ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩናይትድ ኪንግደም የስደተኞች ጀልባዎችን በበይነ መረብ ማስተዋወቅ በወንጀል የሚያስጠይቅ ልታደረግ ነው
ሕገወጥ የስደተኛ ማቋረጦችን በበይነ መረብ ላይ የሚያስተዋውቁ ሰዎች የዩኬ መንግሥት ሊያስተዋውቀው ባቀደው አዲስ ሕግ እስከ አምስት ዓመት እስራት ሊጠብቃቸው ይችላል።
የዩኬ መንግሥት የድንበር ደህንነት፣ጥገኝነት እና ኢሚግሬሽን ሕጉ በትናንሽ ጀልባዎች ወደ እንግሊዝ የሚመጡትን ስደተኞች ቁጥር ለመቆጣጠር የሚወሰደው እርምጃ አካል ይሆናል።
ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚደረግ ሕገ ወጥ ስደትን መርዳት ቀድሞውንም ወንጀል ነው።
ነገር ግን ባለስልጣናት ጥፋቱ ፖሊስ እና ሌሎች ኤጀንሲዎች የወንጀል ቡድኖችን ለመግታት የበለጠ ስልጣን እንደሚሰጣቸው ያምናሉ።
ባለፈው ሳምንት የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እ.ኤ.አ. በ 2025 እስካሁን ከ 25,000 በላይ ስደተኞች በትናንሽ ጀልባዎች ወደ እንግሊዝ የገቡ ሲሆን ይህም በዚህ ዓመት ውስጥ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
አዲሱ የዩናይትድ ኪንግደም ሕግ በይነ መረብ ላይ የሚታተሙ ይዘቶችን መፍጠርን ወንጀል ያደርገዋል።
በዚህ ሕግ መሰረት የዩናይትድ ኪንግደም የኢሚግሬሽን ሕግን መጣስ የሚያመቻቹ አገልግሎቶችን የሚያስተዋውቁ ወይም የሚያቀርቡ ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ዒላማ ተደርገዋል።
ይህ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ ሰዎች የውሸት ፓስፖርቶችን ወይም ቪዛዎችን ለማስተዋወቅ ወይም በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሕገ ወጥ የስራ እድሎችን ቃል መግባትን የሚያካትት ሲሆን፤ ከእስር በተጨማሪ ትልቅ ቅጣትን ሊያስከትል ይችላል ።
የፖሊስ ሚኒስትሯ ዲያና ጆንሰን እንዳሉት ሕጉ የሚረቀቀው "ከአገር ውጭ ያሉትንም ለማካተት" ነው።
ይህም ማለት ማስታወቂያ በውጭ አገር ተሰርቶ ወንጀለኛው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከተጓዘ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት "ጉዳያቸውን በዚህ ሕግ መሰረት ይመለከቱታል" ማለት ነው።
አክለውም "ለብዙ ወራት እንዳደረግነው ሁሉ ከሌሎች አገራት ባለስልጣናት ጋር እነዚህን ሰዎች ተጠያቂ ለማድረግ፣ እነዚህን የወንጀል ቡድኖች ለመዝጋት እና ይህን የንግድ ሞዴል ለማስቆም እንሰራለን" ብለዋል።
በአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ ትንታኔ መሰረት በትንሽ ጀልባ ወደ እንግሊዝ ከሚገቡት ስደተኞች 80 በመቶ ያህሉ በጉዟቸው ወቅት ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እንደሚጠቀሙ ለባለሥልጣናቱ ተናግረዋል ።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ኢቬት ኩፐር እንዳሉት "በቀላሉ ገንዘብ ለማግኘት በሚል ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚደረገው ጉዞ እና በዚህች አገር ውስጥ ያለ ሕይወት አስተማማኝ ነው የሚል ሐሰተኛ መረጃ መሸጥ፣በበይነ መረብ ላይም ሆነ ከዛ ውጪ፣ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ነገር ነው።
"እነዚህ ወንጀለኞች በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ አሳሳች ስልቶችን በመጠቀም ስደተኞችን ለሕይወት አስጊ ወደ ሆነ ሁኔታ መምራታቸው ግድ አይላቸውም። እነሱን ለማስቆም የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠን ተነስተናል።"
የብሔራዊ የወንጀል ኤጀንሲ በ2024 ከ8 ሺህ በላይ ልጥፎችን በማንሳት የተደራጁ የኢሚግሬሽን ወንጀሎችን የሚያስተዋውቁ የበይነ መረብ ልጥፎችን ዒላማ ለማድረግ ከማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ጋር ይሰራል።
የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶች በመጠቀም መሻገሪያን ባስተዋወቁ በርካታ ሰዎችን በሚዘዋወሩ ቡድኖች ላይ የብሔራዊ የወንጀል ኤጀንሲ እርምጃ ወስዷል።
ለ17 ዓመታት በእስር ላይ የነበረው በፕሬስተን ኮንትሮባንዲስት አማንጅ ሀሰን ዛዳ የሚተዳደር ኔትወርክ ስደተኞቹ ስለረዳቸው እሱን ሲያመሰግኑ የሚያሳይ ቪዲዮ አውጥቷል።
የብሔራዊ የወንጀል ኤጀንሲ ኦፕሬሽን ጄኔራል ዳይሬክተር ሮብ ጆንስ እንዳሉት የታቀደው አዲስ ወንጀል ወንበዴዎችን እና የንግድ ሞዴሎቻቸው ላይ ለማነጣጠር ተጨማሪ አማራጮችን እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳዮች ቢሮ እንዳስታወቀው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ተጠቅመው የ12 ሺህ ፓውንድ "ጥቅል ስምምነቶችን" በብሪታንያ ለማስተዋወቅ የተጠቀሙ የአልባኒያ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ጉዳይ በታቀደው ጥፋት ውስጥ የሚታይ ይሆናል።
ወግ አጥባቂዎቹ እቅዱ "በጣም፣ በጣም ዘግይቷል" ብለዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳዮች ትይዩ ሚኒስትሩ ክሪስ ፊሊፕ "ይህ መጠነኛ ውሳኔ ችግሩን አያስተካክለውም" ብለዋል።
አክለውም የወግ አጥባቂው የጥረዛ ሕግ ፖሊሶች እና ሌሎች ኤጀንሲዎች "ሕገ ወጥ ስደተኞችን በአስቸኳይ እና ሳይዘገዩ እንዲያስወግዷቸው" ይፈቅዳል።
የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ማቋረጫ መንገዶችን ለመቀነስ ከፈረንሳይ ጋር በቅርበት መስራት ይፈልጋል።
በትናንሽ ጀልባዎች የሚመጡትን አንዳንድ ስደተኞች ወደ ፈረንሳይ ለመላክ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር እና በፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መካከል ስምምነት ተደረሷል።
ለተመለሰ እያንዳንዱ ስደተኛ ፈረንሳይ ከብሪታንያ ጋር የቤተሰብ ግንኙነት ያለውን ጥገኝነት ጠያቂን ወደ እንግሊዝ ትልካለች።
ነገር ግን ተቺዎች ይህ በአሁኑ ጊዜ ከሚሻገሩት መካከል ጥቂቱን እንደሚያካትት ጠቁመው እቅዱ ስደተኞችን ይከላከላል ወይ ብለው ጠይቀዋል።
በትናንሽ ጀልባ ወደ እንግሊዝ የገባ ማንኛውም ሰው የብሪታኒያ ዜጋ መሆን እንዳይችል ለማድረግ መንግሥት ሕጎችን አጠናክሯል።