ፖፕ ፍራንሲስ ሆስፒታል ገቡ

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በመተንፈሻ አካላት የጤና ችግር ምክንያት ሆስፒታል ገቡ።

ፖፕ ፍራንሲስ ከመተንፈሻ አካላት ህመም ጋር በተያያዘ ለጥቂት ቀናት ሮም በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ሊቆዩ እንደሚችሉም ቫቲካን አስታውቋል።

የ86 ዓመቱ አባ ፍራንሲስ በቅርብ ቀናት ውስጥ የመተንፈስ ችግር እንደገጠማቸው ነገር ግን በኮቪድ-19 አልተያዙም ሲል መግለጫው አክሏል።

“ለተወሰኑ ቀናት ተገቢ የሆስፒታል ህክምና ያስፈልጋቸዋልም” ብሏል የቫቲካን መግለጫ።

“ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በደረሷቸው በርካታ መልዕክቶች ልባቸው የተነካ ሲሆን እየተደረገላቸው ላለው ጸሎትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል” ሲልም አክሏል።

የአባ ፍራንሲስ ጥበቃን ጨምሮ የቅርብ ሰራተኞቻቸው በጌሚሊ ሆስፒታል እንደሚቆዩም ለጉዳዩ ቅርበት ያለው ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ለአባ ፍራንሲስ ይህ ወቅት በዓመቱ ውስጥ በሥራ የሚጨናነቁበት ጊዜም ነው።

የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዐቢይ ጾምን እየጾሙ ሲሆን በመጨረሻው ሳምንትም የህማማት፣ ስቅለትና ፋሲካ በዓላትን ያከብራሉ።ለእነዚህም ክብረ በዓላት አባ ፍራንሲስ እየተዘጋጁ እንደሆነ ተነግሯል።

በዚህ ሳምንት እሑድ የሆሳዕና በዓል የሚከበር ሲሆን ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የህማማት ሳምንት እንዲሁም የትንሳዔ በዓል ይከበራል።

በተጨማሪም በሚያዝያ ወር መጨረሻ ሃንጋሪን ለመጎብኘት ቀጠሮ ይዘው ነበር።

ረቡዕ ጥዋት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ሳምንታዊውን የጸሎት ፕሮግራም መርተው የነበረ ሲሆን በወቅቱም በጥሩ መንፈስ ላይ ነበሩ ተብሏል። ነገር ግን ወደ ተሽከርካሪያቸው ሲገቡ በእርዳታ የገቡ ሲሆን ተዳክመው ታይተዋል።

ቫቲካን መጀመሪያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በየጊዜው ለሚያደርጉት ምርመራ ወደ ሆስፒታል ማቅናታቸውን አሳውቆ የነበረ ቢሆንም አባ ፍራንሲስ የቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ በአጭር ጊዜ ውስጥ መሰረዛቸውን ተከትሎ የጣሊያን ሚዲያዎች መታመማቸውን ዘግበዋል።

የህመማቸው ዜና ከወጣ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አባ ፍራንሲስ እንዲያገግሙ ሕዝቡ በጸሎት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

በአሜሪካ መሪነት ሁለተኛው የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑት ፕሬዚዳንት ባይደን፣ አባ ፍራንሲስ በዓለም ካሉ ሰዎች “እንደ እየሱስ ክርስቶስ የመሰሉ” ሲሉም ገልጸዋቸዋል።