በአጣዬ ከተማ ከትላንት ረፋድ ጀምሮ በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ የሰዎች ሕይወት አለፈ

በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ አጣዬ ከተማ ከትናንት እሁድ ረፋድ ጀምሮ በመከላከያ ሠራዊት እና በታጣዊዎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የሰው ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናገሩ።

እሁድ ኅዳር 30/2016 ዓ. ም. የመከላከያ ሠራዊት ከፋኖ እና መንግሥት “ሸኔ” ከሚላቸው ታጣቂዎች ጋር በአካባቢው የተኩስ ለውውጥ ማድረጉን አራት የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአጣዬ ከተማ ነዋሪ፣ የተኩስ ልውውጡ እሁድ ረፋድ ላይ እንደተጀመረ ገልጸው፣ ዛሬ ሰኞ እስከ እኩለ ቀን ገደማ ድረስ “አልፎ አልፎ ይተኮሳል” ብለዋል።

ነዋሪው አክለውም ሰኞ ረፋድ በመከላከያ እና በታጣቂዎች መካከል ከሚደረገው የተኩስ ልውውጡ በመሸሽ ላይ የነበሩ ሰዎች በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው ማለፉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች በባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ከአጣዬ ከተማ ይምለዎ ወደምትባል የገጠር ቀበሌ “ሽሽት” ላይ እንደነበሩ ነዋሪው አክለዋል።

በተኩስ ለውውጡ ሕይወታቸውን ያጡት ነዋሪዎች ብዛት አራት መሆኑንም ነዋሪው ጨምረው ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌሎች ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎች በተኩስ ልውውጡ የሰዎች ሕይወት ማለፉን ቢያረጋግጡም የሟቾች ቀጥርን በተመለከተ ግን የሰጡት አሃዝ የተለየ ነው።

ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላ የአጣዬ ከተማ ነዋሪ ሕይወታቸውን ያጡት “ሁለት ጠና ያሉ ሴት የባጃጁ ተሳፋሪዎች” መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሦስተኛው የከተማዋ ነዋሪ በበኩሉ “ቁጥራቸውን ይሄን ያህል ማለት አይቻልም። አሁንም በከተማዋ ውስጥ የተኩስ ልውውጡ ስላልቆመ እንኳን ቁጥሩን ለማወቅ ይቅር እና እነማን እንደሞቱም ለመለየት አዳጋች ነው” ሲል የሟቾቹን ቁጥር በአሃዝ ለማስቀመጥ አንደሚያስቸግር ተናግሯል።

በአጣዬ ከተማ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ የእሁዱ የመጀመሪያው አይደለም። የከተማዋ ነዋሪዎች ጆሮም ከተኩስ ድምጽ ጋር ከተላመደ ሰንበትበት እንዳለ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የእሁድ ረፋዱ የተኩስ ልውውጥ የተጀመረው በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ተኩሱ ከአጣዬ ከተማ ወደ መሃል ሜዳ በሚወስደው መንገድ ላይ ከተጀመረ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት ወደ አጣዬ ከተማ መመለሱን ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ።

አንድ ስማቸው እንዳይገልጽ የጠየቁ ነዋሪ፤ “ከእሁድ ጠዋት ጀምሮ የተኩስ ልውውጡ ተጀመረ። የተኩስ ልውውጡ በፋኖ እና መከላከያ መካከል ነው። መነሻው እነሱ [መከላከያ] ገጠር አካባቢ ያሉበት ሄደው በከባድ መሣሪያ በመደብደባቸ ነው። ከዚያ በኋላ ገጠር የነበሩት መከላከያዎች ወደ ከተማ ለቅቀው መጡ” ሲሉ አብራርተዋል።

የተኩስ ልውውጡ ከተጀመረ በኋላ አጣዬ ከተማን ለቀው ወደ ማጀቴ የሸሹ አንድ ነዋሪ በበኩላቸው፤ “ማታ መከላከከያ ይምለዎ ከሚባለው አካባቢ ተነስቶ ወደ ከተማ ሲገባ እኔ ባጃጅ ይዤ ወደ ማጀቴ ከተማ ሄድኩኝ” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል።

የተኩስ ልውውጡ ከተጀመረ በኋላ እሁድ አመሻሽ ላይ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ገብተው እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ወደ ከተማዋ ገብተው ነበር” የተባሉት የፋኖ ታጣቂዎች አጣዬን ለቀው ከወጡ በኋላ፤ “የሸኔ ታጣቂዎች” በከተማዋ ከነበረው የመከላከያ ሠራዊት ጋር የተኩስ ልውውጥ መጀመራቸውንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አንድ ነዋሪ ሁኔታውን ሲያስረዱ፤ “[የፋኖ ታጣቂዎች] ከተማው ውስጥ ገቡ እና ወደ አንድ ሰዓት አካባቢ ተመልሰው ወጡ። ከዚያ እንደገና ሸኔ የሚባለው መተኮስ ጀምረ እና አዳራቸውን ሲተኩሱ አደሩ። ጋብ ቢልም ሕዝቡ ተፈናቅሏል” ብለዋል።

ሌላ ነዋሪ ደግሞ “[ሰኞ] ከጠዋት ጀምሮ ነው ትንሽ ከበድ ያለው። ኦነግ ሸኔ ወደ ከተማዋ እገባለሁ ሲል መከላከያ ደግሞ ወደ እነሱ እየተኮሰ ነው ያለው” ሲሉ በከተማዋ ዙሪያ ያለውን ሁኔታ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የአካባቢውን ባለሥልጣናትን አስተያት ለማካተት ቢቢሲ ያደረገው ጥረት የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ አሳልፍ ደርቤ፤ “አሁን እኔ እዚያ አካባቢ የለሁም” በማለታቸው አልተሳካም።

ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በተፈጸሙ ጥቃቶች የነዋሪዎች ሞት እና መፈናቀል በተደጋጋሚ ከሚከሰትባቸው አካባቢዎች መካከል የአጣዬ ከተማ አንዷ ናት።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የምትገኘው አጣዬ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ጋር ትጎራበታለች።

በከተማዋ ለሚደርሰው ተደጋጋሚ ጥቃት መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን በአካባቢው ባለሥልጣናት ተጠያቂ ይደረጋል።