በፕሬዝዳንት ማክሮን ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ ነበር የተባሉ ቀኝ አክራሪዎች ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሲያሴሩ ነበር የተባሉ ሦስት የቀኝ አክራሪ ቡድን አባላት ጥፋተኛ ተብለው ተፈረደባቸው።
ግለሰቦቹ በ2018 (እአአ) ፕሬዝዳንቱ ይገኙበታል በተባለው የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት መታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ በቢላ ጥቃት ሊፈጽሙባቸው አቅደው ነበር ተብሏል።
የተከሳሾቹ ጠበቆች ደንበኞቻቸው ግልጽ ዕቅድ የሌላቸው፣ ግራ የተጋቡ ጽንፈኞች ናቸው በማለት ለፍረድ ቤቱ ተናግረዋል።
የፈረንሳይ ዐቃቤ ሕግ ግን ጥቃቱን ሊፈጽሙ ሲያሴሩ የነበሩት ጽንፈኛ ግለሰቦች በኃይል መንግሥትን የመገልበጥም ፍላጎት ነበራቸው ሲል ከሷቸዋል።
ጉዳያቸውን ሲመለከት የነበረው ፍርድ ቤት ሦስቱ ተከሳሾች የሽብር ድርጊት ለመፈጸም በመዘጋጀት ሴራ ጥፋተኛ ሆነው እንዳገኛቸው ገልጿል።
በዚህም ከተከሳሾቹ መካከል የ66 ዓመቱ ጃን ፒየር ቡየር ከፍተኛው ቅጣት ተበይኖበታል። ወንጀሉ አስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስር የሚያስቀጣ ቢሆንም፣ ግለሰቡ በአንድ ዓመት ገደብ የአራት ዓመት አስር ተፈርዶበታል።
ሌሎቹ ሁለት ተከሳሾች ግን የአጭር ጊዜ የእስር ቅጣት ብቻ ተላልፎባቸዋል።
ሌላ አራተኛ ሰው ደግሞ የጦር መሳሪያ በመያዝ በቀረበበት ክስ በገደብ የስድስት ወራት እስር ተፈርዶበታል።
ሁሉም ተከሳሾች የተያዙት በፈረንሳይ ምሥራቃዊ ክፍል በምትገኘው ሞዜል ክልል ውስጥ ነው። ፖሊስ በቦየር መኪና ውስጥ ኮማንዶዎች የሚጠቀሙበት አይነት ቢላ እና የወታደሮች ጃኬት ያገኘ ሲሆን፣ እንዲሁም ቤቱ ውስጥም ሽጉጦች ተገኝተዋል።
ሌሎች ዘጠኝ የጽንፈኛ የቡድኑ አባለት ከቀረበባቸው ክስ በነጻ ተሰናብተዋል።
የቡድኑ አባላት በኢንተርኔት ላይ በተደረጉ የዘረኝነት ውይይቶች ላይ ስለስደት፣ የእርስ በርስ ጦርነት ስጋት እንዳላቸው እና ለፕሬዝዳንት ማክሮን ስላላቸው ጥላቻ የተናገሩት በፍርድ ሂደቱ ወቅት በችሎቱ ተደምጧል።
በአንደኛው ውይይት ላይ ሦስት ልጆች ያሏት እናት፣ በ500 የሩሲያ ወታደሮች በመታገዝ በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቤተ መንግሥት ላይ ጥቃት መሰንዘር ስለሚቻልበት ሁኔታ ስትናገር ተደምጣላች።
በተጨማሪም ቡድኑ በመስጂዶች እና በስደተኞች ላይ ጥቃቶችን ለመፈጸም በማሴር እንደተጠረጠሩ ተገልጿል።
አንዲት የ55 ዓመት ተከሳሽ ስለሰነዘረችው ሙስሊሞችን የማገት እና የማቃጠል ሃሳቧን በተመለከተ በፍርድ ቤቱ ተጠይቃ “ተበሳጭቼ እና ተቆጥቼ ስለነበረ፣ ይህንን ተናግሬ ሊሆን ይችላል” ብላ መልሳለች።
ዋናው ዐቃቤ ሕግ ጽንፈኛው ቡድን “የአመጽ ድርጊቶች መፈልፈያ” ነው በማለት፣ አመለካከታቸውም “ከተለመደው ወጣ ያለ” እና “የሚደቅኑት አደጋም ተጨባጭ ነው” በማለት ከሰዋል።
የተከሳሾቹ ጠበቃ ግን ቡድኑ አባላት ትኩረት ያላገኙ እና ከገጠር አካባቢ የመጡ የፀረ መንግሥቱ የቢጫ ጃኬት ለባሾቹ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች ናቸው ብሏል። ጨምሮም በቡድኑ አባላት “የጥላቻ” ንግግር መንጸባረቁን ተቀብሎ፣ ነገር ግን ይህ ስሜት በገጠማቸው ማኅበራዊ ችግር ምክንያት የተፈጠረ ነው ብሏል።
ይህ ጽንፈኛ ቡድን የተመሠረተው ከስድስት ዓመት በፊት ጂሃዲስቶች አማካይነት እዚያው ፈረንሳይ ውስጥ በቻርሊ ሄብዶ መጽሔት እና የባታክላን የኮንሰርት አዳራሽን ጨምሮ በሌሎች ስፍራዎች ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነበር።












