አሜሪካ የወሮበሎች ብጥብጥን ተከትሎ የኤምባሲ ሠራተኞቿን ከሄይቲ አስወጣች

ሄይቲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ በወሮበላ ቡድኖች አመጽ እየታመሰች ካለችው ሄይቲ መሠረታዊ ያልሆኑ የኤምባሲ ሠራተኞችን ከአገሪቱ በአየር ማስወጣቷን ገለጸች።

አሜሪካ በሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት-አው -ፕሪንስ በሚገኘው ሚሽኗ የጸጥታ ጥበቃንም አጠናክራለች።

በዚህ ሳምንት በአውሮፕላን ማረፊያ፣ በፖሊስ ጣቢያዎች እና በማረሚያ ቤቶች ላይ ጥቃት ያደረሱት ወሮበሎች የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪዬል ሄንሪ ከስልጣን እንዲወርዱ ግፊት እያደረጉ ነው።

ለሦስት ቀናት ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአንድ ወር ተራዝሟል።

"በዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ አካባቢ እና በአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ በተፈጠረው የወሮበሎች ጥቃት ምክንያት የስቴት ዲፓርትመንት ተጨማሪ የኤምባሲ ሠራተኞች ለቀው እንዲወጡ ወስኗል" ሲል ኤምባሲው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለጥፏል።

ኤምባሲው ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም አክሏል።

በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች የሄሊኮፕተር ድምጽ መስማታቸውን በመጥቀስ ከማለዳ በፊት የተደረገው ዘመቻ በሄሊኮፕተር የተካሄደ መሆኑን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

እሁድ እለት በሄይቲ የጀርመን አምባሳደርም ከሌሎች የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች ጋር ወደ ዶሚኒካን ሪፓብሊክ መሄዳቸውን የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዜና ወኪሉ ተናግሯል።

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ ወደ ክልላዊ ስብሰባ ሲሄዱ ወሮበሎች ጥቃታቸውን አጠናክረዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ ዕለት ወደ ፖርት-አው-ፕሪንስ ለመመለስ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ መዳረሻቸውን ለመቀየር ተገደዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መዳረሻቸውን የቀየሩት ታጣቂዎች በዋና ከተማዋ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለመቆጣጠር መሞከራቸውን ተከትሎ አየር ማረፊያው በመዘጋቱ ነው።

ሄንሪ ኬንያን ከጎበኙ በኋላ ምንም አይነት የህዝብ መግለጫ አልሰጡም። ሚኒስትሩ ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ተገናኝተው ምስራቃዊ አፍሪካዊቷ ሀገር የሄይቲን ፀጥታ ወደ ነበረበት ለመመለስ የተደረሰውን ስምምነት ለማዳን ነው።

ሁለቱ መሪዎች 2,000 የኬንያ ፖሊሶች ወደ ሄይቲ እንዲላኩ መንገድ የሚከፍት ስምምነት ተፈራርመዋል ነገር ግን አንድ የኬንያ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ስምምነቱን ፍርድ ቤት ወስደውታል።

በፖርት-አው-ፕሪንስ ውስጥ ያሉ ወሮበሎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን አለመኖር በመጠቀም ተከታታይ የተቀናጀ ጥቃቶችን ፈጽመዋል።

ከእስረ ቤቶችም በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን አስመልጠዋል።

ብጥብጡ የሄይቲ ሰብአዊ ቀውስ የበለጠ እንዲባባስ አድርጓል።

ወሮበሎቹ ሄንሪን ከስልጣን ከማስወገድ ባለፈ አላማቸው ምን እንደሆነ አልተናገሩም።

ጂ9 የተባለውን የወንበዴ ቡድኖችን ጥምረት የሚመራው የቀድሞ የፖሊስ አባል ጂሚ ሼሪዢየር (ባርቤኪው)፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሄነሪ ከስልጣን የማይወርዱ ከሆነ “የእርስ በርስ ጦርነት” እንደሚኖር ዝቷል።

ብጥብጡ 362,000 የሄይቲ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉን የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ተናግሯል። ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህጻናት ናቸው።

በሄይቲ የአይኦኤም ኃላፊ ፊሊፕ ብራንቻት በሰጡት መግለጫ “ሄይቲ ሰዎች ጥሩ ኑሮ መምራት አልቻሉም። በፍርሃት እየኖሩ ነው፣ እና በየሰዓቱ ይህ ሁኔታ እየቀጠለ ነው፣ ጉዳቱ እየባሰ ይሄዳል” ብለዋል።