ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአውሮፓ የነበረኝን ሥራ አጠናቅቂያለሁ አለ
ለሳዑዲ አረቢያው ክለብ ፊርማውን ያኖረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአውሮፓ የነበረኝ የክለብ ጨዋታ አብቅቶለታል አለ።
ሮናልዶ ከብዙ እሰጣ ገባ በኋላ ማንችስተር ዩናይትድን ተሰናብቶ በነጻ ዝውውር አል ናስር ክለብን መቀላቀሉ ይታወሳል።
ሮናልዶ በአውሮፓ የነበረኝ ሥራ ይጠናቀቅ እንጂ ወደ ሳዑዲው ክለብ ለመዘዋወር ከመወሰኔ በፊት ሌሎች ክለቦችን የመቀላቀል በርካታ ዕድል ነበረኝ ብሏል።
የ37 ዓመቱ የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን አምበል ሮናልዶ፥ ከብራዚል፣ አውስትራሊያ፣ አሜሪካ እና ከፖርቹጋል ክለቦች ጥሪ ቀርቦለት እንደነበረ ተናግሯል።
“ቃሌን ለዚህ ክለብ ነው የሰጠሁት። ሁሉንም ዋንጫ አንስቻለሁ። በአውሮፓ ላሉ ወሳኝ ክለቦች ተጫውቻለሁ አሁን ፈተናው በእሲያ ነው” ብሏል።
የአምስት ጊዜ የባሎን ዶር አሸናፊው ሮናልዶ ይህን ያለው የሳዑዲው ክለብ በደማቅ ሁኔታ በይፋ ሲያስተዋውቀው ነው።
ፖርቹጋላዊው በእግር ኳስ ተጫዋቾች ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ ደሞዝ እንደሚከፈለው ተገልጿል። እስከ አውሮፓውያኑ 2025 በሚቆየው ውል የሳዑዲው ክለብ ለሮናልዶ በዓመት 177 ሚሊዮን ፓዎንድ ለመክፈል ተስማምቷል።
ሮናልዶ ከክለቡ ጋር ስለገባው ውል ተጠይቆ፤ “ውሉ ልዩ ነው፤ እኔም ልዩ ተጫዋች ነኝ፤ ስለዚህ ይህ ለአኔ የተለየ ነገር አይደለም” ብሏል።
“ሊጉ በጣም ፉክክር ያለበት ነው፤ በርካታ ጨዋታዎችን ተመልክቻለሁ። አሰልጣኙ ዕድሉን ከሰጡኝ የመጫወት ተስፋ አለኝ። እግር ኳስ ለመጫወት ዝግጁ ነኝ።”
የአል ናስር አሰልጣኝ ሩዲ ጋርሺያ ሮናልዶን ማስፈረም ከክለባቸው አልፎ ለሳዑዲ አረቢያ መልካም ነገር ነው ብለዋል።
“በሕይወቴ፤ እንደ ክርስቲያኖ ሮናልዶ አይነት ለማሰልጠን ቀላል የሆነ ተጫዋች አይቼ አላውቅም፤ ምክንያቱም ምንም የማስተምረው ነገር የለም” ብለዋል ፈረንሳይዊው አሰልጣኝ።
“ዓላማዬ ክርስቲያኖን ደስተኛ ማድረግ ነው። በአል ናስር መጫወት እንዲያስደስተው እና ከአል ናስር ጋር እንዲያሸንፍ ነው” ሲሉ አሰልጣኙ ጨምረው ተናግረዋል።