ሁለት የአሜሪካ ባሕር ኃይል አባላት ለቻይና በመሰለል ተከሰሱ

ዩኤስኤስ ኤሴክስ የተሰኘችው የባሕር ኃይል መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዩኤስኤስ ኤሴክስ የተሰኘችው የባሕር ኃይል መርከብ

ሁለት የአሜሪካ ባሕር ኃይል አባላት ለቻይና ሚስጥራዊ መረጃ በማቀበል ካሊፈኖርኒያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው ክስ ተመሠረተባቸው።

በቅርቡ ዜግነቱን ወደ አሜሪካዊ የቀየረ የ22 ዓመቱ ጂንቻዎ ዌይ፤ ለቻይና ሰላይ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለመስጠር ሲያሴር ነበር ተብሎ ተከሷል።

ሌላኛው መኮንን የ26 ዓመቱ ዌንሄንግ ዣዎ ሚስጥራዊ ፎቶዎችና ቪድዮዎች አሳልፎ ለመስጠት ገንዘብ ተቀብሏል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ሁለቱ የባሕር ኃይል አባላት መረጃውን ለማቀበል ተመሳሳይ ቻይናዊ ሰላይ ጋር ግንኙነት ስለመፍጠራቸው ግልጽ አልሆነም።

ሁለቱ የባሕር ኃይል አባላት ባለፈው ረቡዕ ካሊፎርኒያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ ዌይ የተያዘው ሳን ዲየጎ ወደሚገኘው ቢሮው እያቀና ነበር።

ዐቃቤ ሕግ ሐሙስ ዕለት ሳን ዲየጎ ውስጥ ሁለቱ ሰዎች መከሰሳቸውን ይፋ አድርጓል።

ዩኤስኤስ ኤሴክስ ለተሰኘችው ጦር መርከብ የሞተር ክፍል ውስጥ ሰራተኛ ሆኖ ያገለግል የነበረው ዌይ በሥራው ምክንያት ስለመርከቧ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ያገኝ ነበር።

የአሜሪካ ዜግነት ሊወስድ ዝግጅት ላይ እያለ ነው በፈረንጆቹ 2022 የካቲት አንድ ቻይናዊ ሰላይ ቀርቦ ያናገረው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፓትሪክ ዌይ በተሰኘ ሌላኛው ስሙ የሚታወቀው የአሜሪካ ባሕር ኃይል አባል ከቻይናዊው ሰላይ ገንዘብ እንደተቀበለ ተጠርጥሯል።

የመርከቧ ውስጣዊ ክፍል ቴክኒካዊ መረጃዎችን በፎቶዎችና ቪድዮዎች አድርጎ ሰጥቶ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ከቻይናዊው እንደተቀበለ ክሱ ያሳያል።

የፍትሕ ክፍል ባለሥልጣናት እንደሚሉት ዌይ ለቻይናዊው ሰላይ ሥልጠና ላይ ስለሚገኙ የአሜሪካ ባሕር ኃይል አባላትም መረጃ ሰጥቷል።

“አንደ ወታደር አሊያም የባሕር ኃይል አባል ከሃገር ይልቅ ገንዘብ አስበልጦ ብሔራዊ መረጃ አሳልፎ በመስጠት ክህደት ሲፈፅም፤ እኛ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት አለብን” ብለዋል። የአሜሪካ አቃቤ ሕግ ራንዲ ግሮስማን።

ቻይና እስካሁን ስለተጠረጠረው ድርጊት የምታውቀው ነገር እንደሌለ ነው የምትናገረው።

ቶማስ ዣዎ በተሰኘ ስሙ የሚታወቀው ሌላኛው ተጠርጣሪ ሎስ አንጀለስ በሚገኘው የባሕር ኃይል ያገልግል የነበረ ነው።

ዣዎ በ2021 ኢንቨስትመንት ላይ ነኝ በሚል ጥናት አድራጊ መስሎ አንድ ቻይናዊ ሰላይ እንደቀረበው ተነግሯል።

ቻይናዊው ሰላይ ለዣዎ 15 ሺህ ዶላር በመክፈል ፎቶዎችና ቪድዮዎች እንዲሁ በጃፓኗ ኦኪዋና ስለሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል ራዳር የሚጠቁሙ መረጃዎች እንደተቀበለ ተሰምቷል።

ተጠርጣሪዎቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 20 ዓመት ድረስ የሚቆይ እሥር ይጠብቃቸዋል።

ባለሥልጣናት እንደሚሉት የሁለቱ ተጠርጣሪዎች የሃገር ክህደት ተግባር ቻይና የአሜሪካን ሚስጥራዊ መረጃዎች ለማግኘት የምታደርገው ጥረት አካል ነው።

በያዝነው ዓመት በአሜሪካ ሰማይ ላይ ይበር የነበረ አንድ ፊኛ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ያሻከረው ሲሆን ኋላ ላይ ግን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ግዙፉ ፊኛ ምንም ዓይነት መረጃ አልወሰደም ብለዋል።

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የሚወክላቸው ጠበቃ ስለመቅጠራቸው እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።