በኢትዮጵያ አቅም የሌላቸው ሰዎች በጸና ሲታመሙ ሕክምና እንዴት ሊያገኙ ይችላሉ?

በሆስፒታል ተኝቶ ሕክምና እያገኘ ያለ ሰው እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዶ/ር ቅድስት መላኩ ትዊተር ገጽ አንዳንዴ እንደ ‘ጎ ፈንድ ሚ’ ያደርገዋል። ወዶ አይደለም።

ነፍስ ለማዳን ስለሚተጋ ነው። ተሳክቶለትም ያውቃል። ከአንዴም ሁለት ሦስቴ።

ነገሩ እንዲህ ነው።

የምትሠራበት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በ‘ነፍስ ውጪ - ነፍስ ግቢ’ ላይ ያሉ ታማሚዎች ይመጣሉ።

ይሄኔኮ ለመዳን አንዲት እንክብል ትሆናለች የምታስፈልጋቸው፤ አንድ ብልቃጥ ሽሮፕ ይሆናል በሕይወት የምታቆያቸው። ያን መግዛት ግን ያቅታቸዋል።

እና ምን አማራጭ አላት? መቼስ ሰው ሲሞት ዝም ተብሎ አይታይ ነገር።

ዶ/ር ቅድስት ግራ ሲገባት ወደ ትዊተሯ ታማትራለች። አዋጡ ለማለት።

የሥራ ባሕሪዋ በየዕለቱ ብዙ ያሳያታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ለምሳሌ 10 ብር ይዘው ሆስፒታል የሚመጡ ታካሚዎች አሉ። 10 ብር ምን ይገዛል? ለካርድ ማውጫ እንኳን ይሆናል?

አንዳንዴ ደግሞ የጎዳና ልጆች መንገድ ላይ ወድቀው ሲጣጣሩ ሰው አፋፍሶ ይዟቸው ይመጣል።

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ፖሊስ ከሞት ደጅ ያሉ ታማሚዎችን ይዞ ይመጣል። በተለይ የጎዳና ነዋሪ ልጆችን።

“በዚህ መልኩ ሲመጡ ብዙውን ጊዜ በድንገተኛ ነው የምንቀበላቸው” ትላለች ዶ/ር ቅድስት።

ለእነዚህ ዜጎች ካርድ ማውጣት ሰለማይቻል ሆስፒታል ውስጥ የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች [ሶሻል ዎርከርስ] ይቀበሏቸዋል።

“ከእነሱ ጋር በመሆን ግቢ ውስጥ ያሉ ነገሮችን በፊርማ እና በማኅተም በምናምን እናደርግና ለጊዜው እንጨርሳለን” ትላለች ዶ/ር።

ችግሩ የሚሆነው መድኃኒት እና ላቦራቶሪ ምርመራ ሲታዘዝ ነው።

ሆስፒታል ውስጥ ሁሉም ነገሮች ተሟልተው አይገኙማ።

አንዱ ሲኖር አንዱ አይኖርም።

“ያን ጊዜ ነው ችግር ውስጥ የምንገባው። ሰዎችን መለመን እንጀምራለን።”

በዚህ ጊዜ ሆስፒታሉ ውስጥ ምን ይከሰታል?

በቃ እዚያው ሆስፒታል ውስጥ ያለው ነርስ፣ ሐኪም፣ ጽዳት ሠራተኛ ሳይቀር አዋጡ ይባልና እሱን ሰብስበው አንድ ነገር ለማድረግ ይሞክራሉ።

የሚደንቀው አዋጡ ከሚባሉት ውስጥ አንዳንዴ እዚያው አልጋ የያዙ ታካሚዎችም ይኖሩበታል። ቢቸግር ነው።

ይህ አካሄድ ግን ብዙውን ጊዜ ብዙ ርቀት አያስኬድም።

ከአልጋ ተነስቶ ለኔም አዋጡልኝ ሊል የሚችል ታካሚም አይጠፋም።

ለራሱ እንኳ በቂ ሳይኖረው መድኃኒት ተካፍለን እንዋጥ የሚል ቅን፣ ነገር ግን የዋሕ ታካሚም አይጠፋም።

“በተለይ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ከቀን ይልቅ ሌሊት ላይ ሲገጥሙን እንቸገራለን። ምክንያቱም ሌሊት ሰው አይኖርማ” ትላለች ዶ/ር።

አዋጡ ለማለትም እኮ ሰው መኖር አለበት።

በዚህ የተነሳ ሌሊት ላይ ወደ ሆስፒታል የሚመጡ የጎዳና ልጆች ይቸገራሉ።

ዶ/ር ቅድስት አንድ ሁለት አጋጣሚዎቿን ራሷ ብትተርክልን ነገሩን ይበልጥ ያሳይ ይሆን?

ሐኪሞች በቀዶ ሕክምና ላይ

የፎቶው ባለመብት, BLACK LION HOSPITAL

መተንፈስ የተቸገረው ልጅ

አንድ ወቅት አንድን የጎዳና ልጅ ሌሊት ይዘው መጡ። ራሱን ስቶ ነበር የመጣው።

‘እትዬ’ የሚባል ማኅበር ነገር አለ፤ በጥቁር አንበሳ። ተማሪዎች የመሠረቱት።

በወር ከዚህም ከዚያም ተብሎ ወደ 50ሺህ ብር በጀት አላቸው።

አንዳንድ ጊዜ ጎዳና ተዳዳሪዎች ታክመው መድኃኒት መግዣ ሲያጡ እነሱ እንዲገዙልን እናደርጋለን።

የሆነ ጊዜ ለምሳሌ ማሳደጊያ ይኖር የነበረ ልጅ መጣ። የሳንባ እና የልብ ችግር ነበረበት።

ካለኦክስጅን ብዙ መቆየት አይችልም።

ለመጀመሪያ ጊዜ ሶሻል ሚዲያ ላይ ወጥቼ እርዱኝ ለማለት ያደረሰኝ ይህ ልጅ ነው።

ይህ ልጅ ብዙውን ጊዜ ሆስፒታል ይመጣል። ሆስፒታል የሚመጣው ለኦክሲጂን ነው፤ መተንፈስ ሲቸገር።

ኦክሲጅን ስናረግለት መሻሻል ያሳያል። ማሳደጊያ ድርጅቱ ኦክሲጅን ሊገዛለት አቅም የለኝም አለ።

በዚህ የተነሳ የልጁ ኦክሲጅን መጠኑ ወርዶ ወርዶ አንዳንድ ቀን በጣም ዝቅተኛ ከሚባለው ደረጃ ይደርሳል።

መተንፈስ ሲቸገር ሐኪም ቤት ተሸክመው ያመጡታል። እኛ ኦክሲጂን ላይ እናደርገዋለን።

ነገር ግን ኦክሲጂን በቀጣይነት ያስፈልገዋል። አለበለዚያ ለሕይወቱ አደገኛ ነው። በቃ ምን እናድርግ? ይህን ልጅ ማትረፍ አለብን ብለን ተነሳን።

ያን ጊዜ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ኦክሲጂን 30ሺህ ነበር።

ኪኒን መግዣ እንኳ የሌለው ልጅ እኮ ነው። 30ሺህ ብር አምጣ ብንለው ከየት ያመጣዋል?

ለምን ‘ኦክስጂን ኮንሰንትሬተር’ አንገዛለትም ተባብለን ከጓደኞቼ ጋር በቃ የቻልነውን ማሰባሰብ ጀመርን።

አልሞላ ሲለን ወደ ሶሻል ሚዲያ ወጥተን ለመንን። ትዊተር ላይ “መርዳት የምትቸሉ ሰዎች ተባበሩኝ አልኩ።”

በመጨረሻ አንዳንድ ሰዎች የኦክስጂን ሲሊንደር ሰጡት። ሌሎች መድኃኒት ገዙለት። ተጨማሪ እርዳታ እናደርግለታለን ያሉም ነበሩ።

በ12 ሰዓት ውስጥ ደጋግ ሰዎች ተረባርበው የምንፈልግን አገኘን።

በአጭር ሰዓት ምን ያህል ሰው እንደተረባረበለት ሳይ ልቤ ተነካ። ለካስ ሰብአዊነት ጨርሶ አልጠፋም አልኩኝ።

በሚቀጥለው ቀን ኦክሲጂን ኮንሰንትሬተሩን ገዛንለት። የሚያስፈልጉ መድኃኒቶች እና የጤና መድኅን ዓመታዊ ምዝገባ አደረግንለት።

ምክንያቱም በጤና መድኅን ሥር ሲሆን ቢያንስ መድኃኒቶቹ ይሸፈኑለታል። ሆስፒታል ሲመጣ በነጻ ይታከማል። ከነማ መድኃኒት ሲገዛ ነጻ ይሆንለታል።

አሁን በጣም ጥሩ ነው ያለው። አልፎ አልፎ ይደውልልኛል።

በደወለልኝ ቁጥር መጀመሪያ እግዚአብሔርን ነው የማመሰግነው፤ ቢያንስ አንድ ሰው እንድረዳ አስችሎኛልና።

ሆስፒታል ተኝቶ የሚታከም ታዳጊ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

“ኧረ ልጄ እኔ 200 ብር ናት በኪሴ ያለችኝ”

ሌላ ጊዜ ደግሞ ዘውዲቱ ጽኑ ሕመምተኞች ክፍል ተኝቶ የነበረ ልጅ ነበር።

ልጁ ቀስ በቀስ እግሩን ሽባ የሚያደርግ በሽታ ነበር ህመሙ።

ኢሚኖግሎቢን የሚባል መድኃኒት መውሰድ አለበት። መድኃኒቱ ግን አንደኛ በጣም ውድ ነው፤ ሁለተኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም የሚገኝ ነገር አይደለም።

በቀን አንድ ጊዜ ለመውሰድ ወደ 34 ሺህ ብር ያስፈልጋል።

እና ይህ ልጅ ፓራሊሲስ እንዳያጋጥመው ይህን ውድ መድኃኒት ለ5 ቀን መውሰድ ነበረበት። አለበለዚያ ፈጣሪ ብሎ ቢድን እንኳ በዊልቸር ነው የሚኖረው።

አባትየውን ጠርተን “እንዲህ ዓይነት መድኃኒት አለ፤ መግዛት ይችላሉ ወይ?” ስንላቸው “አዎን” አሉን።

በሰዓቱ የተረዱንም አልመሰለኝም።

ከዚያ ወጥቼ “አባባ ይህ መድኃኒት እኮ እንዲህ ያህል ገንዘብ ያስወጣዎታል” ስላቸው “እረ ልጄ 200 ብር ናት በኪሴ ያለችኝ” ብለው እሱን ሰጡኝ።

ግራ ገባን።

የመጀመሪያውን ዙር መድኃኒት የሰውየው አሰሪዎች ሸፈኑላቸው።

ከዚያ ግን ገንዘብ ከየት ይምጣ። ልጁ መድኃኒቱን ካላገኘ አደጋ ነው። በቃ እንደለመድኩት ወደ ትዊተር ወጣሁ።

ደጋግ ሰዎች ወደ 110ሺህ ብር አዋጡለት።

5ቱን ‘ዶዞች’ ወሰደ። ይህ ልጅ ከሆስፒታሉ በእግሩ ተራምዶ ነው የወጣው።

ከዚህ በላይ ምን የሚያስደስት ነገር አለ? እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ስታይ አመስጋኝ እንድትሆን ያደርግሃል።

ለስንቱ አዋጡ ተብሎ ይዘለቃል?

ዶ/ር ቅድስት ትዊተር ሜዳ ወጥታም ቢሆን ሰው ማዳን ፈጣሪዋን እንድታመሰግን ያደርጋታል።

መለመን እስከመቼ ማለቷ ግን አልቀረም።

“የችግራችን ስፋት ወሰን የለውም። አንዱን ችግር እየቀረፍክ እያለ የባሰ ይመጣል። አንዱን ረዳሁ ብለህ ዞር ስትል ሌላው ይመጣል። በቃ ግራ ይገባሃል” ትላለች።

ታዲያ ምንም መጠጊያ የሌላቸው ሰዎችን ዘላቂ መድኅን መስጠት የሚቻለው እንዴት ነው?

ብዙ ሆስፒታሎች የድጋፍ ደብዳቤ ይፈልጋሉ። የድሃ ድሃ እንኳ ለማጻፍ ትንሽ ገንዘብ ማስፈለግ ጀምሯል።

ደብዳቤ ተጽፎ ቀበሌ መስክሮ በስንት መከራ ነው የድሃ ድሃ ደረጃ ራሱ የሚገኘው።

የትኛው ቀበሌ ነው ለእነዚህ ቤታቸው ጎዳና ለሆነ ልጆች ኃላፊነት ወስዶ የሚጽፈው? ሲጀመር ቀበሌ መታወቂያስ አላቸው?

“የግድ ከሆነ ውጭ አገር ልከንም እናሳክማቸዋለን”

አቶ እርቅይሁን አሸናፊ የሆፕ ፎር ጀስቲስ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ፕሮግራም ማናጀር ናቸው።

ድርጅታቸው የጎዳና ልጆች ላይ ነው የሚሠራው። በአገር ደረጃ 6 ማዕከላት አሏቸው።

በሱስ ብዙ የተጎዱ፣ የታመሙ፣ ጎዳና የወደቁ ልጆችን ቅድሚያ ሰጥተው ይቀበላሉ።

እነርሱ ዘንድ መልከ ብዙ የጤና ቅርቃር ውስጥ የገቡ ልጆች ያጋጥሟቸዋል።

አካላቸው ተደብድቦ፤ ጎዳና ተደፍረው የሚመጡ ሴቶችም ወንዶችም ይኖራሉ።

በቤት ሠራተኝነት ገብተው ጉልበታቸው ተበዝብዞ ጎዳና ወጥተው በእነሱ ድርጅት የሚነሱም አሉ።

በሱስ ክፉኛ የተጎዱ፣ በሳምባ ምች የተጠቁ፣ በኤችአይቪ የተያዙም አልፎ አልፎ ያጋጥማሉ።

በብዛት ደግሞ የአእምሮ ጤና እክል ያጋጠማቸው ይመጣሉ፤ በተለይ ሴቶች።

በገዛ ወላጅ አባቷ ከተደፈረች ሴት ጀምሮ ብዙ ለመስማት የሚከብዱ ነገሮች ያጋጠሟቸው አዳጊ ልጆች ጎዳና ላይ ይገኛሉ።

“ካለው ችግር አንጻር የእኛ ድርጅት ሥራ ኢምንት ነው። ጎዳና ያሉት ሕጻናት እልፍ ናቸው። ብዙ ሰዎች መረባረብ አለባቸው” ይላሉ፤ አቶ እርቅይሁን።

ይሁንና ሆፕ ፎር ጀስቲስ ድርጅት በዓመት በትንሽ ቁጥር ልጆችን ከጎዳና ቢያነሳም፤ ከጎዳና አንስቶ ቢያሳክምም፤ አሳክሞ ከቤተሰባቸው ጋር ቢቀላቅልም በሚሰጣቸው ክብካቤ ግን ስስት የሚታይበት አይመስልም።

ብዙዎችን ከመድረስ ይልቅ የጥቂቶችን ሕይወት መለወጥ ላይ ያተኮረ ይመስላል።

“ልጆቹ እኛ ጋ ከገቡ በኋላ ሙሉ ፓኬጅ ሕክምና ያገኛሉ” ይላሉ አቶ እርቅይሁን።

ሲጀመር ጀምሮ፣ ድርጅቱ ልጆቹን ከጎዳና ሲቀበላቸው ቅድሚያ መሠረታዊ የጤና ምርመራ በማድረግ ነው።

ልብሳቸው ይቀየራል። ቁስል ካለባቸው በራሳቸው ክሊኒክ ይታከማሉ። በ24 ሰዓት ውስጥ ደግሞ ከፍ ወዳለ ሆስፒታል ተልከው

ሄፒታይተስ ቢ፣ ኤችአይቪ እና የመሳሰሉ በሽታዎችን ምርመራ ያደርጉላቸዋል።

ይህ ብቻ አይደለም ታዲያ፤ የአመጋገብ ሥርዓታቸው ይስተካከላል። መኝታ ለብቻ ይደረግላቸዋል።

ከተረጋጉ መኋላ የማማከር [ካውንስሊንግ] አገልግሎት ይሰጣቸዋል።

ወደ ማዕከሉ የገቡት የጎዳና ልጆች እስከ ቀዶ ሕክምና እንኳ ቢያስፈልጋቸው ድርጅቱ በተፈራረማቸው ትልልቅ የግል ሆስፒታሎች ወስዶ ያሳክማቸዋል።

አይበለውና አንድ ከጎዳና የተነሳ ልጅ የከፋ ሕመም ገጥሞት የውጭ ሕክምና ቢፈልግ ድርጅታቸው ወጪውን ይሸፍናል።

“አስር አገራት ላይ ስለምንሠራ የአውሮፕላን ወጪ ችለን እናሳክመዋለን” ይላሉ አቶ እርቅይሁን።

እርግጥ ልጆቹ ከኖሩት የሰቆቃ የጎዳና ሕይወት ጋር ሲነጻጸር በዚህ ድርጅት የሚያገኙት አገልግሎት ለማመንም የሚከበድ ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

“ምክንያቱም የእኛ ድርጅት የሚያስበው ወጪውን ሳይሆን የልጁን ሕይወት ማዳን ከዚያም መቀየር ነው” ይላሉ ኃላፊው።

የጎዳና ልጆች በጤና መድኅን ለምን አይታቀፉም?

እንደ ሆፕ ፎር ጀስቲስ ያሉ ብዙ አይደሉም። የጎዳና ላይ ልጆች ደግሞ ቁጥር ስፍር የላቸውም።

ቢያንስ ነጻ ሕክምና እንዴት ነው ሊያገኙ የሚችሉት? እንኳንስ ሕክምና የሚቀምሱትን የት አገኙና የሚል አይጠፋም።

ቢሆንም ጤናቸው ሲቃወስ፣ በሕመም ሲሰቃዩ መቼስ አንዳች ሕክምና ማግኘት አለባቸው።

በእኛ አገር የጤና መድኅን ሥርዓቱ የተጀመረው በቅርብ ነው።

ወ/ሮ ፍሬሕይወት አበበ የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

ይህን ነገር አንስተንባቸው ነበር፤ መጀመሪያ የጤና መድኅን አገልግሎቱን በሁለት ይከፍሉታል።

አንዱ ‘ማኅበራዊ ጤና መድኅን’ የሚባለው ነው።

የመንግሥት ሠራተኛውንና ተቃጣሪን የሚያካትት ነው። ይህ ግን ከሕዝባችን 17 ከመቶውን ብቻ ነው የሚሸፍነው።

ሁለተኛው ‘ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን’ ይባላል።

ይህ መደበኛ ባልሆነው ኢኮኖሚ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ያካትታል።

አርብቶ አደሩ፣ አርሶ አደሩ፣ ጥቃቅን እና አነስተኛ የሚነግደው፣ በአጠቃላይ ፔሮል የማያውቀውን ዜጋን በሙሉ ይመለከታል።

ይህ ማዕቀፍ 83 ከመቶ ሕዝባችንን ይይዛል።

የጎዳና ልጆች የትኛው ላይ ነው ያሉት?

ወ/ሮ ፍሬሕይወት ይህ ጥያቄ ፈተና ሆኖ እንደቆየ ያወሳሉ።

ምክንያቱም የጤና መድኅን ሥርዓቱ በጎዳና ሳይሆን በቤተሰብ ደረጃ ስለሚሠራ ነው።

“እስከአሁን በነበረን አካሄድ ለጤና መድኅን በቤተሰብ ደረጃ ነበር ምዝገባው” ይላሉ።

ስለዚህ የጎዳና ልጆችን አያካትትም ነበር።

አሁን ግን አዲስ ነገር አለ።

አዲስ በወጣው አዋጅ የጎዳና ልጆችን ጨምሮ ከድህነት ወለል በታች ያሉ 23.4 በመቶ ዜጎችንም በጤና መድኅኑ ይካተታሉ።

ወጪያችን ደግሞ መንግሥት ከዚያም ከዚህም ብሎ ይደጎመዋል።

ይሁንና ምዝገባው አሁንም የድሃ ደሃን እንጂ ጎዳና ተዳዳሪዎችን አያካትትም። ቀደም ያለው ሕግም በግለሰብ ደረጃ አባል እንዲሆኑ አይፈቅድም ነበር።

“ይህ ጉድለት ሆኖ ስለተገኘ በግለሰብ ደረጃ አባል እንዲሆኑ ተወስኗል” ይላሉ ዳይሬክተሯ።

ማነው የሚመዘገብቸው ታዲያ? የሚለው አሁንም አልተመለሰም።

ወ/ሮ ፍሬሕይወት ለዚህ እንቆቅልሽ የሚሰጡት ምላሽ ይህ ኃላፊነት የክልሎች መሆኑን ነው።

“አዋጁ የክልል መንግሥታት ለጎዳና ልጆች የጤና ሽፋን ሊገዙላቸው ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል” ይላሉ።

ይህን ግን እያደረጉ አይደለም።

“ሕጉ ለጎዳና ልጆች መብት ሰጥቷቸዋል። ተግባራዊ ማድረግ ግን ቀላል አይደለም፤ እየሠራንበት ነው” ይላሉ ወ/ሮ ፍሬሕይወት።

በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2023 ዓ.ም. ‘ሁሉም ዜጋ’ ከኪሱ ሳይከፍል በጤና መድኅን ታቅፎ ሕክምና ያገኛል ተብሎ እየተሠራ ነው።

የጎዳና ልጆች፣ “ሁሉም ዜጋ” በሚለው ሐረግ ውስጥ አሉ ወይስ የሉም?