ኢላን መስክ ኤክስን በነፃ መጠቀም ሊቀር እንደሆነ ጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢላን መስክ ተጠቃሚዎች ዘንድሮ ኤክስ ተብሎ የሚጠራው የቀድሞውን ትዊተር ለመጠቀም ወርሐዊ ክፍያ ሊከፍሉ እንደሚችሉ ጠቆም አድርጓል።
ከእስራኤሉ ፕሬዝደንት ቤንያሚን ኔታኒያሁ ጋር ውይይት የነበረው ቢሊየነሩ ተጠቃሚዎች ማስከፈል ሐሰተኛ ገፆችን ለማጥፋት ብቸኛው አማራጭ ነው ብሏል።
“ቀጣይ ሐሳባችን ተጠቃሚዎች አነስተኛ ወርሐዊ ክፍያ እንዲከፍሉ ማድረግ ነው” ይላል የቴስላ እና ስፔስኤክስ አለቃ።
ቢቢሲ ስለክፍያው አስተያየት ለማግኘት ለኤክስ ጥያቄ ቢልክም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
ባለሐብቱ የሰጠው አስተያያት እንዲሁ በደፈናው ይሁን አሊያም የታሰበበት የድርጅቱ ዕቅድ በውል አልታወቀም።
ነገር ግን መስክ ለረዥም ጊዜ ሐሰተኛ ገፆችን ከማሕበራዊ ሚድያው ለማጥፋት ያለው አማራጭ ተጠቃሚዎችን ማስከፈል ነው የሚል አስተያየት ሲሰጥ ይደመጣል።
ባለፈው ዓመት ትዊተርን በረብጣ ዶላር የገዛው መስክ ለበርካታ አገልግሎቶች ክፍያ የሚጠይቅ ኤክስ ፕሪሚዬም የተሰኘ ማዕቀፍ አዘጋጅቷል።
የዚህ ማዕቀፍ ተጠቃሚዎች ከሌላው ተጠቃሚ በተለየ ረዥም ፅሑፍ መለጠፍ ይችላሉ፤ አልፎም የለጠፉት መልዕክት በብዙዎች እንዲታይላቸው ይሆናል።
ነገር ግን አሁንም ቢሆንም በርካቶች ኤክስን በነፃ ይጠቀማሉ።
ምንም እንኳ ኩባንያው ተጠቃሚዎችን ለማስከፈል ቢዳዳም መስክ ግን የሚለው ዋነኛ ዓላማው ሐሰተኛ ገፆችን መግታት ነው።
አሜሪካ ያሉ ኤክስ ፕሪሚዬም ተጠቃሚዎች በየወሩ 8 ዶላር ይከፍላሉ። ክፍያው ከሃገር ሃገር ይለያያል።
የዓለማችን ሐብታሙ ሰው ኤክስ ተጠቃሚዎች እንዴት በትንሽ ገንዘብ ማሕበራዊ ሚድያውን መገልገል ይችላሉ የሚሉ አማራጮችን እየተመለከተ እንደሆነ ይናገራል።
“በአነስተኛ ገንዘብ መጠቀም የሚቻልበትን መንገድ እናመቻቻለን። በጣም ትንሽ ገንዘብ ነው የምንጠይቀው” ይላል።
“ይህ ረዘም ያለ ውይይት የሚጠይቅ ነው። ነገር ግን እንደኔ ቢሆን ይህ ሐሰተኛ ገፆችን ለመጠራረግ ብቸኛው አማራጭ ነው” ሲል ያክላል።
ነገር ግን ተጠቃሚዎች ወርሐዊ ክፍያ እንዲከፍሉ መጠየቅ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ኤክስን መጠቀም እንዲያቆሙ ሊያስገድድ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ይህ ደግሞ ኤክስ ላይ ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ድርጅቶችም እንዲለቁ ምክንያት የመሆን ዕድል አለው።
በአሁኑ ወቅት የኤክስ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ከማስታወቂያ የሚገኘው ገንዘብ ነው።
ከእስራኤሉ ፕሬዝደንት ጋር ውይይት ያደረገው መስክ ኤክስ ላይ ስለሚስተዋለው ፀረ-ሴማዊነትም አውርቷል።
'አንታይ ዲፋማሽን ሊግ' የተሰኘው ተቋም መስክ ፀረ-ሴማዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶችን አልተቆጣጠረም የሚል ወቀሳ ይሰነዝራል።
ድርጅቱ በመግለጫው ኢላን መስክ ፀረ-ሴማዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶችን “ያጋራል እንዲሁም ያበረታታል” የሚል ትችት አሰምቷል።
በያዝነው የአውሮፓውያኑ ወር መባቻ መስክ “የኤክስን ስም ለማጥራት” ድርጅቱን እንደሚከስ ተናግሮ ነበር።
ኔታኒያሁ በንግግር ነፃነት እና በይዘት ቁጥጥር መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ ከባድ እንደሆነ አምነው ነገር ግን መስክ ይህን ሚዛን ማስተካከል አለበት ብለዋል።












