ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፓኪስታን ባለሥልጣናት ‘አሳፋሪ’ ያሏት የዓለም የቁንጅና ተወዳዳሪ
በፓኪስታን የቁንጅና ውድድር አገሪቷን እያወዛገበ ይገኛል።
በውድድሩ ላይ ከአገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ፖለቲከኞች ውግዘት ብቻ ሳይሆን፣ ምርመራም እንዲከፈት ትዕዛዝ ተላልፏል።
ጃምዓት አል ኢስላሚ የተባለ ፓርቲን የሚመሩት የፓኪስታኑ የሕዝብ ተወካይ ሙሽታቅ አህመድም ውድድሩን ‘አሳፋሪ’ ሲሉ ጠርተውታል።
አገሪቷን በጊዜያዊነት እንዲመሩ የተመረጡት ተጠባባቂው ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋል አል ሃቅ ካካር በውድድሩ ላይ ምርመራ እንዲደረግ አዘዋል።
በተለያዩ ማኅበራዊ ድረገጾች ላይም ጉዳዩ መወያያ ሆኗል።
በተለይም የፓኪስታን ወንዶች በዝምታ አልተመለከቱትም፣ በጥላቻ እና በትችት የተሞሉ መልዕክቶቻቸውን እያዘነቡ ይገኛሉ።
እንዲህ ዓይነቱ ቁጣ እየደረሰባት ያለችው ደግሞ በዓለም የቁንጅና መድረክ ፓኪስታንን ትወክላለች የተባለችው የ24 ዓመቷ ሴት ናት።
ኤሪካ ሮቢን ትባላለች።
በካራቺ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ኤሪካ የክርስትና እምነት ተከታይ መሆኗም ሌላ የውዝግብ መነሻ ሆኗል።
ኤሪካ ወግ አጥባቂነት ስር የሰደደባትን ፓኪስታንን ‘ሚስ ዩኒቨርስ’ በተሰኘው የቁንጅና ውድድር እንድትወክል ተመርጣለች።
በማልዲቪስ በተካሄደው ውድድር ከአምስት የፍጻሜ ዕጩዎች መካከል ኤሪካ ‘ሚስ ዩኒቨርስ ፓኪስታን’ ተብላለች።
ዝግጅቱን ያዘጋጀው በዱባይ መቀመጫውን ያደረገው ዩገን ግሩፕ የተባለ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ ሚስ ዩኒቨርስ ባህሬን እና ሚስ ዩኒቨርስ ግብፅ የተሰኙት ውድድሮች መብትም ባለቤት ነው።
ፓኪስታንን በዓለም መድረክ ለምትወክለው ‘ሚስ ዩኒቨርስ ፓኪስታን’ በርካታ አመልካቾች እንደነበሩ ድርጅቱ አስታውቋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ሚስ ዩኒቨርስ የቁንጅና ውድድር በደቡብ አሜሪካዋ ኤል ሳልቫዶር ውስጥ በኅዳር ወር ይካሄዳል።
ውግዘት እና ድጋፍ ያስተናገደው የቁንጅና ውድድር
“ፓኪስታንን መወከሌ በጣም ደስ ብሎኛል። ነገር ግን ይኼ ሁሌ ውግዘት ከየት እንደመጣ አልገባኝም። ምናልባትም በወንዶች በተሞላ ክፍል ውስጥ የዋና ልብስ ለብሳ ትመላለሳለች የሚለው ሃሳብ ሊሆን ይችላል” ስትል ኤሪካ ለቢቢሲ ተናግራለች።
‘ለሚስ ዩኒቨርስ’ መታጨቷን እየተቹ ያሉ ወገኖች አገሪቷ መወከል በማትፈልግበት የቁንጅና ውድድር ላይ መወከሏ ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ።
ከ90 በመቶ በላይ የሆነው ሕዝቧ የእስልምና እምነት ተከታይ በሆነው ፓኪስታን የቁንጅና ውድድር ብርቅ እና ድንቅ ነው።
ሆኖም በዓለም ዙሪያ ላሉ የፓኪስታን ተወላጆች የቁንጅና ውድድር አዲስ አይደለም። ‘ሚስ ፓኪስታን ወርልድ’ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የፓኪስታን ዝርያ ያላቸው ቁንጅና ተወዳዳሪዎችን ያሳትፋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው በአውሮፓውያኑ 2002 በቶሮንቶ ሲሆን፣ በ2020 ወደ ላሆር ተዛውሯል።
ሆኖም በሚስ ዩኒቨርስ የ72 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ፓኪስታን ተወክላ አታውቅም።
ኤሪካ በዙም በተካሄደው ሁለተኛ ዙር የምርጫ ውድድር ላይ ለአገሯ ልታደርገው የምትፈልገውን አንድ ነገር እንድትጠቅስ መጠየቋን ታስታውሳለች።
እሷም “ፓኪስታን ኋላ ቀር አገር ናት የሚለውን አስተሳሰብ መቀየር እፈልጋለሁ” ብላ መመለሷንም ጠቅሳለች።
መታጨቷን ተከትሎ እያስተናገደችው ካሉ የጥላቻ ምላሾች እና ውግዘቶች አንጻር ይህንን ማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል።
ሆኖም የሁሉም ምላሽ ግን ጥላቻ ብቻ አይደለም።
ውደሳ እና ምስጋናንም ከአንዳንድ ስፍራዎች እየደረሳት ትገኛለች።
በአገሪቷ ያሉ ፀሐፊዎች፣ ጋዜጠኞች እና ሞዴሎች ለቁንጅና ተዋዳዳሪዋ የእንኳን ደስ አለሽ መልዕክታቸውን እያጎረፉላት ይገኛሉ።
“ውበት እና ድንቅ ጭንቅላትን የተላበሰች” ስትል ማሪያና ባባር የተባለች ጋዜጠኛ አሞግሳታለች።
ኤሪካን ወደ ሞዴልነት እንድትገባ ያበረታታቻት ቫኔዛ አህመድ በበኩሏ “በዓለም አቀፍ የወንዶች ውድድር ላይ ‘ሚስተር ፓኪስታን’ ሲባሉ ምንም ችግር የለባቸውም። የሴት ስኬት ለምን ችግር ሆነባቸው” ስትልም ለቮይስ ኦፍ አሜሪካ የኡርዱ ቋንቋ አገልግሎት ተናግራለች።
ከሮክ ሙዚቃ ወደ እስላማዊ ሪፐብሊክ
“የበርካታ ቅራኔዎች መገኛ አገር ነን። ይህም ሴቶንች እና ሌሎች የተገለሉ ማኅበረሰቦች የበለጠ ይነኩናል” ሲሉም የካራቺ ነዋሪ ፀሐፊ እና ተንታኝ ራፋይ መህሙድ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
“ፓኪስታን ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት የሰፈነባት አገር ናት። ይህም በተቋም እንዲሁም በማኅበራዊ ደረጃ በሚታዩ የፆተኝነት እሴቶች ውስጥ ይንጸባረቃል። ኤሪካ ሮቢን የገጠማት እና እሷን የመቆጣጠር ሁኔታም የሥርዓቱ ቅጥያ ነው” ይላሉ።
ፓኪስታን በአሁኑ ወቅት መገለጫዋ ስር የሰደደ ወግ አጥባቂነት ቢሆንም፣ በአንድ ወቅት ማኅበረሰቡ ሻል ያለ ለዘብተኝነት ይታይ እንደነበረ የታሪክ ማኅደራት ያስረዳሉ።
ከአውሮፓውያኑ 1950ዎቹ እስከ 1970ዎቹ መገባደጃ ድረስ ዶውን የተሰኘው ጋዜጣ ያወጣቸው የነበሩ ማስታወቂያዎች የዚህ ለዘብተኝነት ማሳያ ናቸው።
የካባሬት እና የውጭ አገር ዳንሰኞች ‘የቤሊ ዳንስ’ የተሰኘውን የዳንስ ዓይነት ትርዒት በካራቺ በሚገኝ ክለብ ዝግጅታቸውን ያቀርባሉ ይላሉ።
የካራቺ የምሸት ክበቦች በ60ዎቹ እና በ70ዎቹ ታዋቂዎች ነበሩ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ዲፕሎማቶች፣ ፖለቲከኞች፣ የአውሮፕላን አስተናጋጆች መሰባሰቢያዎችም ነበሩ።
በካራቺ የሚገኘው ታሪካዊው ሜትሮፖል ሆቴል የጃዝ ሙዚቃ ማዕከልም ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1973 የፓኪስታን ፓርላማ አገሪቱ እስላማዊ ሪፐብሊክ ናት ብሎ ሲያውጅ ሁኔታዎች ተቀየሩ።
እስልምናም የመንግሥት ሃይማኖት ነው ተሎም በሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፈረ።
ከአራት ዓመታት በኋላ ወታደራዊው መሪ ጄኔራል ዚያ ኡል ሃቅ የጠቅላይ ሚኒስትር ዙልፊካር አሊ ቡቶን አመራር በመፈንቅለ መንግሥት ገርስሰው ሥልጣን ተቆጣጠሩ።
ከዚያ በኋላ የተከተሉት አስርት ዓመታት በአገሪቷ ታሪክ ውስጥ አስከፊ ምዕራፍ እንደሆኑ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በአገሪቷ እስላማዊ ሕጎች ተግባራዊ መደረግ ሲጀምሩም የፓኪስታን ማኅበረሰብ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀየረ።
ይባስ ብሎ በ1980ዎቹ አጋማሽ ጄኔራል ዚያ ለእስልምና ሕግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማሳየት የአደባባይ ግርፋትን እንደገና አመጡ።
በአሁኑ ወቅት እስከ 70ዎቹ መጀመሪያ የነበሩት የደመቁ የምሸት ክበቦች እና መጠጥ ቤቶች ደብዛቸው ጠፍቷል።
ታሪካዊው የሜትሮፖል ሆቴል የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል።
ነገር ግን ፓኪስታን ነጻ እና የሁሉንም ስሜት የምታስተናግድ እንድትሆን መፈለጉ ሙሉ በሙሉ አልደበዘዘም።
እንደ ኤሪካ ያሉ የቁንጅና ተወዳዳሪዎች ማኅበረሰቡ ተቀባይነት የላቸውም የሚላቸውን እሴቶችን እየተገዳደሩት ይገኛሉ።
ከመንግሥታዊው የንግድ እና ምጣኔ ሃብት ኮሌጅ የተመረቀችው ኤሪካ ምንም ዓይነት ስህተት እንዳልሰራች ትናገራለች።
“ፓኪስታንን በዓለም አቀፍ መድረክ በመወከል የጣስኩት ምንም አይነት ሕግ የለም። አንዳንድ አመለካከቶችን ለማስወገድ የተቻለኝን ጥረት እያደረግኩ ነው” ስትልም ታስረዳለች።