ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዕውቅና ያላገኘው እና የተከፋፈለው ህወሓት ደብረጽዮንን ሊቀ መንበሩ አድርጎ መረጠ
አመራሩ ለሁለት የተከፈለበት ህወሓት በምርጫ ቦርድ ዕውቅናን ሳያገኝ ለቀናት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤልን (ዶ/ር) በሊቀመንበርነት እንዲቀጥሉ መምረጡን አስታወቀ።
ሕጋዊውን ሂደት የተከተለ አይደለም በሚል ከ14ኛው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ እራሳቸውን ያገለሉት የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እንዲሁም በርካታ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በሌሎች ተተክተዋል።
በዚህም መሠረት የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በአቶ አማኑኤል አሰፋ የተተኩ ሲሆን፣ የጉባኤውን ሂደት በመቃወም ተሳታፊ ያልሆኑት ሌሎችም የፓርቲው አመራሮች ከማዕከላዊ ኮሚቴው ኃላፊነት ውጪ መደረጋቸው ተገልጿል።
የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር መሆናቸው የተነገረላቸው አቶ አማኑኤል አሰፋ የትግራይ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፣ ኋላ ላይም የፓርቲው ቃል አቀባይ ሆነዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ምርጫ ቦርድ ህወሓትን በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን ያሳወቀበትን ውሳኔ በመቃወም የቀደመ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ብቻ እንደሚፈልጉ የገለጹት ሊቀ መንበሩ የፓርቲውን ጉባኤ ሲያካሄዱ ነበር የሰነበቱት።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ከማካሄዱ ከ21 ቀናት በፊት ማሳወቅ እና የቦርዱ ታዛቢመገኘት እንዳለበት በመግለጽ ከዚህ ውጪ የሚካሄድ ጉባኤ እና ውሳኔው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለህወሓት በጻፈው ደብዳቤ ገልጾ ነበር።
ይህንን የቦርዱን ማሳሰቢያ ያልተከተለው የህወሓት ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበሩን አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ከከፍተኛ አመራሮቹ ተቃውሞ ቢገጥመውም ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰባት ቀናት ሲያካሂድ ቆይቷል።
ህወሓት ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ እንዳሳወቀው በጉባኤው ያልተሳተፉትን ከፍተኛ አመራሩን ሳይጨምር 45 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እና ዘጠኝ የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን መምረጡንም አሳውቋል።
ይህ በአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ዕውቅና የሌለው የፓርቲው አመራሮች ምርጫ በህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን መሰንጠቅ የበለጠ የሚያሰፋው ሲሆን፣ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ያለውንም ግንኙነት የበለጠ የሚያባብሰው ይሆናል።
በህወሓት መሪዎች መካከል መካከል የተፈጠረው ክፍፍል በተባባሰበት ጊዜ በተካሄደው ጉባኤ መክፈቻ ላይ ደብረጽዮን (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር “በውስጣችን የተፈለፈለ የጥፋት አንጃ/ቡድን የሚያካሄደው እንቅስቃሴ የፓርቲውን ሁኔታ ወደከፋ ደረጃ እንዳሸጋገረው” ጉባኤ ማካሄድ ብቸኛ መፍትሄ ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።
ጉባኤው መካሄዱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል ያሉት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በሊቀመንበሩ የሚመራውን ቡድን “ከጀርባው ደጀን ይሆነናል፣ ይደግፈናል በሚሉት ባልታወቀ የውጭ ኃይል ተማምነው” መሆኑን ተናግረዋል።
ከሁለት ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት ውድመት ያላገገመችው ትግራይ ክልል ውስጥ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱ ሕግ እንዲከበር ከማሳሰብ ውጪ እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም።
በሁለቱ የፓርቲው አመራሮች መካከል በተፈጠረው መከፋፈል ውስጥ እስካሁን የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች የትኛውን ወገን ደግፈው እንደቆሙ የሚያመለክት ነገር ባይኖርም፤ አቶ ጌታቸው ገለልተኛ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ባለፈው ቅዳሜ እንደተናገሩት ጉባኤ ያካሄደው ቡድን ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለመቆጣጠር ሊሞክር እንደሚችል የተናገሩ ሲሆን፣ ይህም በፌደራል መንግሥቱ ይሁንታ የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር ህልውና ሊጥስ ይችላል።
እንደ አቶ ጌታቸው ስጋት የደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን የሚፈታተን ከሆነ የፌደራል መንግሥቱ ሊቃወም እና ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት ዕድል ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት አለ።