ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተደራራቢው የኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ጭቆና
በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ዕድላዊት የጋዜጠኝነትን የሕይወት መንገድ አንድ ብላ ከጀመረች አንድ ዓመት እንኳ አልተቆጠረም።
ገና በጅማሮዋ ላይ ነበር ባልጠበቀችው አጋጣሚ ጾታን መሰረት ያደረገ የጥቃት ሙከራ የገጠማት።
[ዕድላዊትን ጨምሮ በዚህ ዘገባ ታሪካቸውን ያካፈሉ ሁሉም ሴት ጋዜጠኞች ማንነታቸውን ለመግለጽ ስላልፈቀዱ ስማቸው እና መለያዎቻቸው ተቀይረዋል]
ከከተማ ውጪ ላለ አንድ ሥራ ወደ ክፍለ ሃገር ማምራቷን የምትናገረው ዕድላዊት፤ ቀን ላይ የሰበሰቡትን መረጃዎች መቀያየር እና ምሽት ላይ የአርትዎት ሥራ መስረት በሂደቱም ካሜራዎቻቸውን መዋዋስ የተለመደ በመሆኑ ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ የተንኳኳውን የክፍሏን በር ለመክፈት አላመነታችም።
ነገር ግን በአልኮል መጠጥ ጫና ውስጥ ሆኖ ወደ ክፍሏ ገፍቶ የገባው ሌላ ጋዜጠኛ በሩን በመቆለፍ ጥቃት ለመፈጸም ትግል እንደገጠማት ትናገራለች።
"የገባሁበት ሁኔታ ስለገባኝ ቀስ ብዬ አረጋግቼው ከክፍሌ እንዲወጣ አደረኩኝ'' ስትል ትናገራለች። ነገር ግን ያለ ፈቃዷ መሳምን ጨምሮ ትግል ገጥሟት ነበር።
በመገናኛ ብዙኃን ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የሰራችው ሃናም ብትሆን የቃላት ጥቃቶች ከሥራ ባልደረቦቿ ጀምሮ ለሥራ ከምታገኛቸው ሰዎች እንዳጋጠማት፤ አሁንም እንደሚገጥማት ትናገራለች።
መረጃ ለማግኘት አበክራ እና ደጋግማ መወትወቷን ከተመለከቱ ደግሞ "አንቺማ በዚህ አይነት ቆመሽ ነው የምትቀሪው" የሚሉ አስተያየቶችን መቀበሏን ትናገራለች።
በርግጥ ይህ በመላው ዓለም ከሚገኙ ሴት ጋዜጠኞች 41 በመቶ የሚሆኑትን የሚያጋጥም ፈተና ነው።
የዓለም አቀፉ የዜና አታሚዎች ማኅበር በያዝነው ዓመት አጋማሽ ላይ ይፋ ባደረገው ጥናቱ ላይ ከተሳተፉ ሴት ጋዜጠኞች ውስጥ 41 በመቶው በሥራ ቦታቸው ላይ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ጥቃቶች አጋጥመውናል ብለዋል።
ነገር ግን የእነዚህ ጥቃቶች ሰለባ የሚሆኑት ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ 13 በመቶ የሚሆኑ ወንዶችም ጾታዊ ጥቃቶች እንደሚያጋጥማቸው፣ ይህም በአጠቃላይ 30 በመቶ የሚሆን ማንኛውም ጋዜጠኛ ለጥቃቱ የተጋለጠ ነው ሲልም ጥናቱ አመላክቷል።
ከቃላት የሚጀምሩት ጥቃቶች
ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ ሲባል ያነጋገራቸው ሴት ጋዜጠኞች እንደሚሉት በተለይም የጋዜጠኝነት ሥራ በጀመሩባቸው የመጀመሪያ ጊዜያት የተለያዩ ማባበያዎችን በማቅረብ፤ ባስ ሲልም ማስፈራሪያ እና ጉልበት በመጠቀም አካላዊ ጥቃቶች በሥራ ቦታዎቻቸው አጋጥሟቸዋል።
ነገር ግን ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሠራተኞችን የሚያስተዳድረው የኢፌድሪ የአሰሪ እና ሠራተኛ ሕጉ ይህንን በጥብቅ ይከለክላል።
የሕጉ የትርጓሜ ክፍሎች ወሲባዊ ትንኮሳን በንግግር፣ በምልክት ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ አንድ ሰው ከፈቃዱ ውጪ ለወሲባዊ ተግባር ፈቃደኛ እንዲሆን ማባበል፣ መገፋፋት፣ ተፅዕኖ ማሳደር ማለት እንደሆነ ይደነግጋል።
እነዚህ ትንኮሳዎች ኃይል ሲቀላቀልባቸው ወይም የድርጊቱ ሙከራ ወሲባዊ ጥቃት እንደሚሆንም ያክላል።
ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በመገናኛ ብዙኃን ውስጥ ስር መስደዳቸውን እና የተለመደ የየቀን ሕይወት አካል መሆኑን ሴት ጋዜጠኞቹ ይናገራሉ።
እነዚህ ጥቃቶች ኢኮኖሚያዊ መልክን በያዙ ማባበያዎችም ተሸፍነው ብቅ እንደሚሉም ጋዜጠኞቹ ይጠቅሳሉ።
"ለምን ቲቪ ላይ ሪኮመንድ አላረግሽም። ይህንን መልክ ይዘሽ ለምን ትደበቂያለሽ። የመድረክ ሥራ አለ አሰራሻለሁ። ሥራሽን አቀልልሻለሁ'' የሚሉ ማባበያዎችን ሽፋን የሚያደርጉ ትንኮሳዎች በተለይም ከአለቆች እንደሚመጣ ሃና ለቢቢሲ ትናገራለች።
ጥቃቶቹን ሪፖርት ማድረግ ለምን አስፈሪ ሆነ?
ሃሴት በምትሰራበት አንድ መገናኛ ብዙኃን እርሷ እና በተለይም አንድ የቅርብ ጓደኛዋ ባጋጠማቸው ትንኮሳ ምክንያት ሥራ ጥለው ወጥተዋል።
በአለቆቻቸው የደረሰባቸውን ጾታዊ ትንኮሳ ለበላይ ኃላፊ ያስታወቁት ሃሴት እና ጓደኛዋ፤ መፍትሔ ከማግኘት ይልቅ የሚደርስባቸው ጥቃት ተጠናክሮ በመቀጠሉ ሥራቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል።
የሚደርስባቸውን ትንኮሳ በዝምታ ሲያሳልፉ የቆዩት ጓደኛሞቹ፤ በሃሴት ጓደኛ ላይ አካላዊ ትንኮሳ በመፈጸሙ ነበር አቤት እንዲሉ የተገደዱት።
አለቃቸው ሁለቱንም ጋዜጠኞች ለሚተነኩሱ ነባር ሠራተኞች ደብዳቤ ጽፈው ማስጠንቀቃቸው ያስቆጣው የጓደኛዋ አጥቂ፤ ከስድብ እና ማዋረድ በተጨማሪ በኮምፒዩተሮቻቸው ላይ የነበሩ ፋይሎችን እስከማጥፋት ደርሶም ነበር ትላለች።
ከ20 በላይ አገራት ያሉ ከ2ሺህ በላይ ጋዜጠኞች የተሳተፉበት ከላይ የጠቀስነው ጥናት አንድ ሴት ጋዜጠኛ ከአንድ ወንድ ባልደረባዋ በበለጠ በእጥፍ ለጾታዊ ጥቃቶች የተጋለጠች መሆኗን ያክላል።
እነዚህ ጥቃቶች ከቃላት እስከ አካላዊ ጥቃት ድረስ ሊደርሱ እንደሚችሉ የሚያብራራው የጥናቱ ግኝት፤ ጥቃት ከሚደርስባቸው 5 ሴቶች ውስጥ አንዷ ብቻ ጥቃቱን ሪፖርት ታደርጋለች።
'እንዲህ አይነት ችግር ገጠመኝ' ብሎ ለሌሎች ባልደረቦች መናገር ያልተለመደ እንዲሁም ተጠቂዎችን የሚያስገምት በመሆኑ ምክንያት በርካቶች ሪፖርት አያደርጉም።
የትኛውም አይነት ጥቃት ያጋጠማት ሴት፤ ችግሩን ሪፖርት ከማድረጓ በፊት ሁለቴ ማሰቧ እና ያጋጠሟትን ጥቃቶች መደበቅ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሥርዓተ ጾታ እኩልነት ጥያቄዎች ገና በቅጡ ማንሳት እንኳ ብዙ በሚቀራቸው አገራት የተለመደ ነው።
ነገር ግን መገናኛ ብዙኃን ማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ መሰል ችግሮችን ይፋ ያወጣሉ መፍትሔ ያስገኛሉ ተብለው ቢታመንም የሴት ጋዜጠኞቹን ፈተና አንስቶ መነጋገር እንኳን እንግዳ ሃሳብ መሆኑን ከ20 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ሚዲያ ውስጥ የቆየችው ኤልሳቤጥ ሳሙኤል ትናገራለች።
በተለይም ጋዜጠኞቹ የሚሰጣቸው ማኅበራዊ ደረጃ እንዲሁም እውቅና 'እንዲህ አይነት ጥቃት ደረሰብን' ሲሉ የሚደርስባቸው ምላሽ በሥነልቦናቸው፣ በሙያዊ ቅቡልነታቸው እንዲሁም በኢኮኖሚያዊ መሰረታቸው ላይ የሚደርሰው አጻፋዊ ምላሽን በመሸሽ ዝምታን እንደሚመርጡ ትናገራለች።
"እነዚህ ሴቶች ወይ ስክሪን ላይ ፊታቸው ይታወቃል፣ ድምጻቸው ወይም ስማቸው ይታወቃል። 'እንዲህ ደረሰብኝ' ሲሉም ጥቃቱን ያደረሰው ሳይሆን ተጠቂዎቹ ናቸው ወቀሳም ሆነ ፍርድ የሚጣልባቸው'' የምትለው ኤልሳ፤ ሌላ ቁልፍ ጉዳይ ግን ለሴት ጋዜጠኞች ለመታፈናቸው ምክንያት ሆኗል ትላለች።
ጠንካራ የሆነ እና በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ እነዚህን ጥቃቶች ይፋ በማውጣት ወቅት የሚደርሱ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሞያዊ ጫናዎችን ለመቋቋም የሚያግዝ የሞያ ማኅበር ያለመኖሩ ቁልፍ ችግር ሆኖ ቀጥሏል ስትልም ትናገራለች።
ጋዜጠኞቹ መረጃ ለመሰብሰብ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ከሚያገኟቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ብሎም ማኅበራዊ አቅም ካላቸው ሰዎችም ጥቃቶቹ ይሰነዘርባቸዋል።
እነዚህ ክስተቶች በተናጠል ከሚያስከትሉት ጉዳት ባሻገር በጊዜ ሂደት ጋዜጠኞቹ ሥራቸውን ጥለው እንዲወጡ እና ከባድ የሥነ ልቦና ጉዳት እንዲያጋጥማቸው ምክንያት ይሆናል።
ለዚህ ማሳይ የሚሆነው የሃና ዕይታ ሲሆን ወንድ ባልደረቦቿ የሚፈለጉትን ጠይቀው እና ሥራቸወን ጨርሰው ቁጭ ሲሉ እሷ "ይሄንን ለብሼ ስሄድ ምን ይሉኝ ይሆን" ከሚለው ጥያቄ ስጋቷ እንደሚጀምር ታስረዳለች።
ድርብርብ ፈተናዎች
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ጋዜጠኝነትን እንደሙያ ይዞ መስራት እጅግ አስቸጋሪ ከሚባሉባቸው አገራት መካከል የቀዳሚ ተርታ ላይ ትሰለፋለች።
ጋዜጠኞች በዕለት ተዕት ከሚያጋጥማቸው የመረጃ ክልከላ ባሻገር ይታሰራሉ፣ ይደበደባሉ አንዳንዴም ይገደላሉ።
ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ኢትዮጵያ ከኤርትራ ቀጥሎ በርካታ ጋጤኞችን በማሰር በ2021 ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ጋዜጠኞችን በተለያዩ ምክንያቶች ከሕግ ውጪ አስሮ ማቆየት ብሎም ተጠያቂነት ለመሸሽ በሚደረጉ ጥረቶች መረጃ መሸሸግ የየዕለት ፈተናዎች ናቸው።
በእንዲህ ባሉ ወንድም ሆነ ሴት ጋዜጠኞች ከመንግሥት በሚያጋጥማቸው ጫናዎች ወቅትም ሴት ጋዜጠኞች ከፍ ላለ አደጋ እንደሚጋለጡ ምሳሌ የምትሆነው ኤልሳቤጥ፤ በእስር ወቅት ተጨማሪ ፈተናዎችን ማለፏን ታስረዳለች።
በታሰረችበት ክፍል ውስጥ ሦስት ሴቶች እንደነበሩ እና ማረፊያው ከወንዶች ጋር አንድ ግቢ ውስጥ መሆኑ ለስጋቷ ዋነኛ ምንጭ ነበር።
ታስራ በቆየችበት የወታደሮች ካምፕ ውስጥ ቀን ቀን ''በተለየ ዕይታ የሚያዩን ሰዎች ማታ ይመጡ ይሆን በሚል ስጋት በየተራ ስንጠባበቅ ነበር ይምናድረው" ስትል ታስታውሳለች።
ሌላው ግን ከአንድ ወር በላይ የቤተሰብ ጥየቃም ሆነ ልብስ መቀየር የማይታሰብ ሆኖ መቆየቱ ለሴት ታሳሪዎቹ ከባድ ፈተና ነበር። የውስጥ ሱሪ እንኳን ሳይቀይሩ መቆየታቸውን ትናገራለች። ንጽህና መጠበቂያዎችን ማግኘት ቀላል እንዳልነበረም በማስታወስ።
ኤልሳቤጥ ታስራ በቆየችባቸው ጊዜያት ውስጥ ምንም አይነት ድጋፍ ያደረገላት የሙያ ማኅበር እንዳልነበረ እና ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ ግን ጠበቃ እንዳቆመላቸው እና ከእስር እንዲፈቱ የቅስቀሳ ጥረት ማድረጉን ትናገራለች።
ይህ ለዚህ ዘገባ ያነጋገርናቸው ጋዜጠኞች የሚስማሙበት እውነታ ነው። ጠንካራ የሆነ የሙያ ማኅበር ወይም ሴት ጋዜጠኞችን ለይቶ የሚደርስባቸውን ችግር ለመፍታት የሚሰራ ስብስብ አለመኖሩ እነዚህ ችግሮች ያለመፍትሄ ዛሬም በውስጥ የሚብላሉ ችግሮች እንዲሆኑ አድርጓል።
እየተበሳጩ ዝም እስከመቼ?
በመላው ዓለም ያሉ ሴት ጋዜጠኞች የሚያጋጥማቸውን ጾታዊ ጥቃት በተለያዩ አጋጣሚዎች በተለያዩ ወቅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።
በበርካቶች ዘንድ ከማይረሱት ክስተቶች መካከል በግብፁ ታህሪር አደባባይ ሕዝባዊ አብዮትን ለመዘገብ በወጣችበት በሰልፈኞች ጾታዊ ጥቃት የገጠማት የጋዜጠኛ ላራ ሎጋን ጉዳይ ነው።
ላራ ከ200 እስከ 300 የሚሆኑ ሰልፈኞች ከጠባቂዋ እና ከአዘጋጇ ነጥለው ልብሷን በመቅደድ ጾታዊ ጥቃት እንዳደረሱባት ይፋ አድርጋ ነበር።
ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ባሻገር ግጭቶችን እና አመጾችን መዘገብ ለሴት ጋዜጠኞች እጅግ አሰቸጋሪ መሆናቸውን በበርካታ ክስተቶች ወቅት ተመልክቷል።
ሴት ጋዜጠኞችን በዘርፉ ማሳተፍ የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑትን ሴቶች ዕይታ ማካተት የሚያስችል ሲሆን እንዲህ ባሉ የቀውስ ጊዜ ዘገባዎች ሴቶች ያለመሰታፋቸው ዘገባዎች የወንዶችን ድምጽ ብቻ ያጎሉ እንዲሆኑ ማድረጉን መታዘብ ቀላል አይሆኑም።
የሚዲያ ልማት ላይ የምትሰራው ኤልሳቤጥ ሳሙኤል የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምኅዳር ሴቶችን ብቻ ሳይሆን አካል ጉዳተኞችን እና ብሎም የብሔር ብሔረሰቦችን ስብጥር ከግምት ውስጥ የከተቱ አይደሉም ብላ ታምናለች።
ሴት ጋዜጠኞችን ከመቅጠር ጀምሮ አሰሪዎች ፍላጎት እንደማያሳዩ እና በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለው የሴቶች ቁጥር እጅግ ያነሰ እንዲሆን ማድረጉንም ታስረዳለች። ሴት ጋዜጠኞችን በውሳኔ ሰጪነት ቦታ ላይ ማግኘት ያልተለመደ መሆኑንም ታወሳለች።
"ሴት ጋዜጠኞች አርዓያ አድርገው ሊያዩዋቸው የሚችሉ ሴት ጋዜጠኞች የሉም" ስትል ኤልሳቤጥ ትናገራለች።
ቀጣሪዎች በተቋማቸው ውስጥ ጠንካራ የሆነ የሚዲያ ፖሊሲ ማውጣት ቁልፉ መፍትሄ ነው የምትለው ኤልሳቤጥ፤ ሴቶችን ማግለል እና መድሎን የሚያስቀር፣ ጾታዊ ጥቃት አድራሾችን የሚቀጣ ሆኖ መጻፍ እና መተግበር ይገባዋል ስትል ትናገራለች።
"ሥርዓተ ጾታን ያገናዘበ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲዎች እንዲያወጡ መሪውን ሚና የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን መውሰድ አለበት። ከዚያ በተረፈ ግን የሚዲያ ባለቤቶች፣ የሙያ ማኅበራት እንዲሁም ሴት ጋዜጠኞች ራሳቸው በጋራ ጥበቃ የሚያደርግላቸው ፖሊሲ እንዲኖር መስራት ይገባቸዋል" ስትል ትናገራለች።
ይህ ሃሳብ ለዚህ ዘገባ ያነገርናቸው ሴት ጋዜጠኞች በሙሉ የሚስማሙበት ነው።
መደራጀት እና በጋራ መቆም መጀመር ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ መቀየር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
የሴት ጋዜጠኞቻቸውን ነጻነት ማክበር እና ማስከበር ያልቻሉ የመገናኛ ብዙኃን የፕሬስን ነጻነት ማምጣት ይቻለው ይሆን?