ትራምፕ ስደተኞችን ከአገር ለማስወጣት በጦርነት ጊዜ የሚተገበረውን ሕግ እንዲጠቀሙ ፍርድ ቤት ፈቀደ

የድርጅት ዓርማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የወንበዴ ቡድን አባላት ናቸው ያሏቸውን ስደተኞች በፍጥነት ከአገር ለማባረር፣ እምብዛም ጥቅም ላይ የማይውለውን የጦርነት ጊዜ ሕግ እንዲጠቀሙ ፈቀደ።

ከዚህ በፊት የስር ፍርድ ቤት የቬንዙዌላውያን ወንበዴ ቡድን አባላት ወደ ኤል ሳልቫዶር እንዳይባረሩ በ1798 የወጣው የውጪ ጠላቶች ሕግ ተጨማሪ ምርመራ ያስፈልገዋል በማለት ለጊዜው አግዶት ነበር።

ትራምፕ ስደተኞቹ የወንበዴ ቡድን አባላት ናቸው ሲሉ የሚከስሱ ሲሆን፣ በአሜሪካ ላይ "መደበኛ ያልሆነ ጦርነት ሲያደርጉ" የቆዩ በመሆናቸው በሕጉ መሰረት ሊባረሩ ይገባቸዋል ሲሉ ተከራክረዋል።

አስተዳደሩ ውሳኔውን እንደ ድል ቢቆጥረውም ዳኞች ግን ከአገር እንዲወጡ የተወሰነባቸው ሰዎች የመቃወም እድል እንዲሰጣቸው ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

ፍርድ ቤቱ ሰኞ ዕለት "ትዕዛዙ በተገቢው ጊዜ ውስጥ መሰጠት አለበት እንዲሁም ከአገር እንዲወጡ ከመደረጉ በፊት በትክክል ነጻ ሆነው ጉዳያቸውን የሚያስረዱበት መንገድ መመቻቸት ይኖርበታል" ሲል በጽሑፍ ትዕዛዝ አስተላልፏል ።

በዚሁ ደብዳቤ ላይ "ጥያቄው የትኛው ፍርድ ቤት ነው ይህንን ጉዳይ ሊመለከተው የሚችለው ብቻ ነው" ሲሉ አስፍረዋል።

የሰኞው ብይን በአምስት ስደተኞች ስም በአሜሪካ የሲቪል ነፃነቶች ኅብረት (ACLU) ለችሎቱ መቅረቡን ገልጾ ጉዳዩ የታየው ስደተኞቹ በታሰሩበት ቴክሳስ ሳይሆን፣ ተገቢ ባልሆነ መንገድ በዋሽንግተን ዲሲ ፍርድ ቤት መሆኑን ገልጿል።

ትራምፕ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ "በአሜሪካ ለፍትህ ታላቅ ቀን" ሲሉ አሞካሽተውታል።

"ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፕሬዝዳንቱ . . . ድንበሮቻችንን እንዲያስከብር፣ አገራችን ራሷን እንድትጠብቅ በመፍቀድ የሕግ የበላይነትን አስከብሯል" ሲሉ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

ለስደተኞች መብት የሚሟገተው ድርጅት በበኩሉ ብይኑንም "ትልቅ ድል" ሲል ጠርቶታል።

የድርጅቱ ዋና ጠበቃ የሆኑት ሊ ጌለርት ለአሜሪካ ሚዲያ በሰጡት መግለጫ "የፍርድ ቤቱን ሂደት እንደገና በሌላ ቦታ ማስጀመር በማስፈለጉ በጣም አዝነናል፤ ነገር ግን ወሳኙ ነጥብ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግለሰቦች በዚህ ሕግ መሰረት ከመባረራቸው በፊት ለመቃወም ተገቢው እድል መሰጠት አለበት ማለቱ ነው" ብለዋል

በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ቢያንስ 137 ስደተኞች በዚህ ሕግ መሰረት ከአገር እንዲባረሩ ተደርገዋል።

ውሳኔው በመብት ተሟጋች ቡድኖች ውግዘት ገጥሞታል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለመጨረሻ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው ይህ ሕግ፣ ለአሜረካ ፕሬዝደንት የተለመዱ ሂደቶችን ሳይከተል የ"ጠላት" አገር ተወላጆች ወይም ዜጎች እንዲታሰሩ እና እንዲባረሩ የማዘዝ ከፍተኛ ስልጣንን ይሰጣል።

ይህ ሕግ የወጣው በ1798 አሜሪካ ከፈረንሳይ ጋር ጦርነት ውስጥ ልትገባ ትችላለች ተብሎ በተሰጋበት ወቅት ከሌሎች ሕጎች ጋር በመሆን ነው።