ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ ዩታ ግዛት መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ታገደ
በአሜሪካ ዩታ ግዛት ውስጥ የዴቪስ ስኩል ዲስትሪክት ትምህርት አስተዳደር መጽሐፍ ቅዱስን “አመጽ እና ነውር” የያዘ በሚል ከመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ ማገዱ ተሰምቷል።
የትምህርት ቤቶቹ አስተዳደር መጽሐፍ ቅዱስን ያገደው አንድ ቤተሰብ የኪንግ ጀምስ ዕትም ለሕጻናት ተስማሚ ያልሆኑ ክፍሎችን ይዟል ብሎ ቅሬታ ማስገባቱን ተከትሎ ነው።
ዩታህን የሚያስተዳድረው የሪፐብሊካን መንግሥት በ2022 “ልቅ ግብረ ሥጋን የሚያትቱ ወይንም ከሥነምግባር ያፈነገጡ” ይዘቶች ያሏቸው መጻሕፍትን ከትምህርት ቤቶች የሚያግድ ሕግ አውጥቶ ነበር።
በግዛቲቱ እስካሁን ድረስ ከትምህርት ቤቶች የታገዱት መጽሐፍት ከዘር ማንነት እና ከተመሳሳይ ጾታ ጋር የተገናኙ ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱሰን ማገድ የመጣው ወግ አጥባቂዎች በግዛቲቱ አከራካሪ የሆኑ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት መብቶች እንዲሁም ዘርና ማንነት ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች እንዳይሰጡ ለማገድ የሚያስችል ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ በኋላ ነው።
ከዩታ ሌላ ቴክሳስ፣ ፍሮሊዳ፣ ሚዙሪ እና ሳውዝ ካሎራይና በተመሳሳይ ተገቢ አይደሉም ያሏቸውን መጻሐፍትን ከትምህርት ቤቶች አግደዋል።
አንዳንድ ሊብራል ነን የሚሉ ግዛቶች በበኩላቸው ከትምህርት ቤቶች በዘር እና ማንነት ላይ ጸያፍ ነገርን ይዘዋል ያሏቸውን መጽሐፍት አግደዋል።
በዩታህ መጽሐፍ ቅዱስን ከትምህርት ቤቶች እንዲታገድ የሚጠይቀው ቅሬታ የገባው በሕዳር ወር አካባቢ ሲሆን፣ ቀድሞውንም መጽሐፍ ቅዱስ በሥርዓተ ትምህርቱ አካል ያልነበረ መሆኑን በመግለጽ ስምንት መጽሐፍ ቅዱሶችን ከትምህርት ቤቶቹ መደርደርያ ላይ መሰብሰባቸውን አስተዳዳሪዎቹ ይፋ አድርገዋል።
ጉዳዩን የተመለከተው ኮሚቴ መጽሐፍ ቅዱስ የትኛው ክፍል ላይ “ነውር የሆኑ፣ ጭካኔና አመጽ የሚያነሳሱ አንቀጾችን የያዘ” እንደሆነ አላብራራም።
በአካባቢው የሚታተም 'ሳልት ሌክ ትሪቢዩን' የተሰኘ ጋዜጣ ቅሬታውን ያስገባውን ወላጅ አናግሮ ኪንግ ጀምስ እትም “ለታዳጊዎች የሚመጥን እሴቶች የሉበትም” ማለታቱን ዘግቧል።
ወላጁ አክሎም ግዛቲቱ በ2022 መጻሕፍትን ለማገድ ያወጣችውን ሕግ በመጥቀስ በእኛ አዲስ አረዳድ ልቅ የሆነ ግብረስጋን የሚገልጹ ክፍሎች አሉት ብሏል።
የግዛቲቱ ሕግ አውጪ የሆኑት እና በ2022 የጸደቀውን ሕግ ያረቀቁት ግለሰብ መጽሐፍ ቅዱስ ይታገድልኝን ጥያቄ ሲሰሙ “ይህ ቀልድ ነው” ሲሉ ተሳልቀው ነበር።
ነገር ግን በዚህ ሳምንት ለታዳጊዎች የማይመጥኑ ” አዳጋች አንቀጾች አሉት” ሲሉ ተደምጠዋል።
ኬን አይቮሪ የተባሉ ግለሰብ “በአሜሪካ መጽሐፍ ቅዱስ ቤተሰቦች ሰብሰብ ብለው የሚያጠኑት፣ በሚገባ የምንረዳው ነው” ብለዋል።
ግዛቲቱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሳለፈችው ውሳኔ በ2022 ያወጣችን ሕግ የሚተላለፍ ባይሆንም ነገር ግን “ለአዳጊ ተማሪዎች የማይመጥን ነውር የሆኑ፣ ጭካኔና አመጽ የሚያነሳሱ አንቀጾችን የያዘ” ነው ብላለች።
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግን መጽሐፍ ቅዱስ ይኖራል ተብሏል።
ቦን ጆንሰን በመጀመርያ ደረጃ የሚማር ልጅ ያለው ሲሆን በግዛቲቱ የተወሰደውን እርምጃ እንደሚቃወም ለሲቢኤስ ኒውስ ገልጿል።
“ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚቀነስ ክፍል መኖሩን ማሰብ አልችልም። ልክ ምስል እንደማውጣት እኮ አይደለም” ብሏል።
ከዩታ ሌላ መጽሐፍ ቅዱስን ከመደርደሪያቸው ላይ ያስወገዱ ሌሎች የአሜሪካ ግዛቶችም አሉ።
ባለፈው ዓመት የቴክሳስ ግዛት ከቤተ መጻሕፍት መደርደርያዎች የወግ አጥባቂዎችን የተወሰኑ መጻሕፍትን ለማገድ የጀመሩትን ጥረት ለማስቆም በሚል የቀረቡ ቅሩታዎችን ተከትሎ መጽሐፍ ቅዱስን ከመደርደርያዎቹ ላይ ሰብስቧል።
ባለፈው ወር በካንሳስ ተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከትምህርት ቤታቸው ቤተ መጻሕፍት እንዲወጣላቸው ጠይቀው ነበር።