ሰሜን ኮሪያ ያለ ፈቃድ ወደ አገሯ በገባው አሜሪካዊ ወታደር ዙሪያ ምላሽ ሰጠች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሰሜን ኮሪያ ድንበር ተሻግሮ ያለ ፈቃድ ወደ አገሯ በገባው አሜሪካዊው ወታደር ትራቪስ ኪንግ ዙሪያ ምላሽ መስጠቷን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕዝ አስታወቀ።
አሜሪካ ወታደሩ የት እንደሚገኝ መረጃ ሰሜን ኮሪያ እንድትሰጣት መጠየቋንም ተከትሎ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ምላሽ የተሰጠው።
የ23 አመቱ አሜሪካዊ ወታደር በደቡብ ኮሪያ በጉብኝት ላይ የነበረ ሲሆን ያለ ፈቃድም ድንበር አቋርጦም ወደ ሰሜን ኮሪያ ግዛት ዘልቆ የገባው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እዝ “ወታደሩን ወደ አሜሪካ ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ጣልቃ ላለመግባት” በሚል ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
ሆኖም ሰሜን ኮሪያ ወታደሩን በተመለከተ ምላሽ መስጠቷ ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን የሚያሳይ ነው ተብሏል።
በሰሜንና በደቡብ ኮሪያ ግዛቶች ድንበር መካከል ከወታደራዊ ቁጥጥር ውጭ የሆነውን ቀጠና የሚቆጣጠረው የተባበሩት መንግሥታት ኮማንድ ዕዝ ወታደሩ ያለበት ሁኔታ ለማወቅም በቀጥታ የስልክ መስመሩን በመጠቀም የሰሜን ኮሪያ ጦር ጋር ደውሎ እንደነበር ተገልጿል።
ሰሜን ኮሪያ ወታደሩን በተመለከተ የቀረበላትን ጥያቄ የተቀበለች ሲሆን የአሜሪካ ወታደር በቁጥጥራቸው ስር ስለመሆኑ በማረጋገጥ ምላሽ ሲሰጡ የመጀመሪያው ነው።
ሰሜን ኮሪያ አሜሪካዊው ወታደር በቁጥጥሯ ስር ስር ስለመሆኑ ይፋዊ መግለጫ አልሰጠችም።
አሜሪካዊው ወታደር ትራቪስ ኪንግ የሰሜን ኮሪያን ድንበር ዘልቆ ከመግባቱ በፊት በደቡብ ኮሪያ በጥቃት ክስ ለሁለት ወራት በእስር ቤት አሳልፏል። የተለቀውም ከወር ገደማ በፊት ነው።
ወታደሩ ከነበረበት ደቡብ ኮሪያ በስነ ምግባር ምክንያት ወደ አሜሪካ ሊመለስ በዝግጅት ላይ እያለ ነው ይህ ሁኔታ የገጠመው።
ትራቪስ ወደ አሜሪካ ሊመለስ የበረራው ጊዜ በቀረበበት ወቅት ባልታወቀ ሁኔታ ቀድሞ ወዳዘጋጀው የድንበር አካባቢ ጉብኝት ተጓዘ።
ይህን ያደረገበት ምክንያት ባይታወቅም የአሜሪካ የጦር ባለስልጣናት ግን ወታደሩ በፈቃዱ ድንበሩን እንደተሻገረ ተናግረዋል።












