የባለትዳሮች አለመግባባት ለምን ወደ ፍቺ ያመራል?

ዓለማችንን ዞር ዞር ብሎ በፍቺ መነጽር የሚመለከት ቢኖር ከአናት ተቀምጣ የሚያገኛት ማልዴቪስን ነው።

ማልዴቪስ በዚሁ የተነሳ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሟ በደማቁ ሰፍሯል።

ከ1000 ትዳሮች 5.52 ያህሉ 'ትዳር በአፍንጫዬ ይውጣ' ብለው ፍቺን መርጠዋል።

ትንሽ ቀደም ቢለም በ2002 የተሰራ ጥናት በዚህችው አገር ከ1ሺህ ባለትዳሮች 10.97 ያህሉ እህል ውሃቸውን በፍቺ ደምድመዋል ይላል።

የሕይወቴ ሕይወት አንቺ በመሆንሽ፣ ብለው የጀመሩት 'ትዳር አይንሽን ላፈር'፣ 'አይንህን ላፈር' ተባብሎ መለያየት በመላው ዓለም የተለመደ ነው።

ትዳር ዓለም አቀፋዊ እውነት እንደሆነ ሁሉ፣ ፍችም እንዲሁ አይቀሬ እጣ ይመስላል።

ካዛኪስታን እና ሩሲያ በተፋቺ ጥንዶች ቁጥር በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ላይ ናቸው።

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካም ትዳር የማይበረከትባቸው አገራት ተብለዋል።

በ2002 ጥናት መሰረት አሜሪካ ሶስተኛ ላይ ነበረች። በ2020 ጥናት መሰረት ደግሞ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በአሜሪካ 53 በመቶ የሚሆኑ ትዳሮች በፍቺ ይጠናቀቃሉ።

በአፍሪካ አገራት ጥናት ላይ የተመሰረተ የተደራጀ መረጃ ባይኖርም ፍቺ ግን መኖሩ የማይካድ ሀቅ ነው።

የሶስት ጉልቻው መሰረት የተናጋበት ትዳር፣ ቋንቋቸው የተደበላለቀባቸው ጥንዶች፣ ጉንጫቸውን ለስሞሽ ሳይሆን ለንክሻ የሚፈላለጉ ባልና ሚስቶች እዚህም እዚያም አሉ።

ፍቺ በልጆች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ያጠኑት እና የጋብቻ አማካሪ የሆኑት ቀበኔ ሁንዴሳ “የትዳር መፍረስ የልጆች የወደፊት እጣ ፈንታ ከማጨለም ባለፈ በአገር ላይ ትልቅ ኪሳራ የሚያደርስ ነው” ይላሉ።

ፍቺ በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ አክራሪ ሀይማኖተኞች እና ባህላቸውን አጥባቂዎች የሚበዙባት አገር እንደመሆኗ ለትዳር ትልቅ ስፍራ ከሚሰጡ አገራት መካከል አንዷ ናት ይላሉ ቀበኔ ሁንዴሳ።

ይኹን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፍቺ በተለይ በከተሞች አካባቢ እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ እና በአካባቢው በሚገኙ ከተሞች ያለው ፍቺ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉትየትዳር አማካሪዋ ቀበኔ፣ ይህ ማለት በገጠር አካባቢ ፍቺ የለም ማለት እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ።

የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ በ2014 በጀት ዓመት ከ14 ሺህ በላይ ጋብቻ ፣1 ሺህ 623 የፍቺ ምዝገባዎችን ማከናወኑን አሳውቆ ነበር።

ይህንን ቁጥር በ2010 ዓ.ም ብናየው ደግሞ በ2010 1 ሺ 923 የሚሆኑ ጥንዶች ፍቺ መፈጸማቸውን የአዲስ አበባ ወሰኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ መረጃ ያሳያል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የፍቺ ቁጥር መጨመሩ እንዳሳሰበው በድረገፁ ላይ ገልፆ ነበር።

በአዲስ አበባ ከ2012-2014 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 16 ሺህ 35 ፍቺዎች እንደተካሄዱ የፍርድ ቤቱ መረጃ ያሳያል።

በአዲስ አበባ ብቻ በዚሁ ዓመታት ከተመዘገቡት 51ሺህ 721 ጋብቻዎች ውስጥ 3ሺህ 550 መፍረሱን የወሳኝ ኩነቶች ጽህፈት ቤት ገልጿል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ትክክለኛው የፍቺ መጠን በቁጥር ተሰልቶ ባይታወቅም ጉዳቱ ግን ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷል ይላሉ ወ/ሮ ቀበኔ።

የጋብቻ መፍረስ በልጆች ላይ የሚያደርሰው ጠባሳ

ፍቺ በየትኛውም የእድሜ ክልል ለሚገኙ ሕጻናት ላይ የሚያደርሰው የስነልቦና ጠባሳ ቀላል የሚባል አይደለም።

የትዳር መፍረስ ልጆችን፣ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብን እና አገርን እንደሚጎዳ በርካታ አገር አቀፍ እና ዓለም አቀፋዊ ጥናቶች ያስረዳሉ።

ተመራማሪዋ ቀበኔ ሁንዴሳ ገለጻ ከሆነ “ትዳር ሲፈርሰ ልጆች ከስሩ እንደተነቀለ ዛፍ ነው የሚሆኑት” ይላሉ።

ልጆች አስተዳደጋቸውን የሚከታተል ሰው ሲያጡ በፍርሃት፣ በቁጣ እና በሐዘን ያድጋሉ ሲሉም ያክላሉ።

በኢትዮጵያ ችግሩ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የሚገልፁት ወ/ሮ ቀበኔ፣ ይህም ሕጻናት ባልተለመደ ባህሪ እንዲያድጉ ያደርጋል ሲሉ ያስረዳሉ።

በፍቺ ምክንያት ሕጻናት ለአካላዊ፣ ለአእምሯዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት እንደሚጋለጡ ጨምረው ገልጸዋል።

“ከእናት እና ከአባታቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና ፍቅር ያቋረጣል። ይህ ደግሞ አእምሯቸውን ከመጉዳቱ ባሻገር በቀሪው ዘመናቸው በድንጋጤ እና ፍርሃት እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል።”

ልጆች የወላጆቻቸውን ፍቅር በጋራ ይፈልጋሉ የሚሉት ወ/ሮ ቀበኔ፣ ፍቺ ትውልድን፣ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብን ከመጉዳት አልፎ ለአገር ትልቅ ጉዳት ነው ይላሉ።

ትዳር በጠንካራ መሰረት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት የሚሉት ወ/ሮ ቀበኔ፣ የጋብቻ መፍረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለአገር መውደቅ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ።

“ቤተሰብ በጋራ ያፈሩትን ልጅ በመንከባከብ በስርዓት ማሳደግ እና ማስተማር፣ ለአገር እንዲሆኑ አድርገው መቅረጽ አለባቸው። ልጆችን በኃላፊነት ካላሳደግናቸው ጠንካራ ማኅበረሰብ ሊገነባ አይችልም። ጠንካራ ማኅበረሰብ የሌላት አገር ሁሌም ችግር ውስጥ ናት። ይህ ነው የፍቺ ችግር”

የፍቺ ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?

በኢትዮጵያ ለፍቺ ዋነኛ መንስዔዎች ተብለው የሚጠቀሱት የኢኮኖሚ መዳከም፣ አለመተማመን፣ ቅናት እና የወሲብ አለመጣጣም ናቸው ይላሉ ባለሙያዋ።

“በእኛ አገር ውስጥ፣ ወሲብ እንደ ነውር ነው የሚቆጠረው። ይህም ብዙ ችግር አስከትሏል። በምዕራቡ ዓለም ግን ይህ እምብዛም ችግር አይደለም”

እንደ ወ/ሮ ቀበኔ ጥናት ትዳሮች በወሲብ አለመጣጣም ችግር ምክንያት የሚፈርሱ ቢሆንም እንኳን፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹ ትልቅ ድርሻ አላቸው።

“በንብረት ላይ መጋጨት፣ አለመግባባት፣ እርስ በእርስ መጠራጠር እንዲሁም ደግሞ ንብረትን መደበቅ ለትዳር መፍረስ ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ናቸው”

ሌላው ከባድ የፍቺ ምክንያት ደግሞ ይላሉ ቀበኔ፣ ጣልቃ ገብነት ነው ።

የቤተሰብና የሌሎች ሰዎች ጣልቃ ገብነት በተለያየ መንገድ ይገለጻል።

በልጆች ቁጥር፣ በአኗኗር ሥርዓት፣ በመኖርያ ስፍራ ምርጫ በባልና ሚስት መካከል ጣልቃ የሚገቡ ሰዎች ለፍቺ ምክንያት ይሆናሉ።

እንደ ባለሙያዋ ገለጻ ዘመድም ሆነ ሌላ ሰው በትዳር ውስጥ ጣልቃ መግባት ከጀመረ ትዳሩ አደጋ ውስጥ እንደሚሆን ጥናት ውጤታቸውን በመጥቀስ አስረድተዋል።

ነገር ግን ይላሉ ተጋቢዎቹ ከተግባቡ፣ ከተመካከሩና ከተከባበሩ ሦስተኛ ወገን ትዳር ለማፍረስ ቦታ አይኖረውም።

በአሁኑ ሰዓት ግን ፍቅራችንን በቀለበት እንሰረው፣ በሰርግ እናድምቀው የሚሉትን ያህል ፍቺያችንን አጽድቁልን ብለው የፍርድ ቤት ደጃፍ የሚመላለሱ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።

ትዳርን ከፍቺ አረንቋ ለማውጣት ግን ወላጆች የሚከፍሉት መስዋዕትነት እንደሚኖር ቀበኔ ያነሳሉ።

ይህ መስዋዕትነት ለልጆች ሲባል ሊከፈል የሚችል እንደሆነ ጨምረው ጠቅሰዋል።

ይህ ሳይሆን ቀርቶ የፍቅር ሸማ የለበሰው ትዳር፣ የፍቺ ጸሐይ ከሞቀው ግን በመካከል ያሉ ልጆች እነዳይጎዱ ማህበረሰቡ እና መንግሥት ተገቢ የሆነ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ቀበኔ ይመክራሉ።

በፍቺ የተለያዩ ቤተሰቦች ያሏቸውን ልጆች “በትምህርት ላይ እንዲያተኩሩ እና የተለያዩ የስራ ተግባራትን እንዲለማመዱ የተወሰነ የማገገሚያ ማዕከል ሊያቋቁምላቸው ይገባል”

አክለውም ጥንዶች ወደ ትዳር ከመግባታቸው በፊት ሊያስተውሉ ስለሚገባው ጉዳይ ያነሳሉ።

“መጀመርያ ትዳር ከመንገድ ላይ ጎራ የምንልበት አይደለም። በእቅድ እና በትኩረት የተገነባ ትዳር ከሁሉም የበለጠ ጠንካራ መሰረት ይኖረዋል።”

በመጨረሻም ጋብቻ ማኅበራዊ ተቋም እንደመሆኑ ተጋቢዎች በሰከነ አዕምሮ ሊጠብቁት ካልቻሉ ሌላ አካል ማንም አይጠብቀውም ሲሉ ሃሳባቸውን ይደመድማሉ።