አይቮሪ ኮስት በማሊ የተያዙባት 49 ወታደሮቿ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP
አይቮሪ ኮስት በማሊ በቁጥጥር ሥር የዋሉባት 49 ወታደሮቿ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠየቀች።
አይቮሪ ኮስት ወታደሮቹ በማሊ መንግሥት የተያዙት “ሕገ-ወጥ” በሆነ ሁኔታ ነው ብላለች።
የማሊ ወታደራዊ መንግሥት በበኩሉ ወታደሮቹ ቅጥረኛ ወታደሮች ናቸው ብሏል።
ወታደሮቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ባሳለፍነው እሁድ ሐምሌ 03/2014 ዓ.ም. በማሊ መዲና ባማኮ አየር ማረፊያ ነበር።
የአይቮሪ ኮስት መንግሥት ወታደሮቹ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት አንዳቸውም የጦር መሳሪያ ታጥቀው እንዳልነበረ እና ወደ ማሊ የተጓዙት የተባበሩት መንግሥት ሰላም አስከባሪ ኃይል አፕሬሽን አካል ሆነው ነው ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በማሊ መንግሥት የተያዙት ወታደሮች በአገሪቱ ከተሰማሩ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች መካከል የሚገኑ ናቸው ብሏል።
የአይቮሪ ኮስት ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በማሊ የታሰሩትን ወታደሮች በተመለከተ በፕሬዝደንቱ የተመራ አስቸኳይ ስብሰባ ማድረጉን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ በሕዝቡ ዘንድ መረጋጋት እንዲፈጠር ጠይቆ፤ ወታደሮቹን ለማስለቀቅ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ ገልጿል።
በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዘው የማሊ ወታደራዊ መንግሥት ከጎረቤት አገራት እና ከምዕራባውያን ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየሻከረ ይገኛል።
በማሊ ጸንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎችን ሲዋጋ የነበረው እና በፈረንሳይ የሚመራ ጥምር ኃይል ከወራት በፊት ከአገሪቱ መውጣት ጀምሯል።
ፈረንሳይ ቅኝ ትገዛት በነበረችው ማሊ ከ5ሺህ ያላነሱ ወታደሮችን አሰማርታ ነበር።
በማሊ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የማሊ እና ፈረንሳይ ግንኙነት እጅጉን ተቀዛቅዟል።
ከወራት በፊት ምዕራባውያን አገራት የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች በማሊ መሰማራታቸውን አስታውቀው ነበር።
ይህ መቀመጫውን በሩሲያ ያደረገ ዋግነር ግሩፕ የተሰኘ የቅጥረኛ ወታደሮች ስብስብ ከዚህ ቀደም በሶሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሱዳን፣ ሊቢያ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ ተሰማርቶ እንደነበረ ተዘግቧል።
ምዕራባውያን ይህ ቅጠረኛ ቡድን የራሱን እና የሚሰማራባቸው አገራት መንግሥታትን ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ ይሰራል ሲሉ ይተቻሉ።












