ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤለን መስክ በእጅ ሰላምታው ምልክት ላይ ለተነሳበት ትችት ምላሽ ሰጠ
ኤለን መስክ የዶናልድ ትራምፕ ሲመተ በዓል ላይ ያሳየው የእጅ ሰላምታ ምልክት "የናዚ ነው" በሚል የቀረበበትን ከፍተኛ ትችት አጣጣለ።
ሰኞ፣ ጥር 12/ 2017 ዓ.ም ዕለት በነበረው ሲመተ በዓል የኤክስ ባለቤት ኤለን መስክ ለተሰበሰሰበው ህዝብ ይህ እንዲሆን ስላስቻሉ አመስግኖ ቀኝ እጁን ደረቱ ላይ ካደረገ በኋላ ወደ ፊት ለፊቱ በኩል ወደላይ በማውጣት አሳይቷል።
ከዚያም ዞር በማለት ከኋላው ለተቀመጡት እንደገና ድርጊቱን ደግሞታል።
ይህንንም ተከትሎ አንዳንዶች የናዚ ሰላምታ ነው ሲሉ ትችታቸውን ሲያቀርቡ ሌሎች ደግሞ አይደለም ሲሉ በኤክስ ገጽ መወዛገቢያ አድርገውታል።
በምላሹ የስፔስ ኤክስና የቴስላ ኃላፊ መስክ "በእውነቱ ከሆነ የተሻለ ማጥቂያ መንገድ መፈለግ አለባቸው። 'ሁሉም ሰው ሂትለር' ነው በሚል ያነጣጠረው ጥቃት የሰለቸ እና ያረጀ ነው" ብሏል።
የዓለማችን ባለጸጋ እና የፕሬዚዳንት ትራምፕ የቅርብ አጋር የሆነው መስክ ይህንን ምልክት ያሳየው በዋሽንግተን ዲሲ ላይ ንግግር ባደረገበት ወቅት ነው።
የ53 ዓመቱ መስክ ሁለተኛውን የሰላምታ ምልክት ከማሳየቱ በፊት "ለእናንተ ምስጋና ይግባችሁና የስልጣኔን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጠብቃችኋል" ብሏል።
ይህንን ምልክት ተከትሎ መስክ ከፍተኛ ትችት እና ወቀሳ በማህበራዊ ሚዲያዎች አስተናግዷል።
በኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ሩዝ ቤን ጂያት "የፋሺስት ነው። የናዚ የሰላምታ ምልክት ያውም ጠንከር ያለ" ብለዋል።
ጸረ ሴማዊነትን ለመታገል የተመሰረተው አንታይ ዲፋሜሽን ሊግ የተሰኘው ድርጅት በበኩሉ በዚህ አልተስማማም።
"ኤለን መስክ የናዚ ሰላምታ ሳይሆን በደስታ ስሜት ተውጦ የማይሆን ሰላምታ ያሳየ ይመስላል" ሲል ድርጅቱ በኤክስ ገጹ አስፍሯል።
የመስክ ታማኝ እና ከቀኝ አክራሪዋ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አንድሪያ ስትሮፓ በበኩሉ "የሮማ ኢምፓየር (ግዛት) መመለስ በሮማውያን ሰላምታ ተጀምሯል" ሲል የመስክን ክሊፕ በማጋራት መለጠፉን የጣሊያን ሚዲያ ዘግቧል።
የሮማውያን ሰላምታ የጀርመኑ መሪ አዶልፍ ሂትለር ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በጣሊያኑ የፋሺስት ፓርቲ መሪ ቤኒቶ ሙሶሎኒ በስፋት ይጠቀምበት የነበረ ነው።
ስትሮፓ በኋላ ላይ ይህንን መልዕክቱን እንደሰረዘው የጣሊያን ሚዲያ አክሎ ዘግቧል።
"አንዳንዶች የናዚ ሰላምታ ሲሉ ያሳሳቱት ምልክት ኦቲዝም ያለበት ኤለን ልቤን ልሰጣችሁ እፈልጋለሁ በማለት ስሜቱን የገለጸበት ነው" ሲል መልዕክቱን አስፍሯል።
መስክ ምልክቱን ያሳየው ፖለቲካው ወደ ቀኝ አክራሪነት እየተቀየረ ነው የሚሉ ጉዳዮች እየተሰማ ባለበት ወቅት ነው። በቅርቡ የቀኝ አክራሪ ፓርቲ የሆነውን ኤኤፍዲ እንዲሁም በብሪታንያ የጸረ ስደት ፓርቲ የሆነው ሪፎርም ዩኬን በመደገፍ መግለጫ አውጥቷል።