሎ ለውይይት ቀርቦ በነበረው ረቂቅ ማሻሻያ ላይ አገር በቀል ድርጅት የ'ፖለቲካ አድቮከሲ'፣ የመራጮች ትምህርት፣ በምርጫ መታዘብ ወይም ከምርጫ ጋር የተያያዙ ስራዎችን ለማከናወን ከውጭ የፋይናንስ ምንጭ ገንዘብ እንዳይቀበሉ ይከለክል ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ድርጅቶች "በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ" ለአገር በቀል ድርጅቶች " የፋይናንስ ወይም የቴክኒካል ድጋፎችን በመስጠት" እነዚሁኑ ስራዎች መስራት አይችሉም።
ይህ ድንጋጌ ከ'መጨረሻው' የማሻሻያ ረቂቅ እንዲወጣ ተደርጓል።
"የሥራ ነጻነት'ን በሚመለከተው አንቀጽ ስር ሌላ የውጭ ድርጅቶችን የሚመለከተው አዲሱ ንዑስ አንቀጽ ተካትቷል።
ይህ ንዑስ አንቀጽ ማንኛውም የውጭ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ፕሮጀክት ቀርጾ ለሚተገብረው ስራ "ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር የፕሮጀክት ስምምነት መፈራረም አለበት" ሲል አስገዳጅ ድንጋጌ ያስቀምጣል።
በሌላ በኩል አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከመንግሥት አካላት ጋር ስምምነት የመፈራረም አማራጭ እንዳላቸው ያትታል።
ከምርጫ ጋር በተያያዘ ለሚኖራቸው ስራ የፋይናንስ ምንጭን የተመለከተ ምንም ዓይነት ከልካይ ወይም አስገዳጅ ድንጋጌ በረቂቅ ማሻሻያው ላይ አልተቀመጠም።
ሆኖም ግን አገር በቀል ድርጅቶች "በመራጮች ትምህርት፣ በምርጫ መታዘብ ወይም ማንኛውም ከምርጫ ጋር የተያያዘ ሥራ ላይ ለመሰማራት ቅድሚያ ከባለስልጣኑ የድጋፍ ደብዳቤ ማግኘት አለባቸው" የሚል አዲስ አስገዳጅ ድንጋጌ ተካቶበታል።
ከዚህ በተጨማሪም 'የአገር ደህንነትን" ምክንያት በማድረግ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት የምዝገባ ጥያቄን ስላለመቀበል በቀዳሚው ማሻሻያ ላይ ቀርቦ የነበረው ድንጋጌ ወጥቷል።
ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሚቀርብ ሪፖርት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ማሻሻያ ድንጋጌዎችም 'መጨረሻው' ረቂቅ ለውጥ ተደርጎበታል።
በቀዳሚው ረቂቅ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማንኛውም ንብረት ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ወይም ለመንግሥት አካላት በስጦታ ከማስተላለፋቸው 15 ቀናት በፊት ቀድሞ ለባለሥልጣኑ በጽሑፍ ማሳወቅ ነበረባቸው። 15 ቀናት የነበረው የጊዜ ማዕቀፍ ስጦታውን ካስተላለፉ በኋላ "በዓመታዊ ሪፖርቱ ውስጥ አካቶ ለባለስልጣኑ ማቅረብ አለበት" በሚል ተለውጧል።
አገር በቀል የሲቪክ ማኅበራት ከውጭ አገር እና በአገር ውስጥ ከሚገኝ የውጭ አካል የፋይናንስ ድጋፍ ሲያገኝ "በ15 ቀናት ውስጥ የገንዘቡን ምንጭ፣ መጠን፣ ዓላማ እና ሌሎች መረጃዎችን" ለባለስልጣኑ እንዲያሳውቅ የሚያስገድድ ድንጋጌ ተካትቶበት ነበር።
በአሁኑ ረቂቅ ግን ይህ ድንጋጌ "ድጋፉን ያገኘበትን ጊዜ፣ የገንዘቡን ምንጭ፣ መጠን፣ ዓላማ እና ሌሎች መረጃዎችን ከደጋፊ ማስረጃ ጋር አያይዞ ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ለብቻው አካትቶ ለባለስልጣኑ ማቅረብ አለበት" በሚል ተተክቷል።
በሌላ በኩል በምርመራ ወቅት የሚደረግ ዕግድ ላይ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለፍርድ ቤት ይግባኝ እንዳያቀርቡ የሚከለክለው ድንጋጌ ለውጥ አልተደረገበትም።
ባለስልጣኑ የምርመራ ስራውን ሲያከናውን ከባድ የሕግ ጥሰት ስለመፈጸማቸው አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥም" እንዲሁም "ድርጅቱ ካልታገደ የማይመለስ ጉዳት ይደርሳል ብሎ ካመነ" ዋና ዳይሬክተሩ ድርጅቱን እስከ ሦስት ወር እንዲታገድ ትዕዛዝ ሊሰጡ ይችላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ማሻሻያ ረቂቁ የምርመራ ሥራው በሦስት ወር የዕግድ ጊዜ ካልተጠናቀቀ ዕግዱን ለተጨማሪ ሦስት ወራት የማራዘም ስልጣን ለቦርዱ ይሰጣል።
ባለሥልጣኑ ለምርመራው "አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው" የድርጅቶችን የባንክ ሂሳብ "በከፊል ወይም በሙሉ" የማገድ ሥልጣን አለው።
በዕግዱ ላይ ቅሬታ ያለው ድርጅት የዕግድ ውሳኔው ከተሰጠ ጊዜ ጀምሮ በሰላሳ ቀናት ውስጥ ለቦርዱ ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል የሚያስረዳው ረቂቁ "ቦርዱ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል" ይላል።
በሥራ ላይ ባለው አዋጅ በዕግዱ ቅር የተሰኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቅሬታቸውን ለቦርዱ፤ በቦርዱ ካልተፈታ ደግሞ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት ነበራቸው።















