ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኦባሳንጆ በናይጄሪያ ከሚካሄደው ምርጫ ጋር በተያያዘ በሰጡት አስተያየት ውዝግብ ውስጥ ገቡ
የናይጄሪያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በአገራቸው በቅርቡ ከሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ፖለቲካዊ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።
በቀጣዩ የካቲት ወር በናይጄሪያ ውስጥ በሚካሄደው እና ከባድ ፉክክር ይደረግበታል በተባለው ምርጫ ላይ ኦባሳንጆ ዋነኛውን የተቃዋሚ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩን በመደገፋቸው ነው አወዛጋቢ የሆኑት።
በናይጄሪያ የተቃዋሚው ሌበር ፓርቲ መሪ እና በምርጫው ያሸንፋሉ ተብለው የሚጠበቁት ፒተር ኦቢ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ ድጋፍ አግኝተዋል።
ኦባሳንጆ አዲሱን ዓመት አስታከው ባስተላላፉት መልዕክት ላይ ነው ለአንደኛው ዕጩ ድጋፋቸውን የገለጹት።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ችግር የገጠማቸው ለተቃዋሚው ፓርቲ ዕጩ ድጋፋቸውን ሲገልጹ በተጠቀሟቸው ቃላት ምክንያት ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት እና ከሌሎቹ ዕጩዎች ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
ኦባሳንጆ የተቃወሚ ፓርቲው ዕጩ እሳቸው የቀረጿቸው/ያሰለጠኗቸው መሆናቸውን በመግለጽ፣ በዚህም ምክንያት ከሌሎቹ ዕጩዎች የበለጡ መሆናቸውን መግለጻቸው ነው ቁጣን የቀሰቀሰው።
በተጨማሪም አገራቸው ናይጄሪያ የምትገኝበትን አጠቃላይ ሁኔታ “ከድጡ ወደ ማጡ እና ከተራራ ጫፍ ወደ ሸለቆ” የመውረድ ያህል ነው በማለት የለውን አስተዳደር ተችተዋል።
የኦባሳንጆን ንግግር ተከትሎ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ ጽህፈት ቤት ቁጣ ያዘለ ምላሽ ሰጥቷል። በዚህም የቀድሞው ፕሬዝዳንት “የተሰማቸውን የቅናት ስሜት” አንጸባርቀዋል በማለት “የናይጄሪያ ዴሞክራሲ ጨለማ ጊዚያት” ማሳያ ናቸው ሲል ኦባሳንጆን ተችቷል።
ጨምሮም ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ “ናይጄሪያን ካስተዳደሩት መሪዎች ሁሉ የበለጡ እና ከእሳቸው የተሻለ መሪ አይመጣም ብለው የሚያስቡ ናቸው” በማለት ከፕሬዝዳንቱ ረዳት ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ ቁጣውን አንጸባርቋል።
ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በአሁኑ ወቅት ዋነኛው ተቃዋሚ የሆነው ፒዲፒ ፓርቲ መሪ በመሆን ከ1999 አስከ 2007 (እአአ) የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ነበሩ።
ኦባሳንጆ ድጋፋቸውን የገለጹላቸው ዕጩ ፒተር ኦቢ በፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ዋነኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ ከተባሉት መካከል አንዱ ናቸው። ሌሎቹ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ኤፒሲ ዕጩ ቦላ አህመድ ቲኑቡ እና የሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ፐዲፒ ዕጩ የሆኑት አቡባካር አቲኩ ናቸው።
የገዢው ፓርቲ ዕጩ ቦላ አህመድ ቲኑቡ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ኦባሳንጆ ለተቀናቃኛቸው ከሰጡት ድጋፍ አንጻር በሰጠው ምላሽ “በእሳቸው ንግግር ተወካያችን ጭንቀት ውስጥ አይገባም” በማለት የቀድሞውን መሪ አስተያየት አጣጥሎታል።
በተጨማሪም ሌላኛው ተፎካካሪ የአቡባካር አቲኩ የምርጫ ቡድንም ኦባሳንጆ “ምንም ያህል ከፍ ያለ ዝና ቢኖራቸውም፣ እሳቸው ለአንድ ዕጩ የሚሰጡት ድጋፍ በምርጫው ድልን የሚያስገኝ አይደለም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
የናይጄሪያ አጠቃላይ ምርጫ ሊካሄድ አንድ ወር ያህል በቀረበት በአሁኑ ጊዜ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ተፎካካሪዎች የሚያካሂዱትን የምርጫ ዘመቻ በከፍተኛ ደረጃ አጧጡፈውታል።