የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የፈፀመውን የጅምላ ግድያ ለመሸፈን እየሞከረ መሆኑን ተመራማሪዎች ገለጹ

የሱዳን ፈጣን ደራሽ ኃይሎች በኤል ፋሸር ከተማ የፈጸሙትን የጅምላ ግድያ አስከሬኖቹን በመቅበር እና በማቃጠል ለመሸፈን እየሞከሩ መሆኑን የዬል ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን አስታወቀ።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) በጥቅምት ወር ታጣቂዎቹ ከተማዋን ሲቆጣጠሩ በፈጸመው የጅምላ ግድያ እና በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ምክንያት ዓለም አቀፍ ውግዘት ደርሶበታል።

አሁን የዬል ዩኒቨርስቲ የሰብዓዊ ምርምር ላብራቶሪ (ኤችአርኤል) የሳተላይት ምስሎችን በመመልከት በሰራው ትንታኔ መሠረት አርኤስኤፍ ኤል ፋሸርን ከያዘ በኋላ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አስከሬኖችን አስወግዷል።

አርኤስኤፍ ለሪፖርቱ ምላሽ አልሰጠም፤ ነገር ግን የታጣቂ ቡድኑ መሪ ቀደም ሲል ተዋጊዎቹ በከተማው ውስጥ አንዳንድ ጥሰቶችን እንደፈጸሙ አምነዋል።

የዬል ዩኒቨርስቲ የምርምር ቡድን በሪፖርቱ ላይ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ "የጅምላ ግድያ ማስረጃዎችን ለማጥፋት ለብዙ ሳምንታት የዘለቀ ስልታዊ ዘመቻ አካሂዷል" ብሏል።

ሪፖርቱ አክሎም ቡድኑ አስክሬኖችን ማቃጠሉን እና ደብዛቸው እንዳይገኝ ማድረጉን እንደቀጠለበት ገልጿል።

በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ እና በሱዳን ጦር መካከል በተፈጠረ የሥልጣን ሽኩቻ የተነሳ እአአ ከሚያዚያ 2023 ጀምሮ ውጊያ እየተካሄደ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግጭቱ በዓለም ላይ እጅግ አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ አስክትሏል ብሏል።

አርኤስኤፍ ኤል ፋሸርን ለ18 ወራት ከብቦ ከቆየ በኋላ በቁጥጥሩ ሥር ማዋል የቻለ ሲሆን ይህም ሠራዊቱን ከሰፊው የዳርፉር ክልል እንዲያወጣ አድርጓል።

ኤል ፋሸር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እጅ ከገባ በኋላ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጭፍጨፋ ፈጽሟል ከሚሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል አንዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነበር።

የዬል ዩኒቨርስቲ የሰብዓዊ ምርምር ላብራቶሪ በከተማዋ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለወራት ሲከታተል የቆየ ሲሆን፣ የቅርብ ጊዜ ሪፖርቱም የከተማዋ ነዋሪዎች የደረሰባቸውን ጥቃት መጠን ለመረዳት የሚያደረገው ጥረት አንዱ አካል ነው።

የምርምር ቡድኑ የሳተላይት ምስሎች ላይ የተደረገው አዲስ ትንተና ኤል ፋሸር በታጣቂዎቹ እጅ ከገባች በኋላ ባሉት ሳምንታት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የአስክሬን ክምሮች መጠናቸው እንደተለወጠ ያሳያል ብሏል።

ይህ ደግሞ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን ማስረጃዎች ለማጥፋት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እያደረገ ያለውን ቀጣይነት ያለው ጥረት የሚያሳይ መሆኑን አክሎ ገልጿል።

ምስሎቹ ከከተማው ውጭ የሚገኙ ከ80 በላይ የአስከሬን ክምሮች ያሉባቸውን ስፍራዎች ያሳያሉ።

ኤችአርኤል እንደሚለው ይህ የሚያሳየው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሰዎች ለመሸሽ ሲሞክሩ እየገደለ እንደነበር ነው።

የዬል ዩኒቨርስቲ የምርምር ቡድን በኅዳር ወር ያገኛቸው የሳተላይት ምስሎች ከተማዋ ከተያዘችበት ጊዜ ጀምሮ የሰላማዊ ሰዎች እንቅስቃሴ የተገደበ መሆኑን ያሳያሉ።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የደረሰበትን ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ተከትሎ፣ ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ኤል ፋሸርን በቁጥጥር ስር በማዋል ወታደሮቻቸው የፈጸሟቸውን ጥሰቶች በተመለከተ ምርመራ እንዲደረግ አዝዘዋል።

ይሁን እንጂ ቡድኑ በከተማው ውስጥ የሚፈጸሙ ግድያዎች በብሔር ላይ የተመሰረቱ ናቸው የሚለውን ሰፊ ​​ውንጀላ ውድቅ ማድረጉን ቀጥሏል።

የቅርብ ጊዜው የዬል ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ሪፖርት ይፋ የሆነው አርኤስኤፍ ኤል ፋሸርን ከተቆጣጠረ በኋላ ከከተማዋ ለማምለጥ የቻሉ ሰዎች ቁጥር በጣም ዝቅተኛ መሆኑን በተመለከተ ከእርዳታ ድርጅቶች የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎችን ተከትሎ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በከተማዋ ውስጥ ወደ 250,000 የሚጠጉ ሰዎች ይኖሩ እንደነበር እንደሚገመት ጠቅሶ ከዚህ ቁጥር ውስጥ ከግማሽ በታች የሚሆኑት ሸሽተው ወደ መጠለያ ጣቢያዎች መምጣት መቻላቸውን ገልጿል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ኤል ፋሸርን በእጃቸው ማስገባታቸውን ተከትሎ በምዕራብ ሱዳን ሥልጣናቸውን አጠናክረዋል።

እንዲሁም በዳርፉር ከተማ ኒያላ ውስጥ ትይዩ መንግሥት አቋቁመዋል።

የሱዳን ጦር አሁንም አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል እየተቆጣጠረ ሲሆን በሁለቱ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ውጊያ ተባብሶ እንደቀጠለ ነው።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ከሚያዚያ 2023 ጀምሮ ከ13 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል ተብሎ ይታመናል።