የመካከለኛው ምሥራቅ እና የአውሮፓ መሪዎች የጋዛን የሰላም ዕቅድ እንደሚደግፉ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የአውሮፓ እና መካከለኛው ምሥራቅ መሪዎች አሜሪካ የጋዛን ጦርነት ለማስቆም ያቀረበችውን የሰላም ዕቅድ እንደሚደግፉ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐማስ ስምምነቱን መቀበል አለበት ብለዋል።
ትራምፕ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተስማሙበት ዕቅድ፤ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ያደርጋል ተብሏል።
ሐማስ በ72 ሰዓታት ውስጥ 20 እስራኤላውያን ታጋቾችን እና የሞቱ ታጋቾችን አስክሬን እንዲያስረክብ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል።
በምላሹም በመቶዎች የሚቆጠሩ የታገቱ የጋዛ ነዋሪዎች ከእስር የሚለቀቁ ይሆናል።
የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝዳንት አንቶኒዮ ኮስታ "ኔታንያሁ ለሰላም ዕቅዱ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸው አበረታች ነው" ብለዋል።
"ሁሉም አካላት ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ለሰላም ዕድል መስጠት አለባቸው" ሲሉም አክለዋል።
ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ቅርብ የሆኑ የፍልስጤም ምንጭ ለቢቢሲ አንደተናገሩት፣ ዋይት ሀውስ ለሐማስ 20 ነጥቦችን አቅርቧል።
የፍልስጤሙ ዋፋ የዜና ኤጀንሲ ላይ በወጣው መግለጫ የፍልስጤም አስተዳደር "በጋዛ ላይ የተከፈተውን ጦርነት ለማስቆም ከአሜሪካ፣ ከቀጣናው አገራት እና አጋሮቻችን ጋር በጋራ ለመሥራት አሁንም ቁርጠኛ ነን" ሲል አቋሙን አስታውቋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ካታር፣ ግብፅ፣ ዮርዳኖስ፣ ቱርክ፣ ኢንዶኔዥያ እና ፓኪስታን በጋራ ባወጡት መግለጫ "ትራምፕ የጋዛን ጦርነት ለመግታት እያደረጉ ያሉትን ያላሰለሰ ጥረት እንደግፋለን" ብለዋል።
አሜሪካ በቀጣይ ጋዛን ማን ያስተዳድራል በሚለው ላይ የወጠነችውን ዕቅድ አስቀምጣለች።
ጋዛን በጊዜያዊነት "ከፖለቲካ ነጻ የሆነ ኮሚቴ" እንደሚመራት እና አስተዳደሩን "አዲስ ዓለም አቀፍ የሽግግር ጊዜ ተቆጣጣሪ አካል" እንደሚከታተል ተገልጿል።
ይህንን ተቆጣጣሪ አካል የሚሾሙት ትራምፕ ይሆናሉ።
የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር የዚህ ተቆጣጣሪ አካል እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ይመሠረታል የተባለውን ተቆጣጣሪ አካል በተመለከተ ቶኒ ብሌር "በጣም ጥሩ ሐሳብ ነው" ብለዋል።
የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ዕቅዱን እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
"ሁሉም ወገኖች አንድ ላይ ሆነው ስምምነቱ እንዲተገበር ከአሜሪካ መንግሥት ጋር እንዲሠሩ እንጠይቃለን" ሲሉም ተናግረዋል።
ሐማስ "የሰላም ዕቅዱን ተቀብሎ ሰቆቃው ሊቆም ይገባል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐማስ "ጦር ማውረድ አለበት። የተቀሩትንም ታጋቾች ይልቀቅ" ብለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን "ፈረንሳይ ጦርነቱ እንዲቆምና ታጋቾች እንዲለቀቁ ለመተባበር ዝግጁ ናት" በማለት ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
"ይሄ ዕቅድ ለተጨማሪ ውይይት በር መክፈት አለበት። በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንም ያስችላል" ሲሉም ማክሮን አክለዋል።
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ባወጡት መግለጫ፤ የሰላም ዕቅዱ "ለውጥ የሚያመጣ ስለሆነ ሁሉም አካላት ሊቀበሉት ይገባል" ብለዋል።
የሰላም ዕቅዱ ሐማስ ጋዛን በማስተዳደር ረገድ "ቀጥተኛ ወይም ተዘዋዋሪ" ሚና ሊኖረው እንደማይችል ያትታል።
አብዛኛው የዕቅዱ ክፍል አሜሪካ ጋዛን መልሶ ለመገንባት የወጠነችው "የምጣኔ ሃብት እድገት" ላይ ያተኮረ ነው።
"እስራኤል ጋዛን አትቆጣጠርም፤ በግዳጅም የግዛቷ አካል አታደርግም" የሚል ነጥብም አካቷል።
የሰላም ዕቅዱ ሲተገበር የእስራኤል ጦር ጋዛን ለቆ እንደሚወጣ ተጠቅሷል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከነበራቸው አቋም በተለየ ሁኔታ የጋዛ ነዋሪዎች ከተማውን ለቀው እንዲወጡ አይገደዱም።
"ነዋሪዎች እዛው እንዲቆዩ እናበረታታለን። የተሻለች ጋዛን እንዲገነቡ እናግዛቸዋለን" በሚል በሰላም ዕቅዱ ላይ ሰፍሯል።
ለስምምነቱ ቅርብ የሆኑ የፍልስጤም ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ የካታርና ግብፅ አመራሮች በዶሀ ለሚገኙ የሐማስ አመራሮች ዕቅዱን አቅርበዋል።
ቀደም ሲል አንድ ከፍተኛ የሐማስ አመራር፤ በጋዛ ጦርነትን የሚያቆም ዕቅድን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ማንኛውም ስምምነት የፍልስጤማውያንን ፍላጎት የሚያስጠብቅ ሊሆን እንደሚገባ እንዲሁም የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ መውጣት እንዳለበት አስምረውበታል።
ትጥቅ መፍታትን በተመለከተ "በግዳጅ በይዞታ ሥር እስከሆንን ድረስ ትጥቅ መፍታት የሚለው ጉዳይ ቀይ መስመር ነው። ፍልስጤም የ1967ቱን ድንበር ተከትላ ነጻ አገር ሆና የምትመሠረትበት ፖለቲካዊ መፍትሔ ሲተገበር ነው ትጥቅ ስለመፍታት የምንነጋገረው" ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት በኒው ዮርኩ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ምዕራባውያን አገራት ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መስጠታቸው ይታወሳል።
ኔታንያሁ ይህንን በመቃወም ንግግር ሲያደርጉ በርካታ ዲፕሎማቶች እና አመራሮች ጉባዔውን ረግጠው ወጥተዋል።
እስራኤል በቅርቡ የአሜሪካ አጋር በሆነችው ካታር የሚገኙ የሐማስ አባላት ላይ ጥቃት መሰንዘሯ ትራምፕን ደስ አላሰኘም።
ኔታንያሁ ከትራምፕ ጋር ውይይት ከማድረጋቸው አስቀድመው በዋይት ሀውስ ሳሉ፣ ለካታር ጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ቢን አብዱልራሕማን ቢን ጃሲም አል-ታሒኒ ደውለው በሚሳዔል ጥቃቱ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
1200 ሰዎች የተገደሉበትን የሐማስ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ 66,055 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
የመንግሥታቱ ድርጅት በጋዛ ረሃብ መስፋፋቱን አስታውቋል። የድርጅቱ ኮሚሽን እስራኤል በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ መፈጸሟን ቢገልጽም እስራኤል ክሱን አልተቀበለችም።















