በዓለማችን ግዙፉ የድንጋይ ከሰል መጫኛ ወደብ ተቃውሞ ያደረጉ ከ100 በላይ ሰዎች ታሰሩ

በዓለማችን ግዙፉ የድንጋይ ከሰል ማጋዣ ለሁለት ቀናት ያክል ተቃውሞ ለማሰማት ከወጡ ሰዎች መካከል 109 ያክል ለእስር ተዳርገዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሟጋቾች በዋና እና በታንኳ በአውስትራሊያዋ ኒውካስል ወደብ ተቃውሟቸውን ለማሰማት ተገኝተዋል።

ሰልፈኞቹ እንደሚሉት በተቃውሞው ምክንያት ግማሽ ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል ተጭኖ እንዳይወጣ ሆኗል።

አውስትራሊያ የዓለማችን ሁለተኛ ግዙፏ የድንጋይ ከሰል ላኪ ሃገር ስትሆን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘትም ትጠቀምበታለች።

ከሲድኒ 170 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የኒውካስል ወደብ ደግሞ የሃገሪቱ ግዙፉ የድንጋይ ከሰል ማመላሻ ነው።

ከአውስትራሊያ የተውጣጡ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ቅዳሜና እሑድ ወደ ወደቡ አቅንተው የድንጋይ ከሰል ተጭኖ እንዳይወጣ ለማገድ ሞክረዋል።

ተቃውሞው በፖሊስ ይሁንታ ቢያገኝም 109 ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል። አምስት ሕፃናት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ወዲያው ተለቀዋል።

የኒው ሳውዝ ዌልስ ፖሊስ እንደጠቆመው 104 ሰዎች የተቃውሞው ሰዓት ካለቀ በኋላ ወደቡን ለቀን አንሄድም በማለታቸው ክስ ቀርቦባቸዋል።

“ይሄን የማደርገው ለልጅ ልጆቼና ለመጪው ትውልድ ነው” ይላሉ የ97 ዓመቱ አለን ስቱዋርት።

“በኛ ድርጊት ምክንያት የሚመጣው ችግር ገፈት ቀማሽ በመሆናቸው ይቅርታ እጠይቃለሁ። ለዚህ ነው የድርሻየን ልወጣ የወሰንኩት” ይላሉ።

ታውሞውን ያሰናዳው ራይሲንግ ታይድ የተባለው ድርጅት “በአውስትራሊያ ታሪክ ለአየር ንብረት ለውጥ የተደረገ ትልቁ ሰላማዊ ተቃውሞ ነው” ብሎታል።

ተቃውሞው ኮፕ28 ከተሰኘው ሐሙስ ዱባይ ከሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ቀድሞ ነው የተደረገው።

ራይሲንግ ታይድ የአንተኒ አልባኒስ መንግሥት የድንጋይ ከሰል ላኪዎችን እንዲቀርጥና አዳዲስ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶችን እንዲያቋርጥ ይጠይቃል።

አውስትራሊያ ብዙውን ጊዜ አየር ንብረት ለውጥን በተለመከተ ወደኋላ የቀረች ሃገር ተደርጋ ብትቆጠርም የአልባኒስ መንግሥት ባለፈው ዓመት ሥልጣን ሲይዝ “ዓለም አቀፉን ትግል እቀላቀላለሁ” ሲል ቃል ገብቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የልቀት መጠንን በ2030፣ በ43 በመቶ ለመቀነስ የሚሠራ ሕግ አውጥተዋል።

ነገር ግን አዳዲስ ‘የፎሲል ፊዩል’ ፕሮጀክቶችን ካለመሰረዛቸውም በላይ ከባለፈው ግንቦት ጀምሮ አዳዲስ አራት አዳዲስ የድንጋይ ከሰል ማውጫ ፋብሪካዎችን ከፍተዋል።