በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ባይደን በኢትዮጵያ ላይ ያሳለፉትን ውሳኔ ትራምፕ ባለበት እንዲቀጥል አዘዙ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ላይ አስተላልፈውት የነበረው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለበት እንዲቀጥል ወሰኑ።

በፕሬዝዳንት ትራምፕ ረቡዕ ዕለት የተፈረመው እና ባለበት እንዲጸና የተወሰነው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ ሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎች ተስፋፍቶ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት አሳሳቢ በነበረበት ወቅት ነበር ተግባራዊ እንዲሆን በቀድሞው ፕሬዝዳንት የተወሰነው።

የተለያዩ ዕቀባዎችን የሚጥለው ይህ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲቀጥል የተወሰነበት ሰነድ "በኢትዮጵያ እና በአጠቃላዩ የአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋትን ስጋት ላይ የጣለው በሰሜን ኢትዮጵያ እና ከእርሱ ጋር ተያይዞ ያለው ሁኔታ ለዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ፖሊሲ አሳሳቢ እና የተለየ ስጋት ደቅኗል" ሲል አመልክቷል።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን በሚመለከት ከአራት ዓመት በፊት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ተላልፎ የነበረው እና ተግባራዊነቱ መስከረም 7/2018 ዓ.ም. ሊያበቃ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲቀጥል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወስነዋል።

ይህ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ጋር በተያያዘ ፕሬዝዳንት ባይደን ጥሰቶችን ፈጽመዋል በተባሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል 14046 የተሰኘ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መስከረም 7/2014 ዓ.ም. ነበር ያስተላለፉት።

በዚህ ትዕዛዝ ጦርነቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ያደናቀፉ፣ ተኩስ አቁም እንዳይደረግ እንቅፋት በመሆን በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑ ወይም ተባባሪዎቻቸው ላይ ዕቀባ እንዲጣል ይፈቅዳል።

ፕሬዝዳንቱ የፈረሙት ትዕዛዝ በዋናነት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት ባለሥልጣናት እንዲሁም በአማራ ክልል አስተዳደር እና በህወሓት አባላት ላይ ያነጣጠረ ነበር።

ትዕዛዙ መውጣቱን ተከትሎ የትዕዛዙ አስፈጻሚ የሆነው የአሜሪካ ግምጃ ቤት (ዲፓርትመንት ኦፍ ትሬዠሪ) በጦርነቱ ተሳታፊዎች ናቸው ባላቸው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጦር ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።

ፕሬዝዳንታዊው ትዕዛዝ ለአንድ ዓመት የሚጸና በመሆኑ ውሳኔው ከተላለፈበት መስከረም ጀምሮ በየዓመቱ በፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ሲታደስ ቆይቷል።

በአሜሪካ ሕግ መሠረት አንድ "ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ" ድንጋጌ የተቀመጠለት ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ባሉት 90 ቀናት ውስጥ ባለበት እንዲጸና የሚያደርግ ጥያቄ ካልቀረበበት በስተቀር ተግባራዊነቱ ስለሚያበቃ ነው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ውሳኔው ባለበት የሚያዘውን ደብዳቤ ረቡዕ ዕለት የፈረሙት።

ፕሬዝዳንታዊው ትዕዛዝ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉንም ወገኖች የሚመለከት ሲሆን፣ የተለያዩ ጥሰቶችን የፈጸሙ እና ሰላም እንዳይወርድ እንቅፋት ሆነዋል የተባሉ ወገኖችን ተጠያቂ ለማድረግ ለአሜሪካ ግምጃ ቤት ሥልጣን የሚሰጥ ነው።

ይህ ትዕዛዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በወጣበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት አሜሪካ በያዘችው አቋም የተሰማውን ቅሬታ በመግለጽ የተቃውሞ ደብዳቤ መጻፉ ይታወሳል።

ለተጨማሪ አንድ ዓመት በአዲሱ ፕሬዝዳንት እንዲራዘም የተወሰነው ይህ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ እንዲወጣ ምክንያት የሆነው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሰላም ስምምነት ከተጠናቀቀ ወደ ሦስተኛ ዓመት እየተቃረበ ቢሆንም አሜሪካ በውሳኔዋ ጸንታለች።

አሜሪካ በሰሜኑ ጦርነት ተሳታፊዎች ናቸው ባለቻቸው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጦር አመራሮች እና ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ከመጣሏ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ከነበረችበት የአሜሪካ የንግድ መርሃ ግብር - አጎዋ- ተጠቃሚነት እንድትወጣ ካደረገቻት ዓመታት ተቆጥረዋል።