አርሰናል ወደ አሸናፊነት ይመለስ ይሆን? የተቀዛቀዘው ኒውካስልሰ እንዴት ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
24ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ነገ ቅዳሜ ቀጥለው ይካሄዳሉ።
የዚህ ሳምንት ጨዋታ የሊጉን መሪነት በማንችስተር ሲቲ የተነጠቁትን መድፈኖች ወደ ቪላ ይወስዳል።
የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን አሁንም አርሰናል የዋንጫ ተፎካካሪ ነው ብዬ አምናለሁ ያለ ሲሆን፤ መድፈኞቹ “ይህን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ አለባቸው” ብሏል።
ሱቶን የነገው ጨዋታ በአርሰናል ደጋፊዎች ተጠልተው ከኢሚሬትስ ለተባረሩት ለቀድሞ የመድፈኞች አሰልጣኝ የመበቀያ መልካም አጋጣሚ ነው ይላል።
ቅዳሜ

አስተን ቪላ ከ አርሰናል
ከሰዓት 9፡30 ሲል አስተን ቪላ መድፈኞቹን በቪላ ፓርክ ያስተናግዳል። ሱቶን ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል ለራቃቸው መድፈኞቹ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ እጅግ ወሳኝ ነው ይላል።
መድፈኞቹ ከሁለት ቀናት በፊት በሲቲ የተሸነፉት መጥፎ በመጫወታቸው አይደለም የሚለው ሱቶች፤ ከቪላ ጋር ምንም አይነት ስልት ይዘው ይግቡ ማሸነፍ ግን ግድ ይላቸዋል ይላል።
በወጣት የተሞላው የመድፈኞቹ ቡድን ድል እየራቀው በሄደ ቁጥር ጫና ውስጥ እንዳይገባ ከተፈለገ ቡድኑ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርበታል።
ግምት፡ ቪላ 1 - 2 አርሰናል
ብሬንትፎርድ ከ ክርስታል ፓላስ
አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ስድስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ይከናወናሉ።
ምስጋና አርሰናል ላይ ላስቆጠሯት አጨቃጫቂ ጎል ይሁንና ብሬንትፎርዶች በሊጉ በ10 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ግስጋሴያቸውን እንዳስጠበቁ ናቸው።
ብሬንትፎርዶች በኢሚሬትስ በነበራቸው ጨዋታ የማሸነፍ ዕድል ነበራቸው የሚለው ሱቶን፤ ከፓላስ ጠንካራ ፉክክር ቢጠብቃቸውም ጨዋታውን በድል ይወጣሉ ይላል።
ግምት፡ ብሬንትፎርድ 2 - 0 ክርስታል ፓላስ
ብራይተን ከ ፉልሃም
ሱቶን ይህን ጨዋታ አዝናኝ እንደሚሆን ይጠብቃል። በሊጉ ጅማሪ ወቅት ብራይተን እና ፉልሃም 6ኛ እና 7ኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጡ ይችላሉ ብሎ ማን ጠብቆ ነበር? ሲል የሚጠይቀው ሱቶን፤ ሁለቱም ቡድኖች አሁን የሚፋለሙት በአውሮፓ መድረክ ለመጫወነት ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።
ከፓላስ ጋር በነበራቸው ጨዋታ በዳኝነት ስህተት ወሳኝ ሦስት ነጥብ የተከለከሉት ብራይተኖች ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ እንደሚሰበስቡ ግምቱን ሰጥቷል።
ግምት፡ ብራይተን 3 - 1 ፉልሃም

ቼልሲ ከ ሳውዝሃምፕተን
የቼልሲው አሰልጣኝ ግርሃም ፖተር ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ግዴታቸው ነው ይላል ሱቶን። አለዚያ ግን ከፍተኛ ጫና ላይ ይወድቃሉ። ቼልሲ በሊጉ ድል ከቀናው ሳምንታት አልፈዋል። በቻምፒየንስ ሊጉም በዶርትመንድ ተሸንፏል።
ባለፉት ጨዋታዎች ነጥብ ለመጣላቸው የተለያዩ ምክንያቶች ሲደረደሩ ቆይተዋል የሚለው ሱቶን በሊጉ ግርጌ ላይ የተቀመጠውን ሳውዝሃምፕተንን ላለማሸነፍ ግን ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም።
ግምት፡ ቼልሲ 2 - 0 ሳውዝሃምፕተን

ኤቨርተን ከ ሊድስ
ይህን ጨዋታ መገመት አዳጋች መሆኑን ሱቶን ያምናል። ምንም እንኳ ሊድሶች አሰልጣኝ አልባ ቢሆኑም ጥሩ ተስጥዖ ያላቸው አጥቂዎች አሏቸው ይላል።
ካለ ካልቨርት ሊውን ወደ ሜዳ የሚገቡት ኤቨርተኖች ደግሞ በጨዋታው ጎል ማስቆጠር ቀላል እንደማይሆንላቸው ይገምታል።
ግምት፡ ኤቨርተን 1 - 1 ሊድስ

ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ማንችስተር ሲቲ
ሲቲ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ የሚከብደው እንዳልሆነ ብዙዎች ሊገምቱ ይችላሉ ግን ለፔፕ ቀላል ጨዋታ ላይሆን ይችላል።
ፎረስቶች በሜዳቸው ከመስከረም ጀምሮ አለመሸነፋቸውን የሚያስታውሰው ሱቶን በጋርዲዮላ ቡድን ውስጥም ወሳኝ አጋጣሚዎች ወደ ዕድል የሚቀየሩ ተጫዋቾች አሉ ይላል።
በዚህም ሲቲ ይህን ጨዋታ አሸንፎ ፎረስቶች በሜዳቸው ያለመሸነፍ ግስጋሴያቸውን ያስቆማል ባይ ነው ሱቶን።
ግምት፡ ኖቲንግሃም ፎረስት 0 - 2 ማንችስተር ሲቲ

ዎልቭስ ከ በርንዝማውዝ
በርንዝማውዞች ባለፉት ጨዋታዎች በመከላከል ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ማድረግ ቢችሉም የሚገባቸውን ነጥብ ማግኘት አለመቻላቸው ለአስልጣኝ ጌሪ ኦ’ኒል የሚዋጥ ነገር አይደለም።
ዎልቭሶች ደግሞ በሁሉም የሜዳ ክፍል እንቅስቃሴያቸው አዎንታዊ ለውጥ እያሳዩ ነው። በ10 ተጫዋች ከመመራት ተነስተው ሳዝውሃምፕተንን ማሸነፋቸው የቡድን መነቃቃት እንደሚጨምርላቸው ሱቶን እምነቱ ነው።
ግምት፡ ዎልቭስ 1 - 0 በርንዝማውዝ

ኒውካስል ከ ሊቨርፑል
ሊቨርፑሎች ከኤቨርተን ጋር በነበራቸው ጨዋታ የድሮውን ሊቨርፑልን ማሳየት ችለዋል። ግን ይሄ ወደ ቀደም አቋማቸው ተመልሰዋል ማለት እንዳልሆነ ሱቶን ይገልጻል።
በቅጣት ብሩኖ ጉሜሬሽን የማያሰልፈው ኒውካስል በአንጻሩ ደግሞ ከበርንዝማውዝ በነበረው ጨዋታ አቅሙን እያጣ የመጣ ክለብ መስሏል።
በዚህ የውድድር ዓመት ኒውካስልን ማሸነፍ የቻለው ብቸኛው ቡድን ሊቨርፑል መሆኑን የሚገልጸው ሱቶን፤ የክሎፕ ልጆች ዳግም ማሸነፍ ቢያቅታቸው ነጥብ ተጋርተው ሊወጡ ይችላሉ ይላል።
ግምት፡ ኒውካስል 1 - 1 ሊቨርፑል

ማንችስተር ዩናይትድ ከ ሌስተር
ማንችስተር ዩናይትድ የሊጉ የዋንጫ ተፎካካሪ አይደለም በሚለው አቋሜ ብጸናም፤ ቀያይ ሴጣኞቹ ግን መጥፎ አቋም እያሳዩ እንኳ ጨዋታዎችን እያሸነፉ ይገኛሉ ብሏል።
በዩሮፓ ሊግ ከባርሴሎና 2 አቻ የተለያዩት ዩናይትዶች ይህን ጨዋታ እንዴት እንደሚወጡት እናያለን ይላል።
በቶተነእሃም ላይ ትልቅ ድል ለተቀናጀው ሌስተር የጄምስ ማዲሰን ወደ ቡድኑ መመለስ ሌላ ኃይል ነው ይላል ሱቶን።
ግምት፡ ማንችስተር ዩናይትድ 2 - 1 ሌስተር

ቶተነሃም ከ ዌስትሃም
ሲቲን አሸንፎ በቀጣዩ ጨዋታ ደግሞ በርካታ ጎል ተቆጥሮበት በሌስተር ስለሚሸነፈው ክለብ ምን መጠብቅ እንዳለበኝ አላውቅም ይላል ሱቶን።
ዌስትሃሞች ደግሞ ከቼልሲ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ምንም እንኳ ደካማ ቢሆኑም ነጥብ ተጋርተው መውጣታቸው ዕድለኛ ያደርጋቸዋል ይላል።
ግምት፡ ቶተነሃም 3 - 1 ዌስትሃም












