ባይደን፡ ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት ለማድረግ አሜሪካ ኃይል ለመጠቀም ዝግጁ ናት

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከአስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከአስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ ጋር

ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት ለማድረግ አሜሪካ “ያላትን ኃይል ሁሉ ለመጠቀም ዝግጁ ናት” ሲሉ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት በእስራኤል እያደረጉት ባለው ጉብኝት ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ ጋር በተወያዩበት ጊዜ ነው።

ኢራን እያካሄደች ያለው የኑክሌር ፕሮግራም ዋነኛ የደኅንነቷ ስጋት አድርጋ እስራኤል የምታቀርበው ሲሆን፣ ኢራን ግን የኑክሌር ግንባታዋ ለሰላማዊ አላማ መሆኑን ትናገራች።

ፕሬዝዳንት ባይደን ከእስራኤል ቀጥሎ አወዛጋቢውን ጉብኝት ባሳዑዲ አረቢያ ከማድረጋቸው በፊት ነገ አርብ ከፍልስጥኤም ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል።

ባይደን በዚህ ጉብኝታቸው በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ዋነኛ ወዳጅ ከሆነችው እስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር የሚያስችላቸውን ሰነድ ማዘጋጀታቸው ይታወቃል።

ባይደን “ኢራን ሔዝቦላህ፣ ሐማስ እና ኢስላማዊ ጂሐድን የመሳሰሉ ሽብርተኛ ቡድኖችን” በመጠቀም እየፈጸመችው ነው ያሉትን “የጠብ አጫሪነት እና ሰላም የማደፍረስ እንቅስቃሴን ከአጋሮቻችን ጋር ለመጋፈጥ እንሰራለን” በማለት ቃል ገብለዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ እና ከዚያም ባሻገር ሽብርተኞችን ትደግፋለች ሲሉ ይከሷታል። ኢራን የገንዘብ፣ የሥልጠናና የመሳሪያ ድጋፍ ለሊባኖሱ ሔዝቦላህ፣ ለፍልስጥኤሙ ሐማስ እና በጋዛ ሰርጥ ለሚንቀሳቀሰው እስላማዊ ጂሃድ ትሰጣለች።

ኢራን በበኩሏ ሽብርተኝነትን ትደግፋላች በሚል የሚቀርብባትን ክስ በማስተባበል፣ ድጋፍ የምታደርግላቸው ድርጅቶች በእስራኤልና በአሜሪካ የሚፈጸሙ ወረራዎችን የሚከላከሉ ቡድኖች ናቸው ትላለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢራን እያካሄደችው ባለው የኑክሌር ፕሮግራም ምክንያት ከአሜሪካ እና ከምዕራባውያን አገራት ጋር ለረጅም ጊዜ ፍጥጫ ውስጥ ቆይታለች።

ኢራን የምታካሂደው የኑክሌር ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ለሰላማዊ ዓላማ የሚውል ነው በማለት በተደጋጋሚ ብትናገርም፣ ምዕራባውያን አገራትንና ዓለም አቀፉ የኑክሌር ተቆጣጣሪ አካልን ግን ለማሳመን አልቻለችም።

አሜሪካ እና እስራኤል በተደጋጋሚ ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንድትሆን እንደማይፈቅዱ ቢያሳውቁም በምን አይነት ዘዴ በሚለው ላይ ግን የተለያየ ሐሳብ ነው ያለቸው።

ባይደን በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውድቅ የሆነውን ስምምነት እንደገና በማንሰራራት ተጨማሪ ጠንካራ ሐሳቦችን ተካተውበት ተግባራዊ እንዲሆን ሐሳብ አላቸው።

እስራኤል ደግሞ አስፈላጊ ከሆነ ኃይልን ጭምር በመጠቀም የኢራን የኑክሌር ፕሮግራም ሙሉ ለሙሉ መቆም አለበት ብላ ታምናለች።

በእስራኤል በጉብኝት ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ባይደን ቻናል 12 ከተባለ የእስራኤል ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይም “የመጨረሻ አማራጭ ሆኖ ከቀረበ” በኢራን ላይ ኃይል ለመጠቀም አሜሪካ ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል።

ባይደን ነገ አርብ በወረራ ወደተያዘችው ዌስት ባንክ በማምራት ቤተልሔም ውስጥ ከፍልስጥኤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ጋር ይወያያሉ ተብሏል።

ፕሬዝዳንቱ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚያደርጉት ጉብኝት ዋነኛ ትኩረት የሆነው ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚያደርጉት ጉዞ ሲሆን፣ ሳዑዲ ባላት የሰብአዊ መብት አያያዝ የተናሰ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ይገኛል።

ባይደን በጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያ ውስጥ እጃቸው አለበት በሚል በአሜሪካ የደኅንት ተቋማት ከሚከሰሱት ከልዑል ሞሐድ ሰልማን ጋር ቅዳሜ ዕለት የሚያደርጉት ውይይት ትችት አስከትሎባቸዋል። ልዑሉ ግድያውን ሲያስተባብሉ የሳዑዲ ዐቃቤ ሕግ ደግሞ በአገሪቱ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ውስጥ ያሉ ሕገ ወጦች የፈጸሙት ነው ይላል።

ጆ ባይደን በዚህ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝታቸው ከእስራኤል በቀጥታ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመብረር የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ።

ከዚህ በፊት ተደርጎ የማይታወቀው ይህ አይነቱ በረራ ቀላል መስሎ ቢታይም፣ ፍልስጥኤማውያንን በመደገፍ ለአስርታት ከአስራኤል ጋር ግንኙነት ሳታደርግ ከቆየችው ሳዑዲ አንጻር መሻሻሎች እንዳሉ የሚያሳይ ምልክት ነው ተብሏል።