ዩኬ ያቀደችው የውጭ እርዳታ ቅነሳ አፍሪካን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዳት ተገለጸ

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ያቀደው የውጭ እርዳታ ቅነሳ በአፍሪካ ለህጻናት ትምህርት እና ለሴቶችን ጤና የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንሰው ተገለጸ።

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት ከአሜሪካ በመጣ ግፊት የመከላከያ ወጪውን 2.5 በመቶ ለማሳደግ በሚል የውጭ እርዳታውን 40 በመቶ እንደሚቀንስ የካቲት ወር ላይ አስታውቆ ነበር።

ይህም ከአገሪቱ አጠቃላይ የብሔራዊ ገቢ አንጻር ሲሰላ ከ0.5 በመቶ ወደ 0.3 በመቶ ዝቅ የሚያደርገው ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሪፖርት እና የተጽዕኖ ግምገማ እንደሚያሳየው አገሪቱ በተያዘው ዓመት በምታደርገው የውጭ እርዳታ ቅነሳ ከፍተኛው የአፍሪካ ነው።

ይህም በሴቶች ጤና፣ ውበሃ እና ንጽህና ላይ የሚደረገውን ድጋፍ በመቁረጥ ለበሽታዎች መጋለጥ እና ሞትን ሊያስከትል እንደሚችልም ሪፖርቱ አካቷል።

በማኅበረሰቡ ውስጥ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች እና ህጻናት በዚህ የእርዳታ ቅነሳ ከፍተኛውን ዋጋ እንደሚከፍሉ ቦንድ የተሰኘው የዩናይትድ ኪንግደም የእርዳታ ድርጅቶች ኔትወርክ አሳስቧል።

ቦንድ ፤ የዩኬ መንግሥት ለትምህርት፣ ለሥርዓተ ፆታ እንዲሁም በሰብዓዊ ቀውስ እየተፈተኑ ላሉ ለኢትዮጵያ፣ ለደቡብ ሱዳን እና ለሶማሊያ እንዲሁም በሚያስደንቅ ሁኔታ በእስራኤል በኃይል በተያዙ ለፍልስጤም ግዛቶች በገንዘብ ድጋፍ ቅድሚያ ከመስጠት አፈግፍጓል ብሏል።

ኔትወርኩ አክሎም መንግሥት እነዚህ ፕሮግራሞች እና አገራት ጥበቃ እንደሚደረግላቸው መናገሩን አስታውሷል።

"ለአፍሪካ፤ ለሥርዓተ ፆታ፣ ለትምህርት እና ለጤና ፕሮግራሞች የሚደረገው የሁለትዮሽ የገንዘብ ድጋፍ መቀነሱ አሳሳቢ ነው" ሲሉ የቦንድ ፖሊሲ ዳይሬክተር ጊዲዮን ራቢኖዊትዝ ተናግረዋል።

"በዓለማችን ላይ በጣም ተጋላጭ የሆኑ ማኅበረሰቦች በተለይም በጦርነቶች ውስጥ ያሉ ሴቶች እና ታዳጊዎች ለእነዚህ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ከፍተኛውን ዋጋ የሚከፍሉ ይሆናል" ብለዋል።

አክለውም "አሜሪካ ሁሉንም የሥርዓተ ፆታ ድጋፎችን ባጠፈችበት በዚህ ወቅት ዩናይትድ ኪንግደም ወደ ኋላ መመለስ ሳይሆን ያንን ክፍተት ልትሞላ ይገባ ነበር" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለህጻናት ትምህርት የሚደረገውን ድጋፍ ጨምሮ የአፍሪካን ዕርዳታ በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ የተያዘው ይህ ዕቅድ እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች ላይ 21 በመቶ የሚቀንስ ይሆናል።

ነገር ግን መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለክትባቶች የሚደረገው የጋቪ ክትባት ጥምረት እንደ የዓለም ባንክ ላሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ እንደማይነካ አስታውቋል።

በተጨማሪም የሰብዓዊ ቀውስ ባለባቸው እንደ ጋዛ፣ ዩክሬን እና ሱዳን ውስጥ የሚያደርገውን እገዛ ይቀጥላል ተብሏል።

"እያንዳንዷ የምናወጣት ፓውንድ ለዩናይትድ ኪንግደም ግብር ከፋዮች እንዲሁም በመላው ዓለም ለምንረዳቸውን ሰዎች ምን ያህል እየሠራ እንደሆነ ማሳየት አለብን። አሁን ያወጣነው አሃዝ ቅድሚያ የምንሰጣቸውን እና ትኩረት የምናደርግባቸውን ሥራዎችን መጀመራችን ማሳያ ነው" ሲሉ የዩኬ የልማት ሚኒስትር ባሮንስ ቻፕማን ገልጸዋል።

መንግሥት ያደረገው የእርዳታ ቅነሳ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የታገዘ "የዕርዳታ ስትራቴጂካዊ ግምገማን" ተከትሎ ነው ብሏል።

በዚህም መሠረት "ቅድሚያ መስጠት፣ ቅልጥፍና፣ የታቀዱ ሰብዓዊ ድጋፎች እና ያሉ ውሎችን መጠበቅ እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ኃላፊነትን በጠበቀ መልኩ ፕሮጀክቶችን ማቋረጥ" የሚል መመሪያን ተከትሎ ቅነሳው ተግባራዊ መደረጉ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አክሎ እንደገለጸው በሁለትዮሽ የትብብር ድጋፍ በቀጥታ የሚደረጉ ዕርዳታዎች ለአንዳንድ አገራት እንደሚቀንስ እና ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳዩ ድርጅቶችም እንዲሁ የሚደረግላቸው ድጋፍ እንደሚቀንስ አስታውቋል።

በዚህ የሁለትዮሽ የትብብር ድጋፍ የትኞቹ አገራት ዕርዳታቸው ሊቀንስ እንደሚችል አልተገለጸም።

ዩናይትድ ኪንግደም ለውጭ አገራት የምታደርገው የገንዘብ ድጋፍ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ መወዛገቢያ የሆነ ሲሆን፣ አንድ ሚኒስትርም ሕዝቡ ከአሁን በኋላ ወጪውን እንደማይደግፍ አምነዋል።