ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ እርዳታ ስረዛ ምክንያት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የ14 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ እንደሚችል ተጠቆመ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለውጭ ሰብዓዊ እርዳታ ትሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ መሰረዛቸው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተጨማሪ 14 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ሊያደርግ እንደሚችል ዘ ላንሴት የተባለው ተቋም የሕክምና ሪፖርት ጠቆመ።
ካለ እድሜያቸው ሕይወታቸው ከሚያልፉት ውስጥ ሲሶ ያህል ሕፃናት መሆናቸውን የጥናቱ ግኝት አሳይቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው መጋቢት የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር በአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የሚሰጡ 80 በመቶ መርሐ ግብሮችን መሰረዙን ተናግረዋል።
ከጥናቱ ፀሐፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዴቪድ ራሰላ "ለበርካታ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው አገራት ውጤቱ ከዓለም አቀፍ ወረርሽኝ አሊያም ከግዙፍ ግጭት ጋር የሚነፃፀር ነው" ብለዋል።
የረድኤት ድጋፉ "ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተጋላጭ ሕዝቦች ጤና ላይ የታየው እድገት በአፋጣኝ እንዲገታ ወይም ወደነበረበት እንዲመለስ አደጋ ደቅኗል" ሲሉ በባርሴሎና ዓለም አቀፍ ጤና ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዴቪድ ራሰላ አክለው ተናግረዋል።
ሪፖርቱ የወጣው የዓለም መሪዎች በስፔን ሰቪል ከተማ በዚህ ሳምንት በመንግሥታቱ ድርጅት የተመራ እና ከአስር ዓመታት በኋላ ግዝፉ የሆነው ጉባኤ ከመካሄዱ አስቀድሞ ነው።
ከ133 አገራት የተገኘ መረጃን የተመለከተው የተመራማሪዎች ቡድን በግመታው እ.አ.አ ከ2001 እስከ 2021 ድረስ በማደግ ላይ ባሉ አገራት የዩኤስኤአይዲ ድጋፍ 91 ሚሊዮን ሰዎችን ከሞት የታደገ ነው።
ተመራማሪዎች ከወራት በፊት በአሜሪካ መንግሥት ይፋ የተደረገው 83 በመቶ ድጋፍ መቀነስ የሞት ምጣኔን ከፍ እንደሚያደርግም ግመታቸውን አስቀምጠዋል።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የእርዳታ መሰረዙ ሕይወታቸውን መታደግ እየተቻለ 14 ሚሊዮን ሰዎችን ወደ ሞት ይመራል ብለዋል።
ይህ አኃዝ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 4.5 ሚሊዮን ሕፃናትን ጨምሮ ሲሆን ይህም ማለት 700 ሺህ ሕፃናት በየዓመቱ ሕይወታቸው ያልፋል ማለት ነው።
ከዚህ ቀደም በቢሊየነሩ ኢለን መስክ ይመራ የነበረው የትራምፕ አስተዳደር ወጪ ቅነሳ መስሪያ ቤት የፌደራል ሰራተኞችንም የመቀነስ ዓላማ የሰነቀ ነው።
መስሪያ ቤቱ ዩኤስኤአይዲ ለዘብተኛ መርሐ ግብሮችን ደግፏል በሚል ወቀሳም አቅርቧል።
የዓለም ከፍተኛ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢ የሆነችው አሜሪካ ከ60 በላይ በሚሆኑ አገራት በአመዛኙ በወኪሎች በኩል እርዳታ ሰጥታለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ በእርሳቸው መስሪያ ቤት ስር "የበለጠ ውጤታማ" ሆነው የሚተዳደሩ አንድ ሺህ የሚሆኑ መርሐ ግብሮች እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ሰራተኞች መሬት ላይ ያለው እውነታ እንዳልተሻሻለ ይናገራሉ።
ባለፈው ሳምንት አንድ የመንግሥታቱ ድርጅት ኃላፊ የአሜሪካ እርዳታ መሰረዙን ተከትሎ በኬንያ የስደተኞች ጣቢያ የምግብ ክፍፍል (ራሽን) በመቀነሱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች "እየተራቡ" ነው ብለዋል።
በኬንያ ሰሜን ምዕራብ በሚገኘው ካኩማ ሆስፒታል ቢቢሲ በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጎዳች እና ቆዳዋ የተሸበሸበ ሕፃን ተመልክቷል።