በኤለን መስክ የሚመራው ጥምረት ቻትጂፒቲን ለመግዛት 97 ቢሊዮን ዶላር አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኤለን መስክ የሚመራው የባለሀብቶች ጥምረት የቻት ጂፒቲን ፈጣሪ የሆነውን ኦፕንኤአይ ለመግዛት ጥያቄ አቀረበ።
ኦፕንኤአይ የተባለው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተቋም ለመግዛት 97.7 ቢሊዮን ዶላር ነው የቀረበው።
ኤለን መስክ በኋላ ላይ ከተቋሙ ጋር ያለስምምነት ቢሊያይም የኦፕንኤአይ ተባባሪ መሥራች ነበር።
የቢሊየነሩ ጠበቃ ማርክ ቶቤሮፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያውን ሁሉንም ንብረት ለመግዛት ሰኞ ለቦርዱ ጥያቄውን ማቅረቡን አረጋግጠዋል።
ይህ ጥያቄ የዓለም ቁጥር አንድ ባለሀብት እና የዶናልድ ትራምፕ ቀኝ እጅ በሆነው ኤለን መስክ እና የኦፕንኤአይ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳም አልታማን መካከል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተቋሙን የወደፊት ቅርጽ በተመለከተ የነበራቸውን ልዩነት ባልተጠበቀ ሁኔታ የቀየረ ሆኗል።
ሳም አልትማን በኤክስ ገፁ "አንፈልግም፣ እናመሰግናለን። ከፈቀድክ ትዊተርን በ9.74 ቢሊዮን ዶላር ልግዛህ" የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ኢላን መስክ የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስን በ44 ቢሊዮን ዶላር መግዛቱ የሚታወስ ነው።
ኦፕንኤአይ በዋና ዋና የሙያ መስኮች ላይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቶችን በማበልጸግ እና በዘርፉ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ በማፈስስ ስሙ የገነነ ተቋም ነው።
መስክ እና አልትማን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ተቋሙን በአውሮፓውኑ 2015 ለትርፍ ያልተቋቋመ ኩባንያ አደርገው ቢመሰርቱትም ከ3 ዓመት በኋላ በ2018 በሁለቱ መካከል የነበረው ግንኙነት በመሻከሩ የቴስላ እና ኤክስ ባለቤቱ መስክ ከተቋሙ ጋር ተለያይቷል።
ከዚህ በኋላ አልትማን ኩባንያውን ድጋሚ በማዋቀር ለትርፍ ወደሚሠራ ተቋም ቀይሮታል። ይህም መስክ ኤአይ ለሰው ልጆች ጥቅም ማዋል የሚለውን ኩባንያው የተመሠረተበትን ዋነኛ ዓለማ የሳተ ነው በሚል ተቃውሞታል።
አልትማን ኦፕንኤአይ አትራፊነት የተቀየረው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፉን በአስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ በመደገፍ ይበልጥ ለማሳደግ ነው ሲል ይከራከራል።
የባለሀብቶቹ ጥምረት የግዢ ጥያቄ በመስክ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኩባንያ ኤክስኤአይ እና በሌሎች ታላላቅ ኩባንያዎች ይደገፋል።
"ኦፕንኤአይ ለምንም ክፍት ወደሚሆንበት አሰራር የሚመለሰብት ጊዜው አሁን ነው። ይህም ደህንነትን መሰረት ወዳደረገው የመጀመሪያው ዓላማው የሚመለስበት ነው። ይህ የሚሆንበትን መንገድ ማረጋገጥ ይኖርብናል" ሲል መስክ በሰጠው የጽሁፍ መግለጫ ተናግሯል።
ኤለን መስክ በሚመራው ጥምረት የቀረበው 97.4 በሊዮን ዶላር "ኦፕንኤአይ በጥቅሉ አለው ተብሎ ከሚታሰበው 157 በሊዮን ዶላር ዋጋ አንጻር ዝቅ ያለ ነው። ይህም ተቋሙ ለመጨረሻ ጊዜ ገቢውን ለማሳደግ ካደረገው የባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ተሳተፎ መዋጮ በመነሳት የተሰላ ነው።
ተቋሙ በተመሳሳይ መንገድ ገቢ በማሰባሰብ ያለውን ዋጋ ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ማቀዱ ተነግሯል።
የመስክ ጠበቃ በጽሁፍ ባወጣው መግለጫ ከዚህ በላይ በሆነ ገንዘብ ተቋሙን ለመግዛት የሚመጣ ተጫራች የሚመጣ ከሆነ የባለሀብቶቹ ጥምረት የሚያቀርበውን ገንዘብ ለማሳደግ እንደተዘጋጀ አሳውቋል።












