በኢትዮጵያ ስደተኞች ለከፍተኛ ረሃብ መጋለጣቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስጠነቀቀ

የፎቶው ባለመብት, WFP
የመንግሥታቱ ድርጅት የምግብ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች የረሃብ አደጋ ላይ መውደቃቸውን አስጠንቅቋል።
ድርጅቱ የረሃብ አደጋው የጨመረው በገንዘብ እጥረት ምክንያት የምግብ ክፍፍሉን ለመቀነስ በመገደዱ መሆኑን ገልጿል።
በጥቅምት ወር የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በ27 መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ 780 ሺህ ስደተኞች፤ 60 በመቶ የነበረውን የምግብ ክፍፍል (ራሽን) ወደ 40 በመቶ ዝቅ እንዲያደርግ መገደዱን አስታውቋል።
ይህም ማለት እያንዳንዱ ሰው የሚያገኘው የምግብ እርዳታ በቀን ከአንድ ሺህ ካሎሪ በታች ነው።
ከጎረቤት አገራት ከሱዳን እና ደቡብ ሱዳት ግጭትን ሸሽተው የመጡ 70 ሺህ የሚሆኑ አዲስ ስደተኞች ብቻ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሙሉ ራሽን ያገኛሉ ብሏል።
አዲስ በሚገቡ ስደተኞች ረሃብ እና ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑንም ድርጅቱ ገልጿል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር እና ተወካይ ዝላታን ሚሊሲክ "የማይቻል ምርጫ እየመረጥን ነው" ብለዋል።
"በምንችለው ልክ ለበርካታ ስደተኞች ትርጉም ያለው መጠን የምግብ እርዳታ ለማቅረብ እየሞከርን ነው። ይሁን እንጂ ገንዘብ የማናገኝ ከሆነ እነዚህ ቅነሳዎች ሙሉ ለሙሉ የምግብ ስርጭቱ እንዲቆም የሚያደርግ፤ አሁን እየረዳናቸው ያሉ ሕይቶችን አደጋ ላይ የሚጥል ነው" ሲሉ ገልፀዋል።
"ይህ የወዲፊት አደጋ አይደለም፤ አሁን እየሆነ እንጂ። እያንዳንዱ የምግብ ቅነሳ ሕፃን ልጅን ረሃብ ላይ የጣለ ነው፤ እናት ምግብ እንድትዘል የሚያስገደድ፣ ቤተሰብ አፋፍ ላይ እንዲሆን የሚገፋፋ ነው" ሲሉ ተፅዕኖውን አብራርተዋል።
የዓለም የምግብ መርሃ-ግብር በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሰብዓዊ ተልዕኮውን ለማስቀጥል በአስቸኳይ 230 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል።
አስቸኳይ ገንዘብ ካላገኘ ድርጅቱ በመጪዎቹ ወራት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሁሉም ስደተኞች ሙሉ ለሙሉ የምግብ እርታውን እንደሚያቆም አስጠንቅቋል።
ድርጅቱ ከፍተኛ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ለገጠማቸው ሕፃናት እና እናቶች የሚያቀርበው አልሚ ምግብም በአደገኛ ሁኔታ መመናመኑን ጠቅሷል።
ታኅሳስ ወር ላይ አልሚ ምግቡ እንደሚያልቅ የገለፀም ሲሆን፤ ይህም ማለት ለአንድ ሚሊዮን የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ላለባቸው ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች እና ጡት የሚያጠቡ እናቶች ተጨማሪ ገንዘብ ካላገኘ ድጋፉን ያቆማል።
ድርጁቱ ባለፈው ሚያዚያ የገንዘብ እጥረት እንደገጠማው ማሳወቁን አስታውሶ፤ በለጋሾች እርዳታ የምግብ መርሃ ግብሮቹናን ማስቀጠል ችሎ እንደነበር ገልጿል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በደቡብ ምስራቅ ሶማሌ ክልል የ700 ሺህ ሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየሰራሁ ነውም ብሏል።
አካባቢው በድርቅ እና ጎርፍ የተጎዳ መሆኑን ጠቅሶ፤ ያለውን የተወሰነ የሰብዓዊ ምግብ እርዳታ ሳይቀንስ ለማቅረብ እየጣረ መሆኑን ገልጿል።
"ተልዕኳችን ለወራት አፋፍ ላይ ሆኖ ቆይቷል" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ "ይህ የምግብ ዋስትና ለሌላቸው ኢትዮጵያዊያን እና ስደተኞች የምናቀርበውን ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለአዲስ ቀውስ ያለንን ዝግጁነት፤ ለአዲስ የስደተኞች ፍሰት፣ ድርቅ እና የአየር ንብረት አደጋዎች የምናደርገውን ጥረት ያዳክማል" ብለዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለመጨረሻ ጊዜ ለስደተኞች የምግብ ክፍፍሉን የቀነሰው እ.አ.አ ግንቦት በ2023 ነበር።
ከዚህን ጊዜ ጀምሮ በሰብዓዊ ፍላጎቱ እና በአቅርቦት ላይ ያለው ልዩነት እየሰፋ መሄዱንም ድርጅቱ አስታውቋል።
በ2025 ከጥር እስከ ጥቅምት ባሉት ወራት ድርጅቱ በኢትዮጵያ ለሚገኙ 4.7 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እርዳታ፣ አልሚ ምግብ፣ የትምህርት ቤት ምገባ እና ሌሎች የመቋቋሚያ እንቅስቃሴዎችን መደገፉን ገልፏል።
ከገንዘብ እጥረቱ ባሻገር በተለይም በአማራ ክልል የቀጠለው የደኅንነት እጦት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሰብዓዊ ሥራዎቹን ማስተጓጎሉን እንደቀጠለ ነው ሲል ባወጣቸው መግለጫ ጠቅሷል።















