ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፓኪስታናዊው ጋዜጠኛ ኬንያ ውስጥ በተተኮሰበት ጥይት ተገደለ
እውቁ ፓኪስታናዊ ጋዜጠኛ ኬንያ ውስጥ መገደሉ ተሰማ።
የኬንያ ፖሊስ ፓኪስታናዊ ጋዜጠኛ አርሻድ ሻሪፍ እሁድ ምሽት የኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ አጎራባች በሆነችው ካጂያዶ ግዛት በተተኮሰበት ጥይት መገደሉን አስታውቋል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ብሩኖ ሺኦሶ፣ ከጋዜጠኛ ሻሪፍ ሞት ጀርባ ስላለው ሁኔታ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ግን ጋዜጠኛው በተሳሳተ ማንነት ከናይሮቢ ወደ ማጋዲ በሚወስደው መንገድ ላይ በተተኮሰበት ጥይት መገደሉን ዘግበዋል።
የጋዜጠኛ ሻሪፍ ባለቤት ጃቨሪያ ሲዲክ፣ ሰኞ ዕለት በትዊተር ገጿ ባሰፈረችው ጽሁፍ "ባለቤቴን፣ ጓደኛዬን እና የምወደውን ጋዜጠኛ አጣሁ" ስትል ሃዘኗን ገልጻለች።
ጋዜጠኛ ሻሪፍ የሚሰራቸው ሙስና ላይ ያነጣጠሩ ዘገባዎች እና በፓኪስታን ባለሥልጣናት ላይ በተደጋጋሚ የሚሰነዝረው ትችት ከባለሥልጣናት ጋር ግጭት ውስጥ ከቶታል።
ከመሞቱ በፊትም ሻሪፍ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ጋዜጠኞች የተካተቱበት እና በፓኪስታን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ያነጣጠረ በመንግሥት የሚደገፉ ወንጀለኛ ቡድኖችን የተመለከተ የምርመራ ዘገባ እየሰራ ነበር ተብሏል።
የፓኪስታን ፖሊስ፣ ጋዜጠኛ ሸሪፍ ከአንድ ተቃዋሚ አክቲቪስት ጋር ያደረገው አከራካሪ ቃለ ምልልስ ተከትሎ "በመንግሥት ላይ አመጽ ማነሳሳት" የሚል ክስ አቅርቦበት ነበር።
የፓኪስታን ፕሬዚደንት አሪፍ አልቪ በጋዜጠኛው ሞት የተሰማቸውን ሃዘን የገለጹ ሲሆን፣ “ የአርሻድ ሻሪፍ ሞት ለጋዜጠኝነት እና ለፓኪስታን ትልቅ እጦት ነው። ነፍሱ በሰላም ትረፍ! ቤተሰቦቹን ጨምሮ ወዳጆቹ ይህንን ሃዘን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ያድላቸው “ ብለዋል።