ልጇን አግታ ሸጣለች የተባለችው ደቡብ አፍሪካዊት እናት ተፈረደባት

ጆሽሊን የተባለችው የስድስት ዓመት ልጅ ከጠፋች አንድ ዓመት አልፏታል።

የፎቶው ባለመብት, Executive Mayor Andrè Truter/ Facebook

የምስሉ መግለጫ, ጆሽሊን የተባለችው የስድስት ዓመት ልጅ ከጠፋች አንድ ዓመት አልፏታል

የስድስት ዓመት ልጇን አግታ በሕገወጥ መንገድ አዘዋውራለች የተባለችው ደቡብ አፍሪካዊት እናት ላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳለፈ።

ፍርድ ቤት ኬሊ ስሚዝ የተባለችው እናት እንዲሁ የወንድ ጓደኛዋ ዩአኪን አፖሊስ እና ጓደኛቸው ስቴቨኖ ቫን ራየን ጥፋተኛ ናቸው ሲል በይኗል።

ጆሽሊን የተባለችው የስድስት ዓመት ልጅ ከጠፋች አንድ ዓመት አልፏታል። በደቡብ አፍሪካዋ ኬፕ ታውን ከተማ ከሚገኘው ሳላዳና ቤይ አካባቢ ነበር ጆሽሊን የጠፋችው።

ሦስቱ ተጠርጣሪዎች ከዚህ ቀደም ጥፋተኛ አይደለንም ሲሉ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተው ነበር።

የጆሽሊን መጥፋት ደቡብ አፍሪካውያንን አስደንግጧል። እስካሁን ድረስም አልተገኘችም።

ዐቃቤ ሕግ የልጅቷ እናት "ሸጣታለች ወይም አዘዋውራታለች። አልያም ደግሞ ለውጣታለች" ሲል ክሱን አቅርቧል።

እናትየዋ ልጅቷ ጠፍታለች ብላ መዋሸቷንም ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

የስድስት ዓመት ልጇን አግታ አዘዋውራለች የተባለችው ደቡብ አፍሪካዊት እናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የስድስት ዓመት ልጇን አግታ አዘዋውራለች የተባለችው ደቡብ አፍሪካዊት እናት

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በተላለፈበት ቀን በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን በአካባቢው ተሰባስበው ዜናውን ለመስማት ሲጠባበቁ ነበር።

በአካባቢው መጨናነቅ እንዳይፈጠር መንገዶች ተዘግተው ፖሊስም ተሰማርቷል።

የእናትየዋ ጎረቤት የነበረችው እና ዐቃቤ ሕግ ምስክር አድርጎ ያቀረባት ሎውሪንታ ሎምባርድ እንዳለችው፣ እናትየዋ "የሞኝ ሥራ ሠርቻለሁ" ብላ ልጇን ለባህላዊ ሐኪም መሸጧን ነግራታለች።

በደቡብ አፍሪካ ሳንጎማ ለሚባሉት ባህላዊ ሐኪሞች ልጇን መሸጧን ለፍርድ ቤት ገልጻለች።

"ጆሽሊንን ባህላዊው ሐኪም የወሰዳት ለዓይኗ እና ለቆዳዋ ሲል ነው" ብላለች።

በአካባቢው የሚያገለግሉ ፓስተርም ለፍርድ ቤት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን፣ የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ኬሊ ልጆቿን በ1,100 ዶላር እንደምትሸጥ ስትናገር መስማታቸውን ገልጸዋል።

ጆሽሊን መጥፋቷን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካውያን አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጆሽሊን መጥፋቷን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካውያን አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል

ጆሽሊን መጥፋቷን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካውያን አደባባይ ወጥተው ፍትህ እንዲገኝ ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል።

በተፈጥሮዋ ሰማያዊ እና አረንጓዴ ዓይን የነበራት ጆሽሊን ለዓይኗ እንዲሁም ነጣ ለሚለው ቆዳዋ በሚል ለባህላዊ ሐኪም መሸጧ በፍርድ ቤት ተገልጿል።

ፍለጋው በስፋት ቢቀጥልም እስካሁን ድረስ የደረሰችበት ሊታወቅ አልቻለም።