አሜሪካ እጅግ ዘመናዊውን ኤፍ-35 ተዋጊ ጄት ለሳዑዲ አረቢያ ልትሸጥ ነው

አሜሪካ ኤፍ-35 ተዋጊ ጄቶችን ለሳዑዲ አረቢያ እንደምትሸጥ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር በዋይት ሐውስ ከመገናኘታቸው አስቀድሞ ነው ስለ ጄቶቹ ሽያጭ የተናገሩት።

ለሳዑዲ አረቢያ "ኤፍ-35 ጄቶችን እንሸጥላቸዋለን። ትልቅ አጋራችን ናቸው" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

መሐመድ ቢን ሳልማን እና ትራምፕ ስለ መከላከያ ስምምነት እና ስለ ሲቪል የኒውክሌር ኃይል ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከሰባት ዓመት በፊት ጋዜጠኛው ጀማል ኻሾግጂ ከተገደለ በኋላ መሐመድ ቢን ሳልማን ወደ ዋይት ሐውስ ሲያቀኑ የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው።

የአሜሪካ የደኅንነት መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ልዑል አልጋ ወራሹ የኻሾግጂን ግድያ ላስከተለው ኦፕሬሽን ይሁንታ ሰጥተዋል። ነገር ግን ልዑል አልጋ ወራሹ ግን ይህንን አስተባብለዋል።

ለመጨረሻ ጊዜ በአሜሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት በአውሮፓውያኑ 2018 ነበር።ኻሾግጂ የተገደለውም በዚያው ዓመት ቱርክ ኢስታንቡል ውስጥ ነው።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፤ መሐመድ ቢን ሳልማንን ባያስተናግዱም፤ በሳዑዲ በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት አገሪቱን "የተገለለች" ለማድረግ መዛታቸው ይታወሳል።

ባይደን በ2022 ወደ ሳዑዲ አቅንተው በተለያዩ ጉዳዩች ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። የኻሾግጂን ግድያም ማንሳታቸውን አስታውቀዋል።

ትራምፕ እና ልዑል አልጋ ወራሹ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በሪያድ ተገናኝተዋል። አሜሪካ ለሳዑዲ 142 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ለመሸጥ ውሳኔ ማሳለፏም አይዘነጋም።

ስምምነቱ "በታሪክ ትልቁ" እንደሆነ የትራምፕ ጽህፈት ቤት ዋይት ሐውስ ገልጾ ነበር። የ600 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ስምምነት ላይም ተደርሷል።

ከአሜሪካ የጦር መሣሪያ በመግዛት ሳዑዲ ግንባር ቀደም አገር ናት።

በዓለም ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የሆነውን ኤፍ-35 የጦር ጄት መሸጥን በተመለከተ የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት ጥያቄ አንስተዋል።

ለሳዑዲ ኃይል የሚሰጥ እንደሆነ እና ሳዑዲ ቴክኖሎጂውን ለቻይና ልታጋራ እንደምትችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ሳዑዲ እና ቻይና የደኅንነት መረጃ ለመለዋወጥ ስምምነት ተፈራርመዋል።

እስራኤልም የመሣሪያ ሽያጩ የደኅንነት ስጋት ሊሆንባት እንደሚችል አስታውቃለች። እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ ዋነኛ የአሜሪካ አጋር ከመሆኗ ባሻገር በቀጣናው ብቸኛዋ የኤፍ-35 ጄት ባለቤትም ናት።

የጦር መሣሪያ አምራቹ ሎክሄድ ማርቲም መረጃ እንደሚጠቁመው፤ አንድ ኤፍ-35ኤ የጦር ጀት 82.5 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ያወጣል።

ዶናልድ ትራምፕ እና መሐመድ ቢን ሳልማን ሲገናኙ ሳዑዲ አብረሃም አኮርድስን እንድትፈርም ጫና እንደሚደረግ ይጠበቃል።

ይህም የሳዑዲ እና የእስራኤልን ግንኙነት ጤናማ የሚያደርግ ይሆናል።

ሳዑዲ ይሄን ስምምነት ለመፈረም እንደ ቅድመ ሁኔታ የምታስቀምጠው የፍልስጤም አገርነት ጉዳይ ሲሆን፤ እስራኤል ይሄንን አትቀበልም።