በሶማሊያ የአንዲት ሕፃን ዘግናኝ ግድያ የቀሰቀሰው ሕዝባዊ ቁጣ

የፎቶው ባለመብት, Radio Gaalkacyo
በአሁኑ ሰዓት በሶማሊያ አንዲት ሴት በምታሳድጋት የ14 ዓመት ታዳጊ ሕፃን ግድያ ተበይኖባት የሞት ፍርዷን እየጠበቀች ነው።
ባለፈው ኅዳር ሳብሪን ሳይላን የተባለችው ሕፃን ላይ በአሳዳጊዋ የተፈፀመው ግድያ እና የግድያውን ዘግናኝ ሁኔታ የቀሰቀሰው ተቃውሞ በአገሪቱ የሕፃናትን ደህንነት ለመጠበቅ አዲስ ውትወታዎች እንዲበረቱ አስገድዷል።
ግድያው በተለይም በቤተሰብ አባላት የሚፈፀም የሕፃናት ጥቃት እምብዛም ለፖሊስ በማይቀርብበት አገር ሕዝባዊ ቁጣን ቀስቅሷል።
ለአብዛኞቹ የሳብሪን ግድያ ሕፃንትን መጠበቅ ያለመቻል ውድቀት እና እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶችን ለመከላከል የተቀመጡ የሕግ ማዕቀፎች ገቢራዊነት ክፍተት መሆኑ ማሳያ ተደርጓል።
ለግድያው የ34 ዓመቷ ሆዳን ሞሐመድ ዲሪይ ከፍተኛው የሕፃናት ጥቃት ቅጣት የሆነው የሞት ፍርድ መፈረዱ በሶማሊያ ታይቶ የማይታወቅ ክስተት ሆኖ ተመዘግቧል።
ዲሪይ ክሱን ብታስተባብልም ጠበቃዋ ግን ብይኑን በመቃወም ይግባኝ አላሉም።
የ65 ዓመቱ ባለቤቷ አብዲዚዝ ኖር ከግድያው ነፃ ቢባሉም ቸልተኝነት በማሳየታቸው የአንድ ዓመት እስር እና በ500 ዶላር የገንዘብ ቅጣት ተበይኖባቸዋል።
ሟቿ ሳብሪን ገና በአንድ ዓመቷ ነበር ወላጆቿን በሞት ያጣችው።
ሁለቱም አያቶቿን በሞት በማጣቷ አደራ የተሰጣት የእናቷ አክስት ትምሕርት እንድትማር እና ባሕላዊ የቁራን ትምሕርት ቤት እንድትገባ አድርጋለች።
ይሁን እንጂ የሳብሪን ሕይወት ወደ አሳዛኝ ምዕራፍ የታጠፈው የቤት ውስጥ እገዛ እንድትሰጥ ወደ ዲሪያ ቤተሰብ ስትሰጥ ነበር።
ፖሊስ በምርመራው ታዳጊዋ ለሁለት ወራት ከዲሪያ ቤተሰብ ጋር ስትኖር ድብደባ እና ስቅይት ወይም "ተደጋጋሚ አካላዊ ጥቃት" እንደተፈፀመባት ታውቋል።
ከዲሪያ ተንቀሳቃሽ ስልክ የተገኘ የድምፅ እና የምስል ማስረጃ ተደጋጋሚ ጥቃት እንደተፈፀመባትም ያሳያል።
ከፍርድ ሂደቱ በፊት ይህ ማስረጃ ባልታወቀ ሰው አማካኝነት አፈትልኮ ለሕዝብ ይፋ ሆኗል።
በአንድ ድምፅ ቅጂ ዲሪያ "ሕመምሽ እያስደሰተኝ ነው" ስትል ትሰማለች።
የአስከሬን ምርመራ ሪፖርት እንደሚያሳው ሳብሪን ተደጋጋሚ ጉዳት እና በስለት መወጋቷን የሚያሳይ ቁስል የተገኘ ሲሆን፤ ለረጅም ጊዜ ጥቃት እንደደረሰባት ታውቋል።
በፖሊስ ምርመራ ዝርዝር መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ የሕዝብ ቁጣ ጨምሯል።

የፎቶው ባለመብት, Abdiqaadir Washington
በሶማሊያ ከፊል ራስ ገዝ ግዛት ፑንትላንድ ትልቅ ከተማ በሆነው በጋልካዮ ጎዳናዎች "ፍትኅ ለሳብሪን" እና ለሞቷ ተጠያቂዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ጥሪ ባቀረቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች እና ወጣቶች ተጥለቅልቀው ነበር።
ተቃዋሚዎች አስከሬኗ በጊዜያዊነት ባረፈበት ሆስፒታል አካባቢም ተሰባስበው ነበር።
በአንድ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በተቃዋሚዎች እና በፖሊስ መካከል ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ አንድ ሰው በተተኮሰበት ጥይት ተገድሏል። መሣሪያውን ማን እንደተኮሰው ግልፅ አይደለም።
በኦንላይንም ወጣት ሴቶች እና ታዳጊዎች የሳብሪንን ስም በመጠቀም የአጋርነት ዘመቻዎችን አካሂደዋል።
የ18 ዓመቷ ተቃዋሚ አኒሶ አብዱላሂ "የትኛውም ሕፃን እንደዚህ ሆኖ መሞት የለበትም" ስትል በማኅበራዊ ትስስር ገፅ ላይ በቪዲዮ አጋርታለች።
"ባህላዊ ሽማግሌዎች ግድያውን በጎሳ ባህል አሊያም በውስጥ ለውስጥ ለመፍታት የሚያደርጉትን ሙከራ እንቃወማለን።"
ይህም በአገሪቱ ባህል ከወንጀል ጥፋተኝነት ብይን ይልቅ የበቀል ግድያን እና ተጨማሪ ግጭትን ለማስቀረት ዓላማ በመሰነቅ ከበዳይ እና ተበዳይ ጎሳዎች የተውጣጡ ሽማግሌዎች ሁኔታውን ለመፍታት የሚያደርጉት ሂደት ነው።
በዚህ ስርዓት ካሳ መክፈል የተለመደ ሲሆን፤ ሂደቱ ለተጎጂዎች ፍትኅ ከመስጠት ይልቅ ሰላም ማስፈን ላይ ያተኮረ ነው። በዚህ ሂደት የሴቶች እና ሕፃናት ድምፅ የማይሰማ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ወንጀሎችም እልባት አያገኙም የሚል ቅራኔ አለ።
በሶማሊያ የሕፃናት መብት ጥሰት ቤት ውስጥ የሚደበቅ ሲሆን፤ በቤተሰብ ጉዳዮች መነግሥት እንዲገባ አይፈለግም።
የዲሪያ የፍርድ ቤት ውሎ እና ሌሎች ተያያዥ የፍርድ ሂደቶች በፍትኅ ስርዓቱ ሕዝባዊ አመኔታን ለመገንባት በማኅበራዊ ትስስር ገፆች በቀጥታ እንዲተላለፉ ተደርጓል።
የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ ሞሐመድ አብዱልሀኪም ብይኑ ለታዳጊዋ ግድያ ፍትኅ ለማግኘት ለተደረገው ጥረት ትልቅ ውሳኔ ነው ብለዋል።
"አጥቂዎቹ የሞት ውሳኔያቸው ተፈፃሚነትን መጠባበቅ ብቻ ነው የቀራቸው። በዚህ ወንጀል ሌሎች ተሳታፊዎች እንዳሉ ተጨማሪ ማስረጃዎች ከተገኙ አንተዋቸውም፤ ሕግ ለእነርሱም ሙሉ ለሙሉ ተፈፃሚ ይሆናል" ብለዋል።
ዶሆዳን የተባለው የሕፃናት መብት ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ነጅብ ወህሊ "የክስ መዝገቡ በማኅበረሰባችን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት የሆነው የሕፃናት መብትን ለመጠበቅ ያለውን ሰፊ ክፍተት ያሳየ ነው" ሲሉ ገልፀዋል።
"ሕፃናት በቤተሰባቸው ቤታቸው ውስጥ ጥቃት እየተፈፀመባቸው ነው። እናም በጣም አስከፊ የሆኑ ጥቃቶች ፖሊስ ላይ አይደርሱም" ሲሉ አክለዋል።
ባለፈው ሰኔ ወር በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ የሦስት ዓመት ልጅ በእንጀራ እናቱ ቤት ውስጥ ጥቃት እንደተፈፀመበት ለፖሊስ ሪፖርት ደርሶታል።
በጥቃቱ የተጠረጠሩት ሰዎች ወዲያው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሶማሊያ የሚገኘው የሕፃናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ችልድረን) መረጃ በአገሪቱ ከጥቅምት እስከ ኅዳር ባለው ጊዜ ሦስት አስከፊ የሕፃናት ጥቃቶች ተፈፅመዋል።
በሐርጌሳ የአራት ሕፃና በእሳት ቃጠሎ ግድያ፣ በፑንትላንድ የ11 ዓመት ሕፃን ላይ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እና በማዕከላዊ ሶማሊያ አንድ እናት ከሦስት ልጆቿ ጋር ተገድለዋል።
በጋልካዮ የሴቶች ማሕበር ኃላፊ ሽኩሪ አብዲ ማኅበረሰቡ በቤት ውስጥ በሚፈፀመው ጥቃት እና ፍርድ ቤት የማይደርሱ ጥቃቶች ከአቅሙ በላይ ሆነዋል ይላሉ።
ባለፈው ጥቅምት የሶማሊያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአፍሪካ ሕብረት ያወጣውን የሕፃናት ደኅንነት እና መብት ቻርተር በ10 ተቃውሞ እና በአምስት ድምፀ ታቅቦ አፅድቋል።
ለአስርት ዓመታት ያስቆጠረው ሕጉ ጥቃትን፣ ብዝበዛን እና ታዳጊዎች ለመጠበቅ የሕግ አማራጮችን የያዘ ነው።
ሕጉ ሁሉንም ዓይነት የሕፃናት ጥቃትን በወንጀል የደነገገ እና ሕፃናትን በሚጎዱ አሳዳጊዎች ላይ ቅጣት ጠንከር ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ የቁጥጥር እና ክትትል ዜዴዎችን ማቋቋም የያዘ ነው።
ሕጉ ከፀደቀ በሦስት ቀናት በኋላ የአገሪሩ የቤተሰብ ሚኒስቴር እና የሰብዓዊ መብቶች ልማት ቢሮ በቻርተሩ ዙሪያ ባወጡት ማብራሪያ ቻርተሩ በእስላማዊ ሕግ እና በሕገ መንግሥቱ መሰረት እንደሚፈፀም አስታውቀዋል።
ሚኒስቴሩ ቻርተሩ ከ18 ዓመት በታች ጋብቻን መከልከሉ እስከ 15 ዓመት ጋብቻን የሚፈቅደውን የሸሪያን ሕግ ይቃረናል በሏል።
የሳብሪን ሕይወት በአጭር ቢቀጭም ሞቷ በሶማሊያ አድሮ የከረመው የሕፃናት ደኅንነት ውይይት እንዲደረግበት አስገድዷል።
ማኅበረሰቡ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ እየተነጋገረ ባለበት በዚህ ጊዜ አንዳንዶች ፍትኅ በዚህ መንገድ ትቀጥላለች የሚለው ያጠራጥራቸዋል።
"አሁን የምንደሰትበት ጊዜ አይደለም፤ አሁንም ግልፅነት እንፈልጋለን" ትላለች ከወጣት ተቃዋሚዎች ውስጥ አንዷ የሆነው ተቃዋሚ።
"የቃል ፍትኅ አንፈልግም፤ በዓይናችን ማየት እንሻለን። እንዲዘገይ አንፈልግም።"















