ቻይና በደኅንነት ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ወደ ሩሲያ መልዕክተኛ ላከች

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
ሞስኮ በዩክሬን እያካሄደችው ባለው ጦርነት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እየፈለገች ባለበት ወቅት የቻይና ከፍተኛ ዲፕሎማት ዋንግ ይ በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ወደ ሩሲያ አቀኑ።
የሞስኮ የቅርብ ወዳጅ የሆነችው ቤይጂንግ በዩክሬን ጦርነት ሩሲያን በተዘዋዋሪ ረድታለች በሚል ትከሰሳለች። ይሁን እንጂ ቤይጂንግ ክሱን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋለች።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ይ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ሩሲያ ያቀኑት ቭላድሚር ፑቲን ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ተገናኝተው የጦር መሣሪያ ስምምነት እንዳደረጉ ከተነገረ በኋላ ነው።
የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን የዲፕሎማቱ ጉዞ ፕሬዚደንት ፑቲን በቅርቡ ለሚያደርጉት ታሪካዊው የቤይጂንግ ጉብኝት መሠረት እንደሚጥል ዘግበዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ፑቲን ከቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግ ጋር እንደሚገናኙ የተናገሩ ሲሆን መቼ እንደሆነ ግን አልገለጹም።
ፑቲን በዩክሬን ተፈፅሟል በተባለ የጦር ወንጀል ምክንያት ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መጋቢት ወር ላይ የእስር ማዘዣ ካወጣባቸው በኋላ የውጭ አገር ጉዞ አላደረጉም።
ለመጨረሻ ጊዜ ከአገራቸው ውጭ የተጓዙት እንደ አውሮፓውያኑ ታኅሳስ 2022 ሲሆን የሄዱትም ወደ ቤላሩስና ኪርጊስታን ነበር።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ዋንግ በሩሲያ ለአራት ቀናት የሚቆዩ ሲሆን በደኅንነት ጉዳዮች ላይ ይነጋገራሉ።
የሩሲያ የዜና ወኪል ታስም መልዕክተኛው ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር እንደሚገናኙ ገልጾ፣ ዋነኛ መነጋገሪያቸው የዩክሬን ጦርነት እንደሚሆን ክሬምሊንን ጠቅሶ ዘግቧል።
ከዚህም በተጨማሪ በእሲያ እና በፓስፊክ ቀጠና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ኃይል እና መሠረተ ልማት መስፋፋት ላይ እንዲሁም እንደ ተባበሩት መንግሥታት ካሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠንከር እንደሚወያዩም ገልጿል።
ከፍተኛ ዲፕሎማቱ ወደ ሞስኮ ያቀኑት ፑቲን እና ኪም ከተገናኙ ከቀናት በኋላ ነው።
አሜሪካ የሁለቱን መሪዎች ግንኙነት በጦር መሣሪያ ሽያጭ ላይ ለመወያየት ያለመ ነበር ብላለች።
ሞስኮ በዩክሬን ጦርነት የጦር መሣሪያ እና ጥይቶች እጥረት አጋጥሟታል ተብሎ ይታሰባል።
ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ግን የተነጋገሩት በጦር ትብብር ላይ እና ለፒዮንግያንግ የሳተላይት ፕሮግራም ድጋፍን በተመለከተ ነው ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት የኪምን ጉብኝት አስመልክቶ መረጃ እንዲሰጥ የተጠየቀው የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “በሁለቱ አገራት መካከል ስላለ ጉዳይ ነበር” ሲል ዝርዝር አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ሆኖም አንዳንድ ተንታኞች ቤይጂንግ ከሁለቱ አገራት ጋር ያላትን የጠበቀ ግንኙነት ግምት ውስጥ በማስገባት የሰሜን ኮሪያ እና የሩሲያ የጋራ ትብብር የተካሄደው በቻይና እውቅና ወይም ፈቃድ ነው ይላሉ።
ሦስቱ አገራት ያላቸው ግንኙነትም ከሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም እና ለምዕራቡ ዓለም ካላቸው እምነት ማጣት ያለፈ እንደሆነም ይነገራል።
ቤይጂንግ የፒዮንግያንግ የኢኮኖሚ መሠረት ስትሆን ባለፉት ዓመታትም የሩሲያን የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ግዢ በመጨመር ለሞስኮም የኢኮኖሚ መሠረት ሆናለች።












