ትራምፕ ከዜሌንስኪ ጋር በነበራቸው ውይይት "አስቸጋሪ ጉዳዮች ቢኖሩም" መሻሻል መታየቱን ተናገሩ

ዜሌንስኪ እና ፕሬዚዳንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዶናልድ ትራምፕ እና ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በፍሎሪዳ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ያካሄዱትን ውይይት ተከትሎ መሻሻሎች መታየታቸውን ቢናገሩም፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ግን የግዛት ጉዳይ አሁንም "አልተፈታም" ብለዋል።

የአሜሪካም ሆነ የዩክሬን ፕሬዚዳንቶች ውይይቱን "በጣም ጥሩ" ሲሉ ቢገልጹትም፣ ትራምፕ "አንድ ወይም ሁለት በጣም አወዛጋቢ ጉዳዮች" አሁንም ድረስ ሳይፈቱ ቀርተዋል፤ በተለይም በግዛት ጉዳይ ብለዋል።

ዜሌንስኪ በማር አ ላጎ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ከባለ 20 ነጥብ የሰላም ዕቅዱ መካከል "90 በመቶ" ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ሲገልጹ፣ ትራምፕ ደግሞ ለዩክሬን የተሰጠው የደህንነት ዋስትና "ወደ 95 በመቶ የሚጠጋው" ተጠናቋል ብለዋል።

ዜሌንስኪ የአሜሪካ እና የዩክሬን ልዑካን በሚቀጥለው ሳምንት ለአራት ዓመታት ያህል የቀጠለውን ጦርነት ለማስቆም ያለሙ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ እንደሚገናኙ ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ በቴሌግራም የመልዕክት መላላኪያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "በሁሉም ጉዳዮች ላይ ጉልህ ውይይት አድርገናል፤ የዩክሬን እና የአሜሪካ ልዑካን ባለፉት ሳምንታት ላሳዩት መቀራረብ ከፍተኛ አድናቆት አለን" ሲሉ ተናግረዋል።

ሩሲያ እአአ በየካቲት 2022 ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ የወረረች ሲሆን በአሁኑ ወቅት 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች።

ሩሲያ በአብዛኛው የምትቆጣጠረውን የምሥራቅ ዩክሬን የዶንባስ ክልልን ከወታደራዊ ኃይል ነፃ ቀጠና ለመቀየር የቀረበው ሀሳብ አሁንም "አልተፈታም" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።

ሞስኮ በአሁኑ ወቅት 75 በመቶ የሚሆነውን የዶኔትስክ ክልል እና 99 በመቶ የሚሆነውን የሉሃንስክ ክልል ትቆጣጠራለች። ክልሎቹ በአንድነት ዶንባስ በመባል ይታወቃሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሩሲያ፣ ዩክሬን አሁንም በዶንባስ የምትቆጣጠረውን ትንሽ ክፍል ለቅቃ እንድትወጣ ትፈልጋለች፣ ኪየቭ ደግሞ አካባቢው በዩክሬን ኃይሎች የሚመራ ነፃ የኢኮኖሚ ቀጠና እንዲሆን እየወተወተች ትገኛለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዩክሬን ያጣቻቸውን ግዛቶች በሚመለከት የነበራቸውን አቋም በተደጋጋሚ ቀይረዋል።

በመስከረም ወር ዩክሬን የተነጠቀችውን ግዛት መልሳ ልትወስደው እንደምትችል በመግለጽ ብዙዎችን አስገርመዋል። በኋላም ይህንን አቋማቸውን ቀይረዋል።

" ያ በጣም ከባድ ጉዳይ ነው" ካሉ በኋላ "የሚፈታ ጉዳይ ነው" ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።

ትራምፕ ዩክሬንን ከወደፊት ጥቃቶች ለመጠበቅ የሎጂስቲክስ ድጋፍ ለማድረግ ወይም ጦር ሰራዊት ለማሰማራት በይፋ ቃል ሳይገቡ የደህንነት ዋስትናዎች በሚመለከትም "95 በመቶ ተጠናቅቋል" ብለዋል።

ትራምፕ በአሜሪካ፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሦስትዮሽ ውይይት ሊኖር እንደሚችል በመግለጽ "ወቅቱን ጠብቆ" ሊከናወን እንደሚችል ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የዩክሬን ሩሲያ ጦርነትን እንዳስቆሟቸው ከሚገልጿቸው ግጭቶች ዝርዝር ውስጥ ለማካተት ቢፈልጉም፣ "በጣም መጥፎ" የሆኑ የተቋረጡ ወይም የቀሩ ውይይቶች ጦርነቱ እንዲቀጥል ሊያደርጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

ቀደም ሲል ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የስልክ ውይይት አድርገው ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ስለ ስልክ ውይይቱ ብዙ ዝርዝሮችን ይፋ ባያደርጉም፣ የሩሲያው መሪ "ዩክሬን ስኬታማ እንድትሆን ይፈልጋሉ" ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ትራምፕ ዩክሬን ሕዝበ ውሳኔ እንድታደርግ የሚያስችል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሞስኮ ብዙም ፍላጎት እንደሌላት አምነዋል።

"ያንን አቋማቸውን ተረድቻለሁ" ሲል ተናግረዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ የስልክ ጥሪው የተደረገው በትራምፕ ጥያቄ እንደሆነ እና እሱና ፑቲን ጦርነቱን ለማስቆም በቅርቡ የአውሮፓ ኅብረት እና ዩክሬን ባቀረቧቸው ሀሳቦች ላይ እንደተወያዩ ተናግረዋል።

የሩሲያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ኡሻኮቭ በበኩላቸው ትራምፕ የክሬምሊንን የውሳኔ ሃሳቦች ግምገማ አዳምጠዋል።

ሁለቱ ፕሬዚዳንቶችም በአውሮፓ ኅብረት እና በዩክሬን የቀረበው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ግጭቱን ያራዝመዋል የሚለው ነጥብ ላይ በመግባባት ውይይታቸውን አጠናቀቅቀዋል ብለዋል።

ዜሌንስኪ የዩክሬን ባለሥልጣናት በጥር ወር በዋይት ሐውስ ከአውሮፓ መሪዎች ጋር በመሆን ሊወያዩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኧርሰላ ቮን ደር ሌየን ከአውሮፓ አጋሮች ጋር ባደረጉት ስብሰባ በፍሎሪዳ የተካሄደው ውይይት "ጥሩ መሻሻል" መታየቱን አድንቀው ዩክሬን "ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ጠንካራ የማይደፈር የደህንነት ዋስትናዎችን" እንድታገኝ ያስፈልጋል ብለዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የኪየቭ አጋሮች በሚቀጥለው ወር በፓሪስ ተገናኝተው የደህንነት ዋስትናዎች ላይ እንደሚወያዩም ተናግረዋል።