ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ በክሪፕቶከረንሲ ያጭበረበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች ተያዙ

ክሪፕቶከረንሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በክሪፕቶከረንሲ አማካይነት 575 ሚሊዮን ዶላር አጭበርብረዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች መያዙን የኢስቶኒያ ፖሊስ አስታወቀ።

የኢስቶኒያ ፖሊስ ከአሜሪካው የፌደራል መርምራ ቢሮ (ኤፍቢይ) ጋር በመተባበር ሁለቱን ተጠርጣሪዎች ሲከታተል ቆይቶ ነው በቁጥጥር ስር የዋላቸው።

የኢስቶኒያ ዜግነት ያላቸው የ37 ዓመት ጎልማሶቹ ሰርጌይ ፓታፔንኮ እና ኢቫን ቱሮጊን ተላለፈው እንዲሰጧቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚፈልጉ ተነግሯል።

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ፖሊቢየስ በተባለ የበይነ መረብ ሐሰተኛ ባንክ እና ሃሽፍሌር በተሰኘ የክሪፕቶከረንሲ ግብይት አገልግሎት አማካይነት ነው በመቶዎቹ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያጭበረበሩት።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም አሜሪካ በግለሰቦቹ ላይ መደበኛ ክስ ከፍታለች።

ከአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት የወጣ መግለጫ፣ ሁለቱ ሰዎች አስከ 20 ዓመት ሊያሳስሩ በሚችሉት የገንዘብ ዝውውር ማጭበርበር እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ ለማድረግ በማሴር ክስ ተመስርቶባቸዋል ብሏል።

ተጠርጣሪዎቹ ኢስቶኒያ ዋና ከተማ ታሊን ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት ቀርበው እንደነበርና፣ ለአሜሪካ ተላልፈው አስኪሰጡ ድረስ በእስር ላይ እንደሚቆዩ መግለጫው አመልክቷል።

እስካሁን ሁለቱ ግለሰቦች ከጠበቆች ስለጉዳዩ የተሰጠ አስተያየት የለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት እንዳለው ሁለቱ ተጠርጣሪዎች፣ ማጭበርበር መሆኑን ያላወቁ ሰዎችን በሃሽፍሌር ክሪፕቶከረንሲ ማውጣት ሥራ ውስጥ እንዲሳተፉ እንደሚያደርጉ በመግለጽ ገንዘብ ሰብስበዋል።

ክሪፕቶ ማውጣት ማለት ኮምፒውተሮችን በመጠቀም ትርፍ የሚያስገኝ ተጨባጭ ያልሆነ ገንዘብ ማምረት ነው። ይህ ሂደትም በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው የኮምፒውተር ኃይልን ይጠቀማል።

በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ሰዎች ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋን የሚያወጣ የሃሽፍሌር ክሪፕቶከረንሲ ኮንትራቶችን በአራት ዓመታት ውስጥ ገዝተዋል። ነገር ግን ግለሰቦቹ የተስማሙትን ሥራ እውን ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት እንዳለው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ከክሪፕቶው በተጨማሪ ሰዎች ፖሊቢየስ በተባለው የበይነ መረብ ባንክ ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን ካፈሰሱ ትርፍ እንደሚያገኙ ቃል ገብተውላቸው ነበር።

በዚህም አማካይነትም 25 ሚሊዮን ዶላር ቢሰበስቡም የተባለው ባንክ ግን የት እንዳለ አይታወቅም።

ተከሳሾቹ በተጨባጭ የሌሉ ኩባንያዎችን በመጠቀም በወንጀል የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አድርገዋል። በዚህም ቢያንስ 75 ንብረቶችን እና የቅንጦት መኪኖችን መግዛታቸውን የአሜሪካ መንግሥት ገልጿል።

በኢስቶኒያ ፖሊስ የበይነ መረብ ወንጀል ቡድን እና በአሜሪካው ኤፍቢአይ አማካይነት በተካሄደው በዚህ ምርመራ 15 አሜሪካውያንን ጨምሮ 100 ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።

በግለሰቦቹ ተፈጽሟል የተባለው ወንጀል በኢስቶያ ውስጥ ካጋጠሙ ግዙፍ የማጭበርበር ድርጊቶች መካከል አንዱ መሆኑን ፖሊስ የገለጸ ሲሆን፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናትም ሕዝቡ እየሰፋ ከመጣው በቴክኖሎጂ የታገዘ ማጭበርበር እራሱን እንዲጠብቅ አስጠንቅቋል።

በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላሮችን ማጭበርበር የተጠረጠሩት ሁለቱ ግለሰቦች የተየዙት ኤፍቲኤክስ የተባለው የዓለም ሁለተኛው የክሪፕቶ ግብይት መድረክ ከስሮ የክሪፕቶከረንሲው ገበያ ቀውስ ውስጥ በወደቀበት ጊዜ ነው።

ኤፍቲኤክስ ባለፈው ሳምንት ኪሳራ እንደገጠመው አሜሪካ ውስጥ ያሳወቀ ሲሆን፣ በዚህም 50 የሚደርሱ የዋነኛ አበዳሪዎቹ 3.1 ቢሊዮን ዶላር እዳ እንዳለበት የፍርድ ቤት ሰነዶች አመልክተዋል።